ከ30 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆኗ ከፍትኛ ወጪ አለው ብለን ለባለሥልጣናት ስናሳስብ ነበር- የፍሬይተርስ ኢንተርናሽናል መስራች ዳንኤል ዘሚካኤል

ወቅታዊ ከሆነው የኢትዮጵያም ሆነ ዓለም አቀፍ የባህር በር ፍላጎት አስቀድመን ከሥስት አስርት ዓመታት በፊት ህወሓት እና ሻዕቢያ እንግሊዝ አገር ለንደን ከተማ የፈረሙት ኢትዮጵያ የባህር በር ስላጣችበት ስምምነት የፍሬተርስ ኢንተርናሽናል መስራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳንኤል ዘሚካኤል ነግረውናል። 

ፍሬይተርስ ኢንተርናሽናል በመርከብ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ እንዲሁም የየብስ ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ላለፉት 30 ዓመታት ሲሰራ የቆየ ሲሆን በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ደረጃ ሥመ ጥር የመርከብ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ነው። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1990 በፊት ከነበሩበት ከኢትዮጵያ የንግድ መርከብ በመውጣት የራሳቸውን የመርከብ ድርጅት ያቋቋሙ ሲሆን፤ በ1994 ደግሞ የዴንማርኩ መርስክ (MAERSK) ኩባንያ ወኪልም ሆኗል።

የፍሬይተርስ ኢንተርናሽናል መስራች ዳንኤል ዘሚካኤል የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር “የሻዕቢያ መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ እና የህወሓት መሪ መለስ ዜናዊ ባሉበት ስብሰባ ኢትዮጵያ 85 ሚሊዮን ህዝብ ስላለባት የባህር በር ያስፈልጋታል” ማለታቸውን በቅድሚያ ያወሳሉ።

“አሰብም ከኤርትራ ያልተካለለ በመሆኑ በአጼ ኃይለስላሴም ሆነ በደርግ ስርዓት ከኤርትራ ውጭ ሆኖ በወሎ ግዛት የተካለለ ስለነበር ቀደም ሲልም አሰብ ከኤርትራ ውጪ ሆኖ በጣሊያንም ብዙ ያልተደፈረች የኢትዮጵያ የባህር በር እንደነበረች ይታወቃል። አሰብ የኢትዮጵያ የባርህ በር መሆን አለባት” ሲሉ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ስለመግለጻቸውም ዳንኤል ዘሚካኤል ያስታውሳሉ።

ይሁን እንጂ በወቅቱ የህወሓት መሪ የነበረው መለስ ዜናዊ አጼ ኃይለስላሴም ሆኑ ደርግ ያስቀመጡት ካርታ አስተዳደራቸው እንደማይቀበል ገልጸው አሰብ የኤርትራ መሬት መሆኑን አውጀው ነበር። “ብንፈልግ ጂቡቲን አሊያም የሶማሊያ እና የኬኒያን ወደቦች እንጠቀማለን። አሰብ የኤርትራ ስለሆነ እምነታችንም ይህ በመሆኑ አሰብ የኤርትራ እንጂ የኢትዮጵያ አይደለም” በማለት ጉዳዩን ቋጭተዋል።

“በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ በአጼ ኃይለስላሴ እንዲሁም በደርግ ዘመነ መንግስት በወሎ ጠቅላይ ግዛት ስር ይተዳደር የነበረውን የአሰብ ወደብ አጣች” ሲሉ የፍሬይተርስ ኢንተርናሽናል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል። 

ከ30 ዓመታት በፊት በአሰብ ወደብ በኩል 80 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ እቃ ይጓጓዝ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ የወጪ ገቢ ንግድ በጅቡቲ ወደብ ላይ የተመሰረተ ነው። ከ30 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆኗ ከፍትኛ ወጪ አለው እያሉ በየአጋጣሚው ለመንግስት ባለስልጣናት ያሳስቡ እንደነበረ የሚገልጹት በዘርፉ የረጅም ዓመታት ባለሞያው ዳንኤል፤ “በወቅቱ ከባለስልጣኖቹ  ያገኘነው ምላሽ የወደብ አባዜ የያዛቸው” እና “ከወደብ ጋር ተጣባቂ ነገሮች” አድርገው ያስቡን ነበር ብለዋል።

በወቅቱ “በማይታወቅ ምክንያት ኢትዮጵያ የራሷ ወደብ እንዲኖራት ምንም አይነት ግፊት አልተደረገም መንግስትም ትኩረት ሳይሰጠው አልፏል” ሲሉም በቁጭት ይገልጻሉ።  ለድርጅታቸው ፍሬይተርስ ኢንተርናሽናልም ትልቁ ፈተና ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላት መሆኑ እንደሆነ  ዋና ስራ አስፈጻሚው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ወደብ አልባ መሆን እንደልብ ተንቀሳቅሶ ለመስራት ሁኔታዎችን አስቸጋሪ እንደሚያደርግም ዳንኤል ዘሚካኤል ተናግረዋል።

ምክንያቱን ለአዲስ ማለዳ ሲገልጹ የሦስተኛ ወገን ወደብ፤ በአሥተዳደራዊ እና በንግድ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ የተቀመጡ ሕጎች በርካታ ለአገር ፋይዳ ያለቸው ጉዳዮች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራሉ ብለዋል። “የኢትዮጵያ ህዝብ ወደብ አልባ መሆኑ ይቆጨዋል። እኛም በዘርፉ ያለነው ጭምር፤ ነገር ግን ገፍተን አልሄደም። የሆነ አካል ሊፈጽመው ይገባ ነበር” ሲሉም ባለሞያው ገልጸዋል።

ዳንኤል ዘሚካኤል “የሆነውም ይኼ ነው” ሲሉ በታህሳስ ወር መጨረሻ በኢትዮጵያ መንግስት እና ሶማሊላንድ ራስ ገዝ አስተዳደር መካከል የተደረሰውን ስምምነት “ወሳኝ እርምጃ” እንደሆነም ገልጸዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ራስ ገዝ የሆነችው ሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ ኢትዮጵያ የባሕር በር የምታገኝበትንና ሶማሊላንድ የአገርነት እውቅና ታገኝበታለች የተባለውን የመግባቢያ ስምምነት ታህሳስ 22 ቀን 2016 መፈራረማቸው አይዘነጋም። 

ይኼን ተከትሎ የሶማሊያ መንግስት ስምምነቱ ሕጋዊ መሠረተ የሌለው እና ተፈጻሚ ሊሆን የማይችል ነው ሲል አጣጥሎታል። በአንጻሩ የኢትዮጵያ መንግስት “በዚህ ስምምነትም የሚጎዳ አካልም ሆነ ሀገር አይኖርም፣ የተጣሰ ሕግና የተሰበረ እምነትም የለም” ሲል ባወጣው መግለጫ ገልጿል። የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መንግስት ግንኙነት መሻከር ግን በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ጭምር ተንጸባርቋል። 

“የኢትዮጵያ የወደብ ፍላጎት ሰፊ ነው። ከሶማሊላንድ ጋር በተደረሰው ስምምነት ኢትዮጵያ የምትፈልገው ሰርቪስ ማሳደግ ይቻላል” ሲሉ የፍሬይተርስ ኢንተርናሽናል መስራች ተናገረዋል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የባህር ኃይል እንደነበራት አስታውሰው በዘመነ በኢሕአዴግ ጊዜ ‘ቤዝ’ ስላነበረ ባህር ኃይል ሊፈርስ ችሏል ብለዋል። ስለሆነም “ወደብና መርከብ ከአገር ህልውና ጋር የተያያዘ ነው። ወደድንም ጠላንም ወደብ አስፈላጊ ነው። የባህር በር መኖሩ አገራችንን በኢኮኖሚም ሆነ በደህንነት ለማሳደግ አስተዋጽኦ ያደርጋል” በማለት የፍሬይተርስ ኢንተርናሽናል መስራች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። 

እንደ ዳንኤል ዘሚካኤል ገለጻ “ኢትዮጵያ ሰፊ ይዞታ ስላላት ተጨማሪ ወደቦችን ማለትም ከኤርትራ፣ ሶማሊያ እንዲሁም ለኢትዮጵያ የደቡብ ክፍል ቅርበት ያለውን የኬንያውን ላሙ ወደብ በመጠቀም የኢትዮጵያን ወጪ እና ገቢ ንግድ ማቀላጠፍ ያስችላል” ብለዋል።

በኬንያ የሚገኘው የላሙ ወደብ በደቡብ ኢትዮጵያ ክፍል አገልግሎት እንዲሰጥ አንዳንድ ሂደቶች መጀመራቸውን በተጨማሪም የሱዳን ፖርት በተወሰነ ደረጃ ከዚህ ቀደም አገልግሎት ይሰጥ እንደነበረና አሁን በሱዳን ባለው ግጭት ምክንያት መቋረጡን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የትኛውም ወደብ ጥቅሙ የሚለካው ከአገልግሎት አሰጣጡ፣ ርቀቱ እና ምጣኔ ሐብታዊ ከሚያስገኘው ትርፍ አንጻር ነው የሚሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ስለዚህ ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ የምትጠቀመው ወደብ ካለ “ይኼ ዋስትናዋ ነው” ብለዋል።

ነገር ግን አፍሪካ ውስጥ “ወደብ ከግዛት ጋር የተያያዘ ነው። በሌላው ዓለም ማንኛውም አካል አቅም ካለው ወደብ መግዛት ይችላል። ይኼ ቢዝነስ እንጂ ፖለቲካ አይደለም። ሆኖም ግን በአፍሪካ የወደብ ጥያቄ የፖለቲካ ጨዋታ ነው” ሲሉ ዳንኤል ዘሚካኤል አጽንኦት ሰጥተዋል።

ሁሌም የወደብ ጥያቄ ሲነሳ የፖለቲካ ውጥረት ይኖረዋል የሚሉት ዳንኤል ሶማሊላንድ ላይ እንኳን በመንግስት ደረጃ መደበኛ የቢዝነስ ሰዎች ሄደው ስምምነት ቢፈጽሙ የሶማሊያ መንግስት መቃወሙ የማይቀር መሆኑን አመላክተዋል። በተመሳሳይ ነጻነቷን ካገኘች 30 ዓመታት ያለፏት ኤርትራ “ወደቧን ለኢትዮጵያ ብትከፍት ገቢ ታገኛለች፤ በቃ ያለው ይኼ ነው። ነገር ግን አፍሪካ ውስጥ ብዙ ይቀረናል። ተዋሕዶ፣ ተባብሮ ለማደግ ሲሰራ አይታይም” በማለት ሞያዊ እይታቸውን ገልጸዋል። 

አሁን በ20 ሚልየን ብር ካፒታል የሚንቀስቀሰው እና 145 ሠራተኞች ያሉት ፍሬይተርስ ኢንተርናሽናልን የሚያስተዳድሩት ዳንኤል ዘሚካኤል ከጅቡቲ ወደብ ወደ ኢትዮጵያ በዓመት ወደ 400 ሺህ ኮንቴይነር እንዲሁም በጭነት መኪናዎች እንደ ነዳጅ፣ ማዳበሪያ፣ ስንዴ እና የመሳሰሉት አራት ሚሊየን ቶን ይጓጓዛል ተብሎ እንደሚገመት አመላክተዋል።

የሆነው ሆኖ ይላሉ ዳንኤል፤ “ይሄን ሁሉ ህዝብ ይዘን ያለወደብ የሚቀጠልበት መንገድ የለም። እንዴት ነው የኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ከታሪክ አመጣጥ ሂደት ሊቀየር የቻለው? ያ ታሪካዊ ሂደት እንዴት ሊፈጸም ቻለ? የሚለውን ልናስብበት የሚገባ ጉዳይ ነው” ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ አጽንኦት ሰጥተዋል። 

እንደ ዳንኤል ዘሚካኤል ገለጻ፤ የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነት እንደሚሳካ ተስፋ በማድረግ ሃሳብ ያለው በሃሳቡ ታሪክ የሚያውቅ በታሪክ ኢትዮጵያን የነበረችበት ቦታ መመለስና ለአዲሱ ትውልድ ማውረስ ግዴታ ነው። 

Source: Link to the Post

Leave a Reply