ኮርፖሬሽኑ ከሦስት አገር በቀል ኩባንያዎች ጋር ለማመረቻ የሚሆን የለማ መሬትና የማምረቻ ሼድ ለማስረከብ የውል ሥምምነት ተፈራረመ

ኩባንያዎቹ በድምሩ ከ430 ሚሊዮን ብር በላይ የኢንቨስትመንት ካፒታል ያላቸው መሆኑ ተገልጿል

አርብ ነሐሴ 13 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ኮርፖሬሽኑ ከሦስት አገር በቀል ኩባንያዎች ጋር ለማመረቻ የሚሆን የለማ መሬትና የማምረቻ ሼድ ለማስረከብ የውል ሥምምነት ተፈራርሟል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በተገኙበት የውል ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኦፕሬሽን ምክክል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሽፈራው ሰለሞን፣ የአፊያን ፒኤል ሲ ሥራ አስኪያጅ አበራ አህመድ፣ የኢላኪም ኢደብል ኦይል ማኑፋክቸሪንግ ፒ ኤል ሲ ተወካይ ሳምሶን እስራኤል እንዲሁም የዶሜይን አልሙኒየም ኮምፖሳይት ፓነል ፒ ኤል ሲ ተወካይ ስምኦን ገ/መስቀል ናቸው። 

በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት መልዕክት ያስተላለፉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሳንዶካን ደበበ፤ የዛሬው ሥምምነት ባለፉት ኹለት ዓመታት የአገር ውስጥ አምራች ኩባንያዎች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ እንዲገቡና ምርት እንዲጀምሩ ሲደረግ የነበረው ከፍተኛ ጥረት ውጤት ማምጣቱን ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አክለውም፤ በተወሰኑ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ላይ ብቻ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው፤ አሁን ላይ ሥምምነት የፈፀሙ አምራች ኩባንያዎች በተለያዩ ሦስት ዘርፎች የተሰማሩ መሆናቸው የዘርፍ ብዝሀነት ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን ስለመሆኑ ማረገገጫ ነው ብለዋል፡፡

በመጨረሻም ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተኪ ምርትን በማምረት፣ የሥራ እድልን በመፍጠር እና የውጪ ምንዛሪን በማዳን ትልቅ አስተዋፅኦ ለሚኖራቸው ለእነዚህ አምራቾች ኮርፖሬሽኑ አስፈላጊውን ኹሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

የየኩባንያዎቹ ሀላፊዎችም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለማምረት ባገኙት እድል ደስተኞች መሆናቸውን፣ ለአገር ውስጥ አምራች ኩባንያዎች እየተሰጡ ያሉ እድሎች ይበል የሚያሰኙ መሆናቸውንና እነርሱም ባስቸኳይ የዝግጅት ምዕራፋቸውን በማጠናቀቅ ወደ ምርት ሂደት ለመግባት አስፈላጊውን ኹሉ እንደሚያደርጉ ማረጋገጣቸውን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ያገኘኘው መረጃ አመላክቷል።

በዛሬው እለት ከኮርፖሬሽኑ ጋር የውል ሥምምነት የተፈራረሙት ሦስቱ የአገር ውስጥ አምራች ኩባንያዎች በድምሩ ከ430 ሚሊዮን ብር በላይ የኢንቨስትመንት ካፒታል ያላቸው ሲሆኑ፤ ወደ ሥራ ሲገቡም ከ520 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራሉ ተብሏል።

ኩባንያዎቹም ኤክስፖርት በማድረግ የውጭ ምንዛሪን ማስገኘት ላይ እንዲሁም ተኪ ምርትን በማምረት ለአገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ ተገልጿል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply