ኬሪያ ኢብራሂም እና ሙሉ ገብረ እግዚብሔር ከህወሓት አባልነታቸው ተሰናበቱ

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በትግራይ ጦርነት ወቅት በፌደራል መንግስት ቁጥጥር ስር ውለው ከነበሩት ከፍተኛ አመራሮቹ ውስጥ፤ ኬሪያ ኢብራሂም እና ሙሉ ገብረ እግዚብሔርን ከማዕከላዊ ኮሚቴ እና ከፓርቲ አባልነታቸው ማሰናበቱን አስታወቀ። በእስር ላይ ከነበሩ አመራሮች መካከል ዶ/ር አዲስ አለም ባሌማ እና ዶ/ር አብርሃ ተከስተ በፓርቲው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነታቸው እንዲቀጥሉ ውሳኔ አሳልፏል።

ህወሓት በከፍተኛ አመራሮቹ ላይ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው፤ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ትላንት ሐሙስ የካቲት 15፤ 2016 ካደረገው ስብሰባ በኋላ መሆኑን ገልጿል። ህወሓት በጦርነቱ ወቅት “በጠላት እጅ ወድቀው ነበር” ያላቸውን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን በተመለከተ “ለረጅም ጊዜ ሲንጓተት” የቆየውን ያስተላለፈው ውሳኔ፤ የነበሩትን ሁኔታዎች በመገምገም እና የፓርቲውን ህገ ደንብ በመከተል መሆኑን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

በዚህም መሰረት “እጃቸውን ለጠላት በመስጠት” እና “ምስጢር አሳልፈው በመስጠት” የተገመገሙት የቀድሞው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ኬሪያ ኢብራሂም እና የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሙሉ ገብረ እግዚብሔር፤ ከማዕከላዊ ኮሚቴ እና ከፓርቲ አባልነታቸው “መባረራቸውን” ህወሓት አስታውቋል። በትላንቱ ሰብሰባ “ከባድ ጸጸት” እንደተሰማቸው መግለጻቸው የተነገረላቸው ሁለቱ ተሰናባቾች፤ ወደፊት “በተሰማሩበት የስራ መስክ ህዝቡን ለመካስ እንደሚሰሩ” ቃል መግባታቸውን የፓርቲው መግለጫ ጠቅሷል። 

ኬሪያ በፌደራል መንግስት ቁጥጥር ስር የዋሉት በትግራይ ክልል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከአንድ ወር በኋላ ነበር። የእርሳቸውን መያዝ በተመለከተ በወቅቱ መረጃውን ይፋ ያደረጉ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን፤ ኬሪያ በገዛ ፍቃዳቸው “ለመንግስት እጃቸውን መስጠታቸውን” መዘገባቸው ይታወሳል። በወቅቱ የህወሓት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የነበሩት ኬሪያ፤ “በመከላከያ ሰራዊ ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈጸም” እና “በሀገር ክህደት ወንጀል” ተጠርጥረው የእስር መያዣ ትዕዛዝ ከወጣባቸው 69 ሰዎች መካከል አንዷ ነበሩ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Source: Link to the Post

Leave a Reply