ኹለተኛው ምዕራፍ የኦነግ ሸኔ እና የመንግሥት ድርድር በቅርቡ እንደሚጀመር ተገለጸ

አርብ ግንቦት 4 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ለኹለተኛ ጊዜ በፌዴራል መንግሥት እና በኦነግ ሸኔ መካከል የሚደረገው ድርድር በቅርቡ እንደሚጀመር የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ፡፡

የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ለኹለተኛ ጊዜ በፌዴራል መንግሥት እና በኦነግ ሸኔ መካከል የሚደረገው ድርድር በቅርቡ እንደሚጀመር አሳውቀዋል፡፡

ኃላፊው በሰጡት ማብራሪያ መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በላይ ግጭትን በዘላቂነት ለማቆም፣ የሕዝብን እና የአገርን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስጠበቅ ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይም በኦሮሚያ ክልል በሀሳብ አለመግባባት በመንግሥት እና በኦነግ ሸኔ ኃይሎች መካከል እየተፈጠሩ ባሉ ግጭቶች እየተሰቃየ የሚገኘውን ሕዝብ በዘላቂነት ሰላሙን ለመመለስ እና በነጻነት ወጥቶ እንዲገባ ለማስቻል በሰለጠነ መንገድ ከመወያየት እና ውሳኔ ላይ ከመድረስ በቀር ሌላ አማራጭ የለንም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ለዚህም <<መንግሥት በክልሉ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ወደ ሠላም መንገድ ለመመለስ ብሎም ሃሳባቸውን ለመስማት ዝግጁ ነው።>> ያሉ ሲሆን፤ ሕዝቡ ከጦርነት ወሬ ወጥቶ ወደመደበኛ ሕይወቱ እንዲመለስ እንዲሁም ኑሮውን እንዲያሻሽል መግባባት እና ሠላም ማውረዱ አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በታንዛኒያ ሲደረግ በነበረው ድርድር የተሻለ መቀራረብ እና መግባባት እንደነበረ ያስታወሱት ኃላፊው፤ በቅርቡ በሚደረገው ኹለተኛ ዙር የድርድር መድረክ ይህንኑ ምህዳር በማስፋት ዘላቂነት ያለው ሰላም ለማስፈን መንግሥት አጽንኦት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት ማንኛውም የሀሳብ ልዩነት ያለው ኃይል ሀሳብን በሀሳብ ብቻ እንዲሞግት እና ለዚህም የዴሞክራሲ ምህዳሩ እንዲሰፋ ፍላጎት አለው ብለዋል፡፡ የትኛውም የፖለቲካ ኃይል ከዚህ በፊት ካሳለፍናቻው ጥፋቶች በመማር እና አሁን የተመቻቸውን የውይይት እንዲሁም የድርድር ጅማሮ በመጠቀም ወደ ሰላም መንገድ እንዲመጣም የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው አሳስበዋል፡፡

የሕዝባችንን እና የአገራችንን ሰላም ለመመለስ የተጀመረውን የሰላም ድርድር ለማደናቀፍ እና ከግብ እንዳይደርስ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ሠላም ጠል አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም ኃላፊው ጠይቀዋል፡፡

የተጀመርው ድርድር በስኬት እንዲጠናቀቅም የሐይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች ምሁራን እና መላው ሠላም ወዳድ የኢትዮጵያ ሕዝብ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በኦሮሞ ነጻነት ስራዊት እና የፌዴራል መንግሥት መካከል ሲደረግ የነበረው የመጀመሪያው ዙር ድርድር በታንዛኒያ ራስ ገዝ በሆነቸው ዛንዚባር ደሴት በኬንያ እና በታንዛኒያ አደራዳሪነት ሲደረግ እንደነበር ይታወሳል።

በመጀመሪያው ዙር ድርድር ኹለቱ ኃይሎች ባደረጉት ድርድር ያለ ስምምነት መለያየታቸውን ያስታወቁ ሲሆን፤ ስምምንት ላይ ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች ውሳኝ የሚባሉ የፖለቲካ ጉዳዮች መሆናቸውም ገልጸዋል፡፡

The post ኹለተኛው ምዕራፍ የኦነግ ሸኔ እና የመንግሥት ድርድር በቅርቡ እንደሚጀመር ተገለጸ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply