ከ79 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ የሚገኙ ሲሆን ከግማሽ በላይ ሴቶች ናቸው

ረቡዕ ግንቦት 14 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በደቡብ ኦሞ ዞን፣ ዳሰነች ወረዳ በሚያዝያ ወር 2012 በወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት በኩል ምዝገባ የተደረገላቸው 62 ሺህ 790 ተፈናቃዮች ሲሆኑ በኅዳር ወር 2016  ዳግም በተደረገው ምዝገባ የተፈናቃዮች ቁጥር 79 ሺህ 828 ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።

ከተፈናቃዮቹም 42 ሺህ 758 ወይንም 54 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸው አዲስ ማለዳ ከሪፖርቱ ተመልክታለች።

ኢሰመኮ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ የሚገኙ ተፈናቃዮችን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ አስመልክቶ ከጥቅምት 5 እስከ 20 ቀን 2016 የሰብአዊ መብቶች ክትትል ማድረጉን የገለጸ ሲሆኑ በዛሬው ዕለት ባለ 26 ገጽ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

በሪፖርቱም በዳግም ምዝገባው የተፈናቃዮች መረጃ በጾታ፣ በዕድሜ እና በአካል ጉዳት ተለይቶ በተሰባጠረ መልኩ አለመያዙ፤ አብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች ማንነታቸውን የሚገልጽ የቀበሌ መታወቂያ የሌላቸው መሆኑ እንዲሁም በወረዳው ወሳኝ ኩነት ጽሕፈት ቤት አማካኝነት ልደት እና ሞት የሚመዘገብ ቢሆንም ተፈናቃዮች የሰነድ ማረጋገጫ የማይሰጣቸው መሆኑ ማረጋገጡን ገልጿል።

እንዲሁም ተፈናቃዮች የግጦሽ መሬት ፍለጋ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ከሀመር አርብቶ አደሮች ጋር አልፎ አልፎ የሚከሰተው ግጭት ለተፈናቃዮቹ የስጋት ምንጭ ሆኗል ብሏል።

በተመሳሳይም መነሻቸውን ከኬንያ ቱርካና ሐይቅ ዳርቻ ካደረጉ አርብቶ አደሮች ጋር ተፈናቃዮች አልፎ አልፎ ግጭት ውስጥ እንደሚገቡ እና ይህም በአካባቢው የጸጥታ ሁኔታ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ አመላክቷል።

በዳሰነች ወረዳ ከ2012 እስከ 2016  ድረስ በኦሞ ወንዝ ሙላት ምክንያት በሰዎች፣ በእንስሳት፣ በሰብል፣ በግል ንብረቶች እና በመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ የተለያዩ ጉዳቶች ደርሰዋል። እንደ ኮሚሽኑ ገለጻ መሠረት፣ በወረዳው ካሉ 40 ቀበሌዎች 28ቱ ከጠቅላላው የወረዳው የቆዳ ስፋት 65 በመቶው በውሃ ተውጠው ይገኛሉ።

Source: Link to the Post

Leave a Reply