ከ10 ኢትዮጵያውያን ስድስቱ በድህነት አልያም በከፋ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ በጥናት ተገለጸ

65 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የአገሪቱን የምጣኔ ሀብት ሁኔታ “እጅግ መጥፎ ወይም በመጠኑ መጥፎ” እንደሆነ እንደሚያስቡ አፍሮባሮሜትር የጥናት ማዕከል ይፋ አደረገ።

26 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ኢኮኖሚው “መልካም” እንደሆነ ገልጸዋል። ይህ በፈረንጆች 2023 ዓመት የተደረገ ጥናት ውጤት ከሁለት ዓመታት በፊት ከተደረገው ጥናት ጋር ሲነጻጸር የኢኮኖሚ ሁኔታው መጥፎ ነው የሚሉ ዜጎች ቁጥር በ20 በመቶ ሲጨምር ጥሩ ደረጃ ላይ ነው የሚሉ ዜጎች ቁጥርም በተመሳሳይ መጠን ቀንሰዋል። 

አህጉር አቀፍ የጥናት ማዕከል የሆነው አፍሮባሮሜትር የኢትዮጵያ ወኪል ሙሉ ተካ እንደገለጹት በ2023 ዓመት የተደረገው ይህ ጥናት በኢትዮጵያ ሁለተኛ ዙር ሲሆን በአፍሪካ ዘጠነኛው ጥናት ሆኗል። የተደረገው ጥናት ግኝት ዛሬ በአዲስ አበባ ይፋ ሲደረፍ አዲስ ማለዳ እንደሰማችው ጥናቱ የአገሪቱ የምጣኔ ሀብት ሁኔታ በዜጎች ዕይታ ምን ይመሳላል?፣ የዜጎች የነፍስ ወከፍ የኑሮ ደረጃ ምን ደረጃ ላይ ነው? እና የዕለት ተዕለት ኑሮ በልዩ ልዩ መሰረታዊ ፍላጎቶች ልኬት ምን ይመስላል? የሚሉትን ለመመለስ የተሰራ ነው። 

ጥናቱ ከተደረገበት 2023 በፊት በነበሩት 12 ወራት [አንድ ዓመት] ውስጥ ኢኮኖሚው ተዳክሟል ያሉ ዜጎች 64 በመቶ ድርሻን የያዙ ሲሆን 42 በመቶ የሚሆኑት በቀጣዩ አንድ ዓመት ይሻሻላል ብለው እንደሚያስቡ በጥናቱ ተገልጿል። የዜጎች የነፍስ ወከፍ የኑሮ ሁኔታን በተመለከተ 47 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ኑሯቸው መልካም እንዳልሆነ የገለጹ ሲሆን ይህ ቁጥር በ2020 ዓመት 42 በመቶ ነበር። 

ጥናቱን ያካሄደው አፍሮባሮሜትር የጥናት ማዕከል የዜጎችን ዕለታዊ የኑሮ ደረጃ ይበልጥ ለመገንዘብ ያስችላሉ ባላቸው የድህነት ኑሮ ተሞክሮ በሚል ለዕለት በቂ የሆነ የጥሬ ገንዘብ ገቢ፣ ምግብ፣ ንጹህ ውሀ፣ ሕክምና እንዲሁም ምቹ የምግብ ማብሰያ ሁኔታን መዝኗል።    

ከአስር ኢትዮጵያውያን አራቱ ወይም 37 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በየቀኑ የዕለት ገቢ እንደሚቸገሩ የተገለጸ ሲሆን 87 በመቶ የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ በዓመት ውስጥ ቢያንስ አንድ ጊዜ የዕለት ገቢ እጥረት አጋጥሟቸዋል ተብሏል። በተጨማሪም 26 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በቂና ንጹህ ውሃ እንደማያገኙ፣ 18 በመቶ የሚሆኑ ዜጎች በቂ ምግብ እንደማያገኙ እንዲሁም 11 በመቶ የሚሆኑ በቂና ምቹ የምግብ ማብሰያ እንደማያገኙ ጥናቱ አመልክቷል። 

በእነዚህ የድህነት ዕለታዊ መመዘኛዎች ሲጠቃለሉ ደግሞ 61 በመቶ [ከ10 ኢትዮጵያውያን ስድስቱ] በድህነት እና ከዚያ በከፋ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል። በድህነትና ከዚያ በባሰ ደረጃ የሚገኙ ዜጎች ብዛት ከሦስት ዓመታት በፊት 54 በመቶ ነበር። 

በ2023 ዓመት የድህነት ደረጃቸው አነስተኛ ነው የተባሉ ዜጎች 34 በመቶ ሲሆኑ በሦስት ዓመታት ውስጥ ከአራት በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ከእነዚህ የድህነት መመዘኛዎች ውጪ የሆኑት ስድስት በመቶ ብቻ የሚሆኑት ናቸው። 

ግኝቶችን በተመለከተ ወቅታዊ እውነታዎች በባለሞያ የቀረበ ሲሆን ጠቅላላ አገራዊ ምርት 130 ቢልየን ዶላር መሆኑ፣ 14 በመቶ የሚሆን የሚታረስ መሬት መኖር፣ በዓለም ደካማ የምግብ ዋስትና ካላቸው አገራት አንዷ መሆኗ የጥናቱን ግኝቶች የሚደግፉ ሆነው ቀርበዋል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የድህነት ወለል መለኪያ ዕለታዊ ገቢው 17 ብር እና ከዚያ በታች የሆነ ዜጋ ድሃ የሚባል ሲሆን በዚህ ስሌት 23 በመቶ የሚሆነው ኢትዮጵያዊ ድህነት ውስጥ መሆኑን ያሳያል። የዓለም ባንክ በሚያወጣው ዓለም አቀፍ መስፈርት ደግሞ ዕለታዊ ገቢ 2.15 የአሜሪካ ዶላር ሲሆን 29.13 በመቶ ኢትዮጵያውያን በዚህ ስሌት ድህነት ውስጥ ናቸው ማለት ነው። 

የዜጎች የኑሮ ደረጃ እና አገር አቀፍ የምጣኔ ሀብት ሁኔታ የተስተካከለ እንዲሆን ተስፋ ይሆናሉ ከተባሉ ጉዳዮች መካከል የኢንዱስትሪ እና የግብርና ዘርፍ የሚታየው መጠነኛ እድገት እንዲሁም በሰራተኝ እድሜ ክልል ወይም ወጣቶች በብዛት መኖር ዋነኞች ናቸው። የኢኮኖሚ ምሁሩ አንዷለም ጎሹ እንደገልጹት ግጭቶችና የሰላም እጦት ለአገርም ሆነ ለነፍስ ወከፍ ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ የሚዳርጉ በመሆናቸው አገራዊ ምክክሩ ዋነኛ መፍትሄ እንደሚሆን ጠቁመዋል። 

አብዛኛውን የኢትዮጵያ ክፍሎች ያዳረሰ ጥናት ነው። የኢትዮጵያን ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ድርሻ የሚወስዱ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በዋነኛነት የገጠር አካባቢ ነዋሪዎች እና ወጣቶች የተሳተፉበት ሲሆን በዘፈቀደ የተመረጡ 2 ሺህ 400 ሰዎች በገጽ ለገጽ ቃለ መጠይቅ እንዲሁም መጠይቅ ጥናቱ እንደተሰራ አዲስ ማለዳ ሰምታለች።

Source: Link to the Post

Leave a Reply