ከ60 ሺህ በላይ ሶማሊያውያን ወደ ኢትዮጵያ ሸሹ

https://gdb.voanews.com/868A9291-E172-4E3B-B99C-1BC0419706A3_w800_h450.jpg

በአብዛኛው ሴቶችና ሕጻናት የሚገኙበት ከ60 ሺህ በላይ ሶማሊያውያን ግጭትንና አለመረጋጋትን በመሸሽ ላስካኑድ ከተሰኘች ከተማ በመነሳት ወደ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ገብተዋል ሲል የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን አስታውቋል።

ከጀኒቫ የኮሚሽኑ መሥሪያ ቤት የተገኘው መረጃ እንዳመለከተው ፍልሰተኞቹ ዘመዶቻቸው በግጭቱ የተገደሉባቸው አልያም በጦርነቱ ወቅት ከቤተ-ዘመድ የተለያዩ ናቸው።

ድካምና መደናገጥ ይታይባቸው እንደነበርና ለምጓጓዣ እንዲሆናቸው ያላቸውን ጥቂት ንብረት እንደሸጡ በአካባቢው ላሉ ለኮሚሽኑ እና ለተመድ የስደተኞች ወኪል ሠራተኞች ተናግረዋል ሲሉ የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ኦልጋ ሳራዶ ሙር ጀኒቫ ላይ ዛሬ ተናግረዋል:: 

ፍልሰተኞቹ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በዶሎ በሚገኙ 13 መጠለያዎች እንደሰፈሩ ታውቋል።

በአማካይ 1000 የሚሆኑ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ በመሻገር ላይ መሆናቸውንና ፍልሰተኞቹን ለመርዳት የአቅርቦት ውስንነት መኖሩን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ካለው ችግር አኳያም ትምህርት ቤቶችንና የመንግስት ሕንጻዎችን ለመጠለያነት መጠቀም ተገደዋል ተብሏል።

ላስካኑድ ከተሰኘችው ከተማ እስከ አሁን 185 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች መፈናቀላቸውንና አብዛኞቹ ወደ ሶማሊላንድ ሲሄዱ፣ ሌሎቹ ደግሞ ወደ ፑንትላንድና ኢትዮጵያ አቅንተዋል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply