You are currently viewing ከ200 ሺህ በላይ ሕዝብ የሚገለገልበት ሆስፒታል ሙሉ በሙሉ ወድሟል።  የአማራ ሚዲያ ማእከል ሕዳር 30/2014 ዓ.ም  አዲስአበባ ኢትዮጵያ የመጨረሻ አቅሙን ተጠቅሞ የአማራ ሕዝብ በኢኮኖሚ…

ከ200 ሺህ በላይ ሕዝብ የሚገለገልበት ሆስፒታል ሙሉ በሙሉ ወድሟል። የአማራ ሚዲያ ማእከል ሕዳር 30/2014 ዓ.ም አዲስአበባ ኢትዮጵያ የመጨረሻ አቅሙን ተጠቅሞ የአማራ ሕዝብ በኢኮኖሚ…

ከ200 ሺህ በላይ ሕዝብ የሚገለገልበት ሆስፒታል ሙሉ በሙሉ ወድሟል። የአማራ ሚዲያ ማእከል ሕዳር 30/2014 ዓ.ም አዲስአበባ ኢትዮጵያ የመጨረሻ አቅሙን ተጠቅሞ የአማራ ሕዝብ በኢኮኖሚ እንዲሽመደመድ እና በማኅበራዊ ሕይወቱ እንዲጎሳቆል የጥፋት ተልዕኮውን እየፈጸመ ነው። አሸባሪ ቡድኑ በየደረሰበት ሁሉ የጤና ተቋማትን የጥቃቱ ዒላማ አድርጓል። አሸባሪ ቡድኑ የዋድላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ላይ 42 ሚሊዮን ብር የሚገመት ዝርፊያ እና ውድመት ፈጽሟል። የአሚኮ የጋዜጠኞች ቡድን በቦታው ተገኝቶ እንደተመለከተው ሁሉም የሆስፒታሉ ክፍሎች ምንም አይነት አገልግሎት እንዳይሰጡ ተደርገው ወድመዋል። መድኃኒቶች፣ የሕክምና ቁሳቁስ እና መሣሪያዎች ተዘርፈዋል። በውድ ዋጋ የተገዙ ትላልቅና ዘመናዊ የሕክምና ማሽኖችም እንዳልነበሩ ሆነው ወድመዋል። እጅግ ዘመናዊ እና ከፍተኛ ወጪ የተደረገባቸው የሕክምና ማሽኖች ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ ሆነዋል። የጉበት እና የኩላሊት በሽታን ጨምሮ ከ60 በላይ ናሙናዎችን በአንድ ጊዜ መርምሮ ውጤት ማሳወቅ የሚችል ማሽን አሁን እንዳልነበር ሆኗል። ከሰው ንክኪ ነጻ በሆነ መንገድ የሚሠሩ ዘመናዊ ላብራቶሪዎች ከጥቅም ውጭ ተደርገዋል። በየዕለቱ ከ60 በላይ ሰው የሚገለገልባቸው እና እያንዳንዱ ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ዘመናዊ የኤክስሬይ ማሽኖችም አገልግሎት እንዳይሰጡ ተደርገዋል። በሕይወት እና በሞት መካከል ያለን ሰው ለማትረፍ የሚያገለግሉ ዘመናዊ የቀዶ ሕክምና ማሽኖች ወድመዋል። አሚኮ በቦታው ተገኝቶ እንደተመለከተው እነዚህ ዘመናዊ መሳሪያዎች በሙሉ በአዲስ ካልተተኩ በስተቀር አገልግሎት መስጠት አይችሉም። በመሰረተ ልማቶች ላይ የደረሰው ከፍተኛ ውድመትም ሆስፒታሉን በአስቸኳይ አደራጅቶ ሥራ ለማስጀመር ትልቅ ሥራ የሚጠይቅ ነው። ዝርዝር ጥናት ማድረግ የሚያስፈልግ ቢሆንም የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ ተስፋዬ ፋንታሁን ተቀራራቢ ባሉት ዋጋ መሰረት ሆስፒታሉ 42 ሚሊዮን ብር የሚገመት ውድመትና ዝርፊያ ተፈጽሞበታል። በዚህም ምክንያት ተመላላሽ እና ተኝቶ ታካሚዎች፣ የቀዶ ሕክምና ፈላጊዎች፣ ድንገተኛ ታካሚዎች፣ የወሊድ እና ቅድመ ወሊድ አገልግሎት ፈላጊዎች ለከፍተኛ የጤና ቀውስ ተጋልጠዋል። በተለይ ጊዜ የማይሰጡ እንደ ደም ግፊት፣ የስኳር በሽታ፣ ቲቢ፣ ወባ፣ የወሊድ ክትትል እና ሌሎች የሕክምና አገልግሎቶች ማግኘት ያልቻሉ በርካታ ሰዎች ለሞት እና ለከፋ የጤና ችግር ተዳርገዋል። ቀሲስ ሰማኝ አዳነ በሕክምና እጦት ምክንያት የእናታቸውን ሕይወት መታደግ አልቻሉም። በደም ግፊት እና ተያያዥ የጤና ችግር ለረጅም ጊዜ በሕክምና ድጋፍ ነበር የእናታቸው ሕይወት የቆየው። ጠላት ኮን እና አካባቢውን በግፍ በወረረ ጊዜ ሆስፒታሉን ጨምሮ ጤና ተቋማት በሙሉ አገልግሎት መስጠት ሲያቆሙ፣ የህክምና ባለሙያዎችም አካባቢውን በአሸባሪው ቡድን ግፍ ሲለቁ በደም ግፊት ሲሰቃዩ የነበሩት እናታቸው ሕይወት አለፈ። የሕክምና ድጋፍ ባለመግኘታቸው ምጥ ጸንቶባቸው ህይወታቸው ያለፈ እናቶችም መኖራቸውን ሰምተናል። ከፍተኛ ርብርብ አድርጎ ሆስፒታሉን በፍጥነት ማደራጀት እና ሥራ ማስጀመር ካልተቻለ እስካሁን ከነበረው የከፋ የጤና ቀውስ ሊከሰት እንደሚችልም ተመላክቷል። እናም የወደሙ መሠረተ ልማቶችን በአስቸኳይ ጠግኖ ለአጎራባች ወረዳዎች አገልግሎት የሚሰጠውን ሆስፒታል ዳግም ሥራ ለማስጀመር የሚባክን ጊዜ መኖር የለበትም። ለዚህም የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ፣ ጤና ሚኒስቴር እና ሕዝብ ወዳድ የሆኑ ሁሉ የአቅማቸውን እንዲያደርጉ ሥራ አስኪያጁ ጥሪ አቅርበዋል። ሆስፒታሉ በ2009 ዓ.ም መጨረሻ ነበር አገልግሎት መስጠት የጀመረው። በወቅቱ የግንባታ ዋጋ ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ዘመናዊ ሆስፒታል ከ 200 ሺህ በላይ የዋድላ እና አጎራባች ወረዳዎችን በሕክምናው ተደራሽ አድርጎ ነበር። ታዲያ አራት ዓመታት እንኳን አገልግሎት ሳይሰጥ ነው አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን የቻለውን ዘርፎ ቀሪውን ያወደመው። አሚኮ

Source: Link to the Post

Leave a Reply