ኹለት ህጻናትን በአሰቃቂ ኹኔታ ህይወታቸው እንዲያልፍ አድርጋለች ተብላ የተከሰሰችው የቤት ሠራተኛ የግድያ ወንጀሉን አልፈጸምኩም ስትል የዕምነት ክህደት ቃሏን ሰጠች

ማክሰኞ ጥቅምት 22 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ኹለት ህጻናትን በአሰቃቂ ኹኔታ ህይወታቸው እንዲያልፍ አድርጋለች ተብላ የተከሰሰችው የቤት ሠራተኛ የግድያ ወንጀሉን አልፈጸምኩም ስትል በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የከባድ ግድያና ውንብድና ወንጀል ችሎት ቀርባ የዕምነት ክህደት ቃሏን ሰጠች።

ተከሳሽ ህይወት መኮንን ሀይሉ በነሃሴ 26 ቀን 2014 ከጠኋቱ 3:30 ላይ በለሚኩራ ክ/ከ አራብሳ ኮንዶሚኒየም በቤት ሠራተኛነት ተቀጥራ በምትሰራበት መኖሪያ ቤት ውስጥ፤ ምክንያቱ ባልታወቀ ኹኔታ የህጻን ግዮናዊት መላኩ አፏን በማፈን በቢላ በማረድ ህይወቷ እንዲያልፍ ማድረጓንና ህጻን ክርስቲና መላኩን ደግሞ አፏን በማፈን በማነቅ በአጠቃላይ ህፃናቶቹን በአሰቃቂ ኹኔታ ህይወታቸው እንዲያልፍ አድርጋለች ሲል በግድያ ወንጀል እና በወቅቱ የሟች ቤተሰቦችን የሰነድ ማስረጃዎች ቀዳዳ በመጣል በአጠቃላይ በተደራራቢ ክስ ዐቃቤ ህግ በጥቅምት 15 ቀን ክስ መመስረቱ ይታወሳል።

ተከሳሿ ክሱ ከደረሳትና ከተነበበላት በኋላ ጠበቃ የማቆም አቅም እንደሌላት መግለጿን ተከትሎ፤ ፍርድ ቤቱ የመንግስት ተከላካይ ጠበቃ እንዲመደብላት በማዘዝ ማረሚያ ቤት ሆና ጉዳይዋን እንድትከታተል ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።

ተከሳሿ ዛሬ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የከባድ ግድያና ውንብድና ወንጀል ችሎት በነበረ ቀጠሮ ቀርባ የግድያ ወንጀሉን አልፈጸምኩም ስትል የዕምነት ክህደት ቃሏን ሰታለች።

ከሳሽ ዐቃቤ ህግ ለወንጀሉን መፈጸም የሚያስረዱ የሰው ምስክሮች ለማሰማት ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው የጠየቀ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ለጥቅምት 30 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ከችሎት ዘግባለች።

The post ኹለት ህጻናትን በአሰቃቂ ኹኔታ ህይወታቸው እንዲያልፍ አድርጋለች ተብላ የተከሰሰችው የቤት ሠራተኛ የግድያ ወንጀሉን አልፈጸምኩም ስትል የዕምነት ክህደት ቃሏን ሰጠች first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply