ከ40 በላይ የኪነጥበብ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ባህላዊ የሙዚቃ ትርኢት ሊካሄድ ነዉ፡፡ሉሲ ድንቅነሽ-ኢትዮጲያ ባህላዊ የሙዚቃ ትርኢት በሚል የሚካሄድ ሲሆን ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ያስተባ…

ከ40 በላይ የኪነጥበብ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ባህላዊ የሙዚቃ ትርኢት ሊካሄድ ነዉ፡፡

ሉሲ ድንቅነሽ-ኢትዮጲያ ባህላዊ የሙዚቃ ትርኢት በሚል የሚካሄድ ሲሆን ባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ያስተባብረዋል ተብሏል፡፡

ሶስት አመታትን ፈጅቷል የተባለው ዝግጅቱ በጥቂት ወራት ውስጥ ለህዝብ እንደሚቀርብም ይጠበቃል፡፡
ስያሜውን ከ3.2 ሚሊየን አመታት በላይ እድሜ ካላት የሰው ልጆች ዝግመተ ለውጥ ማሳያ ከሆነችው ሉሲ ጋር ማስተሳሰር ያስፈለገውም፣ የኪነጥበብ ስራዎችን ለመላው የሰው ልጆች ለማቅረብ ከማሰብ አንፃር ነው ተብሏል፡፡
የኪነጥበብ ስራዎቹን በማዘጋጀት ገጣሚ ፣ ፀሐፈ ተውኔት እና መምህር ጋሽ አያልነህ ሙላቱ፣ ክቡር ዶክተር ሙላቱ አስታጥቄ እና ከ40 በላይ ወጣት የኪነጥበብ ባለሙያዎች መሳተፋቸውም ታውቋል፡፡

ሉሲ ድንቅ ነሽ ኢትዮጲያ ባህላዊ የሙዚቃ ትርኢት የ7 ሚሊየን ብር ፕሮጀክት መሆኑን ያስታወቁት በባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነጥበብ ስነጥበብ እና ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ነፊሳ አልመህዲ ሲሆኑ 2 ሚሊየን የሚሆነዉ ከመንግስት የተገኘ እና ቀሪው ከህዝብም ተሳትፎ የሚገኝ ይሆናል ብለዋል፡፡

ለዘርፉ ከፍተኛ ወጪ እንደሚያስፈልግ ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ በመንግስት በኩል ዝግጅቱ ግቡን እስከሚመታ ድረስ ድጋፉ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል፡፡
ገጣሚ ፣ ፀሐፌ ተውኔት እና መምህር ጋሽ አያልነህ ሙላቱ ኪነጥበብ በበርካታ ችግሮች ወቅት ለህዝቦች መውጫ ቀዳዳን አበጅታለች ብለዋል፡፡ ‹‹ በእናት ሃገራችን ለተፈጠሩ ችግሮች መውጫ መንገድም እናገኝበታል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሉሲ ድንቅ ነሽ ኢትዮጲያ ባህላዊ የሙዚቃ ትርኢት መሰናዳቱ ለሃገራችን የሚኖረውንም አስተዋጽ ገፅታችንን ከማደስ አንፃር፣ የጥበብን ሽግግር በጥበበኞች መካከል ተቀናጅቶ መስራትን ለማበረታታት እና ህዝባዊ ትስስራችንን የበለጠ ለማጠናከር ይረዳናል ብለዋል፡፡

ጋሽ አያልነህ አክለውም ኪነጥበብ በፖለቲካው ውስጥ ለተፈጠሩ ችግሮችም መፍቻ ይሆነናል ብለዋል፡፡

ክቡር ዶ/ር ሙላቲ አስታጥቄ በበኩላቸው የሉሲ ድንቅ ነሽ ኢትዮጲያ ባህላዊ የሙዚቃ ትርኢት ለሃገር ውስጥ እና ለአለም አቀፍ አድማጭ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሉሲ ድንቅ ነሽ ኢትዮጲያ ባህላዊ የሙዚቃ ትርኢት ከመዝናኛ ባለፈ በርካታ አዳዲስ ነገሮችን ይዞ እንደሚቀርብም ጠቁመዋል፡፡

በአብዱሰላም አንሳር

ሚያዚያ 11 ቀን 2014 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply