You are currently viewing ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸውን ለመመገብ ተቸግረዋል

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸውን ለመመገብ ተቸግረዋል

Ahmed Shide- Minster of Finance – FILE

ዋዜማ- በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ዩንቨርስቲዎች መንግስት በመደበው በቀን 22 ብር በጀት ተማሪዎችን በቀን ሦስት ጊዜ ለመመገብ መመገብ እንደተቸገሩና ተመሪዎች ለረሀብ የሚጋለጡበት ዕድል እየተቃረበ መምጣቱን ዋዜማ ካሰባሰበችው መረጃ ተረድታለች።

የጎንደር ዩንቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ይዳኙ ማንደፍሮ፣ ዩንቨርሲቲያቸው ባገጠመው ተማሪዎቹን በቅጡ የመመገብ ችግር የተነሳ፣ ለሌሎች ሥራዎች ከያዘው በጀት ወደ ተማሪዎች ምገባ በማዛወር፣ ምገባውን ለማስቀጠል ጥረት እያደረገ መሆኑን ለዋዜማ ተናግረዋል። ዩንቨርሲቲው፣ መንግሥት በመደበው 22 ብር ተማሪዎቹን በቀን ሦስት ጊዜ መመገብ እንደማይችል ጠቅሰው፣ ምንም ማድረግ ባይቻልም ልጆቹ ችግር ላይ መውደቅ ስለሌለባቸው፣ በተለያዩ ጥረቶች ከዚህ ቀደም የነበረው ምገባ እስከአሁን አልተቋረጠም ብለውናል።

የሕዝብ ግንኙነቱ እንደሚሉት፣ ዩንቨርሲቲው በክልሉ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ዘግይቶ ተማሪዎቹን መቀበሉ፣ እንዲሁም ለተማሪዎች የሚቀርበው ምግብ ኹሉም ግቢ ውስጥ የሚዘጋጅ መሆኑ የምግብ ለውጥ ሳያደርግ እንዲቀጥል አስችሎታል። ዩንቨርሲቲው በቀጣይ ዓመት መስከረም ላይ የሚቀበላቸውን ተማሪዎች እስከ ቀጣዩ ሰኔ ወር ድረስ ለመመገብ፣ አሁን ላይ በተቀመጠው በጀት የማይታሰብ እንደሆነ ለዋዜማ ነግረዋታል። ከጊዜ ወደ ጊዜ የምግብ ዋጋ እየጨመረ ስለሆነ፣ መንግሥት ያስቀመጠው በጀት ከሦስት ወር የዘለለ ለመመገብ አያስችልም ያሉት ኃላፊው፣ መንግሥት ይህን አይቶ የበጀት ጭማሪ ካላደረገ መጪው የትምህርት ዓመት ከባድ ነው ሲሉም ስጋታቸውን ገልፀዋል።

የወልቂጤ ዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፋሪስ ደሊል (ዶ/ር) መንግሥት ለአንድ ተማሪ የዕለት የምግብ ወጪ የመደበው 22 ብር የማይበቃ መሆኑን ገልጸው፣ ዩንቨርሲቲው ለሌላ ከያዘው በጀት በማዛወር ተማሪዎችን እየመገበ መሆኑን ለዋዜማ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ በጀቱ በቂ እንዳልሆነ እና እየተቸገርን መሆኑን መንግሥት ያውቃል ሲሉ ገልጸው፣ ትምህርት ሚንስቴርም ጉዳዩን በትኩረት ይዞ ጥናት በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል። ግንቦት 08/2016 ከትምህርት ሚንስቴር ጋር በነበረን የጋራ መድረክ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተማሪዎች ቁጥር እና አማካኝ የተማሪ የዕለት የምግብ ወጪ ከዩንቨርሲቲዎች መረጃ ሰብስቧል፣ ስለዚህም በቀጣይ በአጭርና በረዥም ግዜ የሚፈታ ጉዳይ ይኖራል ሲሉ ተናግረዋል።

በአጭር ግዜ ውስጥ መንግሥት አሁን ያለውን የተማሪዎች የዕለት የምግብ ተመንን እንደሚያሻሽል እንጠብቃለን ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ በረዥም ጊዜ ደግሞ ሌሎች አገራት የሚከተሉትን ስርዓት ለመከተል እና ሌሎች አማራጮችን ለመውሰድ ጥናት እየተደረገ መሆኑ ተነግሮናል ብለዋል።

ዩንቨርሲታያችን አሁን ባለው የኑሮ ሁኔታ ለአንድ ተማሪ የዕለት የምግብ ወጪ 120 ብር ቢመደብ አብቃቅቶ መጠቀም ይችላል ሲሉ ገልጸው፣ አሁንም ዩንቨርሲቲው ለአንድ ተማሪ የተጠቀሰውን ያህል ገንዘብ ለዕለት የምግብ ወጪ እያወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ፣ የበጀት ጉድለቱን ተከትሎ የምግብ ቅያሬ መደረጉን ገልጸው፣ ማስተካከያ ባናደርግ ኖሮ ተማሪዎችን መመገብ አንችልም ነበር ነው ያሉት።

መንግሥት ማሻሻያ ሲያደርግ የአገሪቷን አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን ጠቁመው፣ ሆኖም በቀጣይ ማሻሻያ ሲደረግ ስንት ብር ሊሆን እንደሚችል መገመት አልችልም ብለዋል። በቅርቡ ገንዝበ ሚንስቴር ዩንቨርሲቲዎች የቀጣይ ዓመት የበጀት ዕቅዳቸውን እንዲያሳውቁ በጠየቀው መሰረት፣ በጀታችንን ስንሰራ የተማሪዎች የምግብ ወጪን ያሰላነው በነበረው 22 ብር ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ ማሻሻያ ሲደረግ በጀቱ ላይ ጭማሪ ይደረግልናል ብለዋል።

የባህር ዳር ዩንቨርሲቲ ሰላም ካምፓስ የተማሪ ሕብረት ተወካይ በበኩሉ፣ በበጀት ችግር ምክንያት የታጠፉ የምግብ ዝርዝሮች ከመኖራቸው ባለፈ በዚህ ዓመት በሳምንት ኹለት ቀን ለቁርስ ይቀርብ የነበረው የቲማቲም ስልስ እንዲቀር መደረጉን ነግሮናል። ከዚሁ ከበጀት እጥረት ጋር በተያያዘም ዕሮብ እና አርብ ጠዋት ቁርስ ላይ እንጀራ ፍርፍር ይቀርብ የነበረ ሲሆን፣ የአንዱ ቀን ባለፈው ዓመት፣ ቀሪው ደግሞ ዘንድሮ እንዲታጠፍ ተደርጎ ሻይ እና ዳቦ ብቻ እንዲቀርብ መደረጉን ጠቁሟል። ከእነ ጉድለቱም ቢሆን ለተማሪዎች የሚቀርበው ፓስታ ጥሩ ነው ያለው ተወካዩ፣ በቀጣይ ይህም ይቀራል የሚል ስጋት በተማሪዎች ዘንድ መኖሩን ጠቁሟል። የሚለወጥ እና የሚሻሻል ነገር ስለሌለም ተማሪዎች ችግሩን አውቀው ተቀብለውታል ያለው የተማሪዎቹ ተወካይ፣ ችግሩ በኹሉም የዩንቨርሲቲው ካምፓሶች ተመሳሳይ መሆኑን መረዳቱንም ጠቅሶልናል።

ስሜ እንዲጠቀስ አልፈልግም ያሉን አንድ የጅማ ዩንቨርሲቲ የሥራ ኃላፊም፣ ዩንቨርሲቲው ያልተከፈል ብዙ የምግብ ዕዳ እንዳለበት ለዋዜማ ገልጸዋል። ምግብ ለማቅረብ ከዩንቨርሲቲው ጋር ኮንትራት የገቡ ነጋዴዎችም እናቀርብም እያሉ ያስፈራሩናል ያሉት ኃላፊው፣ መንግሥት ከመደበው በጀት አንጻር “በተዓምር” ነው ተማሪዎችን እየመገብን ያለው ሲሉም የሁኔታውን ከባድነት ተናግረዋል።

ለአራት ሰው መቅረብ ያለበትን ምግብ ለሦስት ሰው ወይም ለ20 ሰው የሚቀርበውን ምግብ ለ15 ሰው በማቅረብ ቁርስ፣ ምሳ እና እራት እንዲመገቡ ለማድረግ እንደሚሞከርም አመልክተዋል።

ዩንቨርሲቲው በስሩ የሚያስተዳድረውን ሆስፒታል ጨምሮ ትልቅ የገንዘብ እጥረት እንዳለበትም የጠቆሙት ኅላፊው፣ “በ22 ብር አንድን ሰው ቁርስ፣ ምሳ እና እራት መመገብ አሁን ባለው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው፤ በዚህ ገንዘብ ተማሪዎችን እየቀለቡ ያሉ ዩንቨርሲቲዎች ሊመሰገኑ ይገባል” ሲሉም የሁኔታውን አስቸጋሪነት አጋርተውናል።

መንግሥት 15 ብር የነበረውን የአንድ ተማሪ የዕለት የምግብ ወጪ ወደ 22 ብር ለማሳደግ ረዥም ጊዜ እንደፈጀበት ጠቅሰው፣ አሁን ያለው የኑሮ እውነታ ስለሚታወቅ በጀቱን በድጋሜ ማስተካከል ግዴታ ነው ብለዋል። ኃላፊው ዩንቨርሲቲው በጉዳዩ ላይ ለመንግሥት ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል።

በዋቻሞ ዩንቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪ የሆነው በረከት በበኩሉ፣ ባለፉት ዓመታት ሲቀርብ የነበረው የምግብ ዝርዝር ላይ ለውጥ ባይደረግም፣ አልፎ አልፎ እንጀራ አለቀ እንደሚባል፤ እንዲሁም የሚቀርበው ምግብ ጥራት እንደሚጎድለውና መጠኑም እያነሰ መምጣቱን ተናግሯል።

ወላይታ ሶዶ ዩንቨርሲቲ በበኩሉ፣ በምግብ ግብዓቶች ዋጋ መጨመር ምክንያት በምግብ አቅርቦት ላይ ማሻሻያ ለማድረግ መገደዱን ከሳምንት በፊት አሳውቆ ነበር።

በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ከዋዜማ ጥያቄ የቀረበላቸው የትምህርት ሚኒስቴር ሀላፊዎች ጉዳዩ የሚመለከተውና በጀት የሚመድበው የገንዘብ ሚኒስቴር ነው በሚል ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል። የገንዘብ ሚኒስቴርን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም። [ዋዜማ]

The post ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸውን ለመመገብ ተቸግረዋል first appeared on Wazemaradio.

The post ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸውን ለመመገብ ተቸግረዋል appeared first on Wazemaradio.

Source: Link to the Post

Leave a Reply