ወሊድ እና እርግዝና ወደ ትምህርት ገበታቸዉ እንዳይመለሱ ከፍተኛ እንቅፋት የሆነባቸዉ የኡጋንዳ ሴት ተማሪዎች፡-የኮቪድ 19 መከሰቱን ተከትሎ ትምህርት እንዲቋረጥ ካደረጉ ሃገራት መካከል ኡጋን…

ወሊድ እና እርግዝና ወደ ትምህርት ገበታቸዉ እንዳይመለሱ ከፍተኛ እንቅፋት የሆነባቸዉ የኡጋንዳ ሴት ተማሪዎች፡-

የኮቪድ 19 መከሰቱን ተከትሎ ትምህርት እንዲቋረጥ ካደረጉ ሃገራት መካከል ኡጋንዳ አንዷ ናት፡፡

እነዚህ ትምህርት ያቋረጡ ተማሪዎች በቀጣዩ የፈረንጆች አመት 2022 ትምህርት እንዲጀምሩ ጥሪ የተደረገላቸዉ ሲሆን አብዛኞቹ በማርገዛቸው እና በመውለዳቸው ምክንያት ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ እንደማይችሉ ነዉ የተገለጸዉ፡፡

የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ባሳለፍነው ወር ትምህርት ቤቶች በፈረንጆቹ አዲስ አመት ጥር 2022 እንደሚከፈት አስታውቀው ነበር፡፡

ነገር ግን በብዛኞቹ ተማሪዎች ትምህርት መዘጋቱን ተከትሎ ማግባታቸውን እና መውለዳቸውን እንዲሁም የእርግዝና ጊዜን እያሳለፉ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ከፈረንጆቹ መጋቢት 2020 ጀምሮ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ሁሉም የትምህርት ተቋማት ተዘግተው ቆይተዋል፡፡

እንደ የሃገሪቱ እቅድ እና ትግበራ ባለስልጣን መረጃ ከሆነ ትምህርት ተዘግቶ በመቆየቱ ሳቢያ እስከ 30 በመቶ የሚደርሱ ተማሪዎች እርግዝና ፣ ያለ እድሜ ጋብቻ በለጋ እድሜያቸው ስራ በመጀመራቸው ምክንያት በጥር ወር በሚጀመረው ትምህርት ላይ አይመለሱም ተብሎ ይጠበቃል ብሏል።

ዩኒሴፍ ከፈረንጆቹ መጋቢት 2020 እስከ ያዝነው ወር ያለውን ሁኔታ ባመላከተዉ ሪፖርቱ በኮቪድ 19 ምክንያት ትምህርታቸውን አቋርጠው በቤታቸው ከተቀመጡት ውስጥ 22. 5 በመቶ የሚሆኑትና እድሜያቸዉ ከ10 አመት እስከ 24 የእድሜ ክልል የሚገኙት ተማሪዎች ማርገዛቸውን በሪፖርቱ ማመልከቱን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

በረድኤት ገበየሁ
ህዳር 28 ቀን 2014 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply