
” #ከ200 በላይ መገደላቸውን እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ አማሮች መታሰራቸውን ተመድ አስታወቀ” በአማራ ክልል በተፈጠረው ግጭትና ግጭቱን ለመግታት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀበት ጊዜ አንስቶ ከአንድ ሺሕ በላይ ሰዎች መታሰራቸውን፣ እንዲሁም ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር አስታወቁ፡፡ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ ሰሞኑን በተጀመረው የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ጉባዔ ላይ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታን የተመለከተ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን፣ በዚህም ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እየተፈጸመባቸው ናቸው ያሏቸውን አገሮች በመጥቀስ ዋና ዋና ጥሰቶቹንም ዘርዝረዋል። ኮሚሽነሩ በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ረገድ በአሳሳቢነት ከጠቀሷቸው አገሮች መካከል ኢት…ዮጵያ፣ ኢራን፣ ፓኪስታን፣ ሊቢያ፣ ሊባኖስ፣ ቱኒዚያና ፔሩ ይገኙበታል። በአማራ ክልል በፌዴራል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና በአማራ ክልል በሚንቀሳቀሰው የፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ከደረሷቸው ሪፖርቶች መረዳታቸውን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። ግጭቱን ለመግታት የፌዴራል መንግሥት በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከጣለ ጀምሮም ከ1,000 በላይ ሰዎች መታሰራቸውን ጠቁመዋል። በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በቀጠለው ግጭት ሳቢያም ግድያ፣ እንግልትና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መኖራቸውን ገልጸዋል። በትግራይ ክልልም እንዲሁ የጅምላ እስራትና አስገድዶ የማፈናቀል ተግባራት መኖራቸው ተገልጿል። እነዚህ ሁሉ ክስተቶች ተመርምረው ጥሰቶቹን የፈጸሙ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ ይገባልም ብለዋል። በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተፈጸሙ ሰብዓዊ ጥሰቶችን በተመለከተ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በአገሪቱ መንግሥት የታቀደውን የሽግግር ፍትሕ ተግባራዊ ለማድረግ፣ በተጀመሩ ምክክሮች ውስጥ የተገኘውን ዕድገት ዕውቅና ሰጥተዋል። የሽግግር ፍትሕንና ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚያበረታቱ የተናገሩት ኮሚሽነሩ፣ በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ የተጀመረው ምክክር እንዲጎለብት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ሴቶችን ጨምሮ ቀጣይ ውይይት እንዲደረግበት አሳስበዋል ።
Source: Link to the Post