
ወቅታዊ ሀገራዊና የማህበሩ ሁነቶችን አስመልክቶ ከአማራ ተማሪዎች ማህበር(አተማ) የተሰጠ መግለጫ የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ፣ የአማራ ተማሪዎች ማህበር(አተማ) ላለፉት አራት ዓመታት በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን የማህበሩ ተቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫዎች በሆኑት የአማራ ተማሪዎች ላይ ከሚደርሰው ተደጋጋሚ ብሔር ተኮር ጥቃት እና እንደ ሕዝብ ከገጠመን ውስብስብ ችግር አኳያ ሲታይ ቀሪ ብዙ ሥራዎች እንዳሉበት ይታመናል፡፡ ማህበሩ በተለይም ችግር ፈቺ የሆኑ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ሲሠራ ከመቆየቱ በተጨማሪ ሐሳቦችን በማመንጨትና ለልዩ ልዩ አካላት በመስጠት ረገድም የማይናቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የቀደሙ ተቋማት የተፈተኑባቸው መሰናክሎች በማህበሩ ውስጥ መታየት ጀመሩ፡፡ ችግሮቹ በአንድ ሌሊት የተፈጠሩ አይደሉም፡፡ ይልቁንም ረዘም ላሉ ጊዜያት ከፊል ገጽታቸው ሲታይ ቆይቶ አሁን ግዘፍ ነሥተው የተገለጡ ናቸው፡፡ በማህበሩ ውስጥ (በተለይም በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ውስጥ) በየጊዜው የነበሩት መኮራረፎች ለጊዜው በማንኛውም ተቋምና ሥራ ውስጥ የሚያጋጠሙ መደበኛ ክስተቶች ቢመስሉም ውለው ሲያድሩ ግን ጤናማ ያልሆኑ ፍላጎቶች የወለዷቸው መሆናቸው አልቀረም፡፡ እነዚህ ጤናማ ያልሆኑ ፍላጎቶች በበኩላቸው በማህበሩ ዓላማ እና የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ላይ በየጊዜው እንቅፋቶችን የሚያስቀምጥ ጤናማ ያልሆነ ቡድን ፈጠሩ፡፡ የዚህ ቡድን አባላት ልዩ ምልክታቸው በማህበሩ ውስጥ በነበራቸው ቆይታ እዚህ ግባ የሚባል ተግባር ያላከናወኑ ይልቁንም የሚሠሩትን እየተከታታሉ መተቸትና ማውገዝን ዋነኛ ተግባራቸው አድርገው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ መሆናቸው ነው፡፡ መነሻ ሐሳባቸው በማህበሩ ውስጥ የሚታዩ ችግሮች ይፈቱ የሚሉ ቢሆኑም ግባቸው ግን ችግሮቹ እንዲፈቱና ማህበሩ የተመሠረተበትን ዓላማ ማሳካት የሚችልበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ከመሥራት ይልቅ በእነዚህ ጥያቄዎች ሽፋን የራሳቸውን ግላዊና ቡድናዊ ፍላጎቶች ለማስፈጸም የሚደክሙ መሆናቸው ሌላው መገለጫቸው ነው፡፡ በማህበሩ ውስጥ ችግሮች መኖራቸውና መፈታት ያለባቸው መሆኑ እንዲሁም ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ከሆነ ተጠያቂ መሆን ያለበት አካል መኖር እንዳለበት የማይካድ ቢሆንም እነዚህ አካላት ግን የተቋሙ ችግር አሳስቧቸው በቅንነት የሚሠሩ ሳይሆኑ ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም ስንጥቅ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ይህ ስብስብ ተቋምን ከግለሰብ መለየት በተሳናቸውና በግለሰባዊ ጥላቻ በሰከሩ ሰዎች የታጨቀ ነው፡፡ ቡድኑ በዋናነት በማህበሩ ምክትል ሊቀ መንበር፣ ሒሳብ ሹም፣ የአደረጃት ዘርፍ ሃላፊ ፣ ምክትል አፈ ጉባኤ እና ተመሳሳይ አልያም ተቀራራቢ ፍላጎት ባላቸው የቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሰብሳቢዎች በነበሩ ግለሰቦች የሚመራ ሲሆን በዋናነት የሚነሱት ጥያቄዎች ማለትም፡- የፋይናንስ ግልጸኝነት ችግር እና የውጭ ግንኙነትን በተመለከተ ሲታይ የነበረው የመርሕ ጥሰት ጥቅምት 15/2015 ዓ.ም ወልድያ ከተማ በተደረገው የማህበሩ ዓመታዊ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በቀረበው የኦዲት ሪፖርት እና በዕለቱ ቀርቦ በጸደቀው የውጭ ግንኙነት መርሕና የኮሚኒኬሽን ስትራቴጂ ለመፍታት የተደረገውን ጥረት ወደ ጎን በመተው ከጉባኤው መልስም ችግሮች እንደተባባሱ አድርጎ ከማቅረብ በተጨማሪ በወቅቱ በኋላ ላይ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊው ለቡድኑ በሚመች መንገድ ያደረገው የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን ማጠናከርና ተሐድሶ ማድረግ እንዲሁም ለማዕከላዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እጩ የሚሆኑ ተማሪዎችን መለየት ከዚያም አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ በጉባኤው ተወስኖ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ግልጽና ተቋሙን ሊገነባ የሚችል ተሐድሶ(Reform) ከማድረግ ይልቅ በሥውር ከማደራጀት እንዲሁም ዓላማውን ለማስፈጸም ድብቅ ተልዕኮ ከመስጠት ባሻገር ሌሎች በመደበኛ ጉባኤው የተወሰኑ ቅድመ ሁኔታዎች ባልተሟሉበት ሁኔታ ኅዳር 25/2015 ዓ.ም በማህበሩ መተዳዳሪያ ደንብ በተቀመጠው መሠረት ስልጣን ባለው አካል ያልተጠራ ተቀባይነት የሌለው ‹‹ጠቅላላ ጉባኤ›› በመጥራት በወቅቱ የጠቅላላ ጉባኤው አባላት ያልሆኑና አንዳንዶቹ የየትኛው ቅርንጫፍ ተወካዮች እንደሆኑ በውል የማይታወቁ እንዲሁም በማህበሩ ሕጋዊ የእውቅና ሹመት ደብዳቤ ያልተሰጣቸው አካላትን በመሰብሰብ፤ ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ውስጥ ሊቀ መንበሩ፣ የጽ/ቤት ኃላፊው እና የሕ/ግንኙነት ኃላፊው ባልተገኙበት ሁኔታ አንዳንዶቹን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በማታለል ጉባኤው ላይ እንዲገኙ በማድረግ ‹‹ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና ሌሎች አመራሮችን አስመርጫለሁ›› በማለት የጉባኤው አባላት ላልሆኑ አካላት ጭምር የሹመት እደላ አከናውኗል፡፡ ከዚህ በኋላ ቡድኑ ማህበሩን ለመረከብ እንቅስቃሴ ከማድረጉ በተጨማሪ ‹‹የአማራ ትውልድ ተቋም›› የተሠኘ የቴሌግራም ግሩፕ በመክፈት ሐሰተኛና የጥላቻ መረጃዎችን ማሰራጨት የጀመረ ሲሆን ምናልባትም ችግሩን በንግግር ለመፍታት በመሥራችና የቀድሞ የማህበሩ ሥራ አስፈጻሚዎች አማካኝነት ታኅሣሥ 09/2015 ዓ.ም በባሕር ዳር ንግግር ቢደረግም አፈንጋጭ ቡድኑ ካለው ግትር ፍላጎት አንጻር መግባባት አልተቻለም፡፡ ነገር ግን ጥረቱን በመቀጠል ጎንደር ከተማ ተጨማሪ ውይይት ተደርጎ በጊዜያዊነት መደበኛ ሥራዎችን አቁመን መፍትሔው ላይ ብቻ ትኩረት እንድናደርግ ከሽማግሌዎች በቀረበው ሐሳብ ተስማምተን የነበረ ቢሆንም ቡድኑ ግን ብዙ ጊዜ ውስጥ ለውስጥ ሌላ ጊዜ በግልጽ እየተንቀሳቀሰ ቅርንጫፎች ላይ የጥላቻ ስብከት ከመስበክ ባሻገር ለብልጽግና ‹‹መንግሥት›› የሀሠት መረጃ በመስጠት ጠቁሞ ወንድሞቹን በማሳፈንና የማህበሩን ተቋማዊ ምስጢራትን ሳይቀር አሳልፎ በመስጠት እንዲሁም ከኢፌዴሪ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ጋር ጤናማ ያልሆኑ እና ኢመደበኛ ግንኙነቶችን በመፍጠር ደብዳቤዎችን በማጻፍ ለሁለተኛ ጊዜ ችግሩን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት አመከነ፡፡ ሂደቱም ምንም እንኳን ወደፊት ስለጉዳዩ ግልጽ ማብራሪያ ይሰጣሉ ብለን የምናስብ ቢሆንም በአሸማጋይነት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ መሥራችና የቀድሞ ሥራ አስፈጻሚዎችን ገለልተኝነት አልያም ቅንነትም ጭምር ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ሆኗል፡፡ ይህ ስብስብ በዋናነት ከሥርዓቱ ገዥዎች ጋር ኢመደበኛ ግንኙነት የሚያደርግና ከጥር 28/2015 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ቀናት በጎንደር 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ በእስር ላይ የቆየው የቀድሞ የማህበሩ አፈ ጉባኤ መኳንንት ሙላትን ጨምሮ የሐሰት መረጃዎችን በማቀነባበርና ስም በመስጠት ለሐሳቡና እና ለፍላጎቱ እንቅፋት ሆነውብኛል ያላቸውን የማህበሩ አካላት ማሳፈን መደበኛ ተግባሩ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ከማህበሩ ሕጋዊ ማኅተም ውጭ ማኅተም በማስቀረጽ ሕገ ወጥ የደብዳቤ ልውውጦችን እያደረገ ይገኛል፡፡ የቡድኑ ዋነኛ ድጋፍ ሰጪ ብልጽግና በመሆኑ ማህበሩን የማዳኑ ጉዳይ ከሥርዓቱ እጅ ፈልቅቆ የማውጣት ተግባር መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ በእኛ በኩል እስካሁን ድረስ ስለጉዳዩ ይፋዊ መግለጫ ከመስጠት የተቆጠብነው በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ እነርሱም፡- የመጀመሪያው አፈንግጠው የወጡት አባላት ምናልባትም ወደ ቀልባቸው ይመለሳሉ፤ በውይይትም ይፈታል በሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በአገዛዙ ምክንያት በመከራ ውስጥ ለሚኖረው የአማራ ሕዝብ ከችግሩ መውጣት የሚያስችል አንዳች ቁም ነገር በመሥራት ፋንታ ተጨማሪ የቤት ሥራና ተጨማሪ ሐዘን የሚያመጣ መግለጫ መስጠት ተገቢ አይደለም በሚል እሳቤ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በማህበሩ ስም በጥቅም የተደራጀው ቡድን ይህን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ራሱን ሕጋዊ አድርጎ ለማቅረብና ከጀርባ ካሉት በርካታ ተቋማት፣ ቡድኖችና ግለሰቦች ጋር በመተባባር ማህበሩን ለማፍረስ ካልሆነም ለራሱ ጥቅም ማስፈጸሚያ ለማድረግ በከፍተኛ ሁኔታ እየተንቃሰቀሰ በመሆኑ እውነታውን ለሕዝብ ይፋ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ይህንን መግለጫ አውጥተናል፡፡ በአጠቃላይ ከላይ እንደተገለጸው ማህበሩ ከሁላችንም በላይ በመሆኑና ከግለሰባዊ ፍላጎቶች ተላቆና ችግሮቹን ፈትቶ ይቀጥል ዘንድ ስለሚገባ ጠቅላላ ጉባኤ በመጥራት ሥራ አስፈጻሚ እና ሌሎች አመራሮችን በማስመረጥ የተሟላ ቁመና መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ በባሕር ዳር ከተማ ጥር 28/2015 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ ያካሄደ ሲሆን ጉባኤው በወቅታዊ የማህበሩ ተግዳሮቶችና መፍትሔዎቻቸው ላይ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ የሚከተሉትን አመራሮች በመምረጥ ተጠናቋል፡፡ እነርሱም፡- ሲሳይ መልካሙ- ሊቀመንበር በለጠ አቤ- ም/ሊቀመንበር አለባቸው ያስር- የጽ/ቤት ኃላፊ በላይሁን ኃ/ማርያም- ሒሳብ ሹም አብ አግማስ- የሕ/ግንኙነት ኃላፊ አብርሃም ፈንታ- የሕግ ጉዳዮች ኃላፊ እዘዝ ሞላ- የጥናትና ምርምር ዘርፍ ኃላፊ መታደል ጓዴ- የሴቶች ጉዳይ ኃላፊ ኤፍሬም ጎበዜ- የአባላት ጉዳይ ሃላፊ የአብሥራ ደስታ- የጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢ መለሰ ባበይ- ም/የጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢ ሀብታሙ አንለይ- ጸሐፊ አባትነህ ለወዬ- የኦዲትና ቁጥጥር ሰብሳቢ ይኼነው ታደሰ- ም/ሰብሳቢ አርጋው ታደለ- ጸሐፊ ታደለ ስመኝ- አባል ዮናስ ተሾመ- አባል ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ከሰሞኑ በሃይማኖት ተቋማት በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ እየተደረገ ያለው ከልኩ ያለፈ ጣልቃ ገብነት ኢ ሕገ መንግሥታዊ ብቻ ሳይሆን ‹‹መንግሥት›› የፖለቲካና የሲቪክ ማህበራትን ከማፍረስ አልፎ የሃይማኖት ተቋማትን ለመቆጣጠርና ለማፍረስ ቆርጦ የተነሳ ስለመሆኑ አይነተኛ ማሳያ ነው፡፡በተጨማሪም በድሬድዋ ዩኒቨርሲቲ ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምዕመናን ጾመ ነነዌን ጥቁር ልብስ በመልበስ፤በጾምና በጸሎት እንዲያሳልፉ የሰጠውን መመሪያ ተከትሎ መመሪያውን ለመፈጸም በሞከሩ ኦርቶዶክሳዊያን ተማሪዎች ላይ የሚደረገው አፈና፣ ድብደባ፤ ወከባና ያልተገባ ጫና በአስቸኳይ እንዲታረምና የሃይማኖት ነጻነታቸው እንዲከበርላቸው በአጽንኦት እናሳስባለን፡፡ በመጨረሻም እንቅስቃሴው በ‹‹መንግሥት›› ድጋፍ የሚደረግለትና ዓላማው ማህበሩን ማፍረስ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሮችን ለመፍታት እየሠራን መሆኑን እየገለጽን መላው የአማራ ሕዝብ ጉዳዩን ተገንዝቦ በማህበሩ ስም ከሚመጡ ሕገ ወጥ ግለሰቦችና ቡድኖች እንዲጠነቀቅ እና ማህበሩን ለመታደግ ለምናደርገው ርብርብ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ የካቲት ፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም “ውድ የአሻራ ሚዲያ ቤተሰቦች የአሻራ ሚዲያ ቻናልን ላይክና ሰብስክራይብ በማድረግ ድጋፋችሁን ታሳዩን ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።” ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች አሻራ ሚዲያ የአይበገሬዎቹ ልሳን:- // Youtube:- https://www.youtube.com/channel/UCPmgFzP2ZPmdGjHxXjigJaw // Facebook:- https://www.facebook.com/asharamedia24 // ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedia24
Source: Link to the Post