ከ50 ቢሊየን ብር ከህዝቡ የሚጠበቀው 10 በመቶ ብቻ ነው- የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 13ተኛ ዓመት የግንባታ ጅማሮን አስመልክቶ በተደረገ የፓናል ውይይት ላይ ግድቡን ለማጠናቀቅ 50 ቢሊየን ብር እንደሚያስፈልግ የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ተናግረዋል። 

ይህ ደግሞ የግድቡ ግንባታ ሲጀመር በ80 ቢልየን ብር ይጠናቀቃል ከመባሉ፣ 95 በመቶ ግንባታው አልቆ ለቀሪው ግንባታ 50 ቢልየን ብር ማስፈለጉ እንዲሁም ገንዘቡ ከየት ይመጣል የሚሉ ጥያቄዎችን ፈጥሯል።

አዲስ ማለዳ አጠቃላይ ግንባታው 95 በመቶ የተጠናቀቀው እና በአንድ ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ እንዴት 50 ቢሊየን ብር አስፈለገው የሚለውን ጉዳይ የግድቡ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤትን ጠይቃለች።

አዲስ ማለዳ ባገኘችው መረጃ መሰረት አሁን ላይ ግድቡ የቀረው የተርባይን ተከላ እና የብረታ ብረት ስራ ነው። አንድ ተርባይን ከዓመታት በፊት የነበረው ዋጋ 70 ሚልየን ዶላር እንደነበረ ደግሞ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት፣ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ኃይሉ አብርሃም በተለይ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። 

“የተርባይን ተከላ ቴክኒካል ስራው ከባድ እና ውስብስብ ነው” የሚሉት ዳይሬክተሩ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚገጠም አንድ ተርባይን ኃይል የማምነጨት አቅሙ 400 ሜጋ ዋት ወይም ከተከዜ ግድብ የማመንጨት አቅም በላይ እንደሆነ አስረድተዋል። 

እስከአሁን በፕሮጀክቱ ሲከናወኑ የነበሩ እንደ ኮንክሪት መሙላት ያሉ ቀላል ስራዎች እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን ቀሪ ስራዎች ግን ከባድ እና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁ እቃዎች የሚያስፈልጉት ደረጃ ላይ ነው ተብሏል። 

የጽህፈት ቤቱ የህዝብ ግንኙነት፣ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር በተለይ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ባለፉት 13 ዓመታት ውስጥ የግድቡ ግንባታ ከ191 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል። እዚህ ጋር በግድቡ ግንባታ ጅማሮ ላይ መጋቢት 24 ቀን 2003 በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የመሰረት ድንጋዩ ሲቀመጥ በስድስት ዓመታት ውስጥ በ80 ቢሊየን ብር ወጪ ተገንብቶ እንደሚጠናቀቅ መገለጹን መዘንጋት አይቻልም።

በ13 ዓመታት ውስጥ ከተሰበሰበው 191 ቢልየን ብር ውስጥ ከኢትዮጵያ ህዝብ የተሰበሰበው ከ19 ቢሊየን ብር በላይ መሆኑን ኃይሉ አብርሃም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። አሁን ለግድቡ ቀሪ ግንባታ ከሚያስፈልገው 50 ቢሊየን ብር ውስጥ ከህዝቡ የሚጠበቀው ቢበዛ 10 በመቶ ብቻ መሆኑን ነግረውናል።

እንደ ኃይሉ አብርሃም ገለጻ 50 ቢልየን ብር ያስፈልጋል ማለት “ስራው ወደ ኋላ ቀርቶ ነው ማለት አይደለም” ብለው በየትኛውም ዓለም የሚሰሩ ትላልቅ ፕሮጀችቶች ከታቀደላቸው ጊዜ በላይ የሚወስዱ በመሆኑ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ደግሞ አጠቃላይ ወጪው በራስ የሚሰራ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል።

ግድቡ ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር ትልቅ ሚና መጫወቱን ያስታወቀው የማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ፤ ግድቡ ከሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አንጻር “የቱንም ያህል ቢፈጅ አዋጭ ነው” ብሏል። “50 ቢልየን ይፈጃል ብለን መስጋት የለብንም” ያሉት የጽህፈት ቤቱ የህዝብ ግንኙነት፣ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ኃይሉ አብርሃም “ሰው ብሩን ሳይሆን የስራውን ግዝፈት ነው መመልከት ያለበት” በማለት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አክለውም “ከአባይ ወንዝ በጭልፋ እንኳን እንዳትነኩ ስንባል የነበርን ህዝቦች ነን። የህዳሴ ግድብ፤ ግድብ ብቻ አይደለም። የአገር ሉአላዊነት ጭምር ነው። የማንነትና የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ ነው” ብለዋል።

የገንዘብ ማሰባሰቢያ መንገዶችን በተመለከተ ከዚህ ቀደም እንደነበረው የቦንድ ሽያጭ፣ 8100 A እንዲሁም በአገር ውስጥ እና በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሚደረግ ስጦታ ሀብት የማሰባሰብ ሂደቱ እንደሚቀጥል ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም በአገር ውስጥ እና በውጭም አገራት የሚገኙ ሰዎች መጠቅም የሚችሉት ዲጂታል አማራጭ በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ አዲስ ማለዳ ከጽህፈት ቤቱ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የኮንክሪት ሙሌት ግንባታ 99 ነጥብ 2 በመቶ ደርሷል። የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ እንድገለጹት በአሁኑ ወቅት የግድቡ የሲቪል ሥራዎች 99 ነጥብ 2 በመቶ እንዲሁም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች አፈፃፀም 79 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል። የውሃ ማስተላለፊያና መቆጣጠሪያ የብረታብረት ሥራዎች አጠቃላይ አፈፃፀም 90 በመቶ ተከናውኗል ተብሏል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply