“ወደዚህ ችሎት ስመጣ ነፍሴ እየተጨነቀች ነው” አቶ ልደቱ አያሌው ለኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ከተናገሩት በጋዜጠኛ በላይ ማናዬ አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ… ጥቅምት 14 ቀን 20…

“ወደዚህ ችሎት ስመጣ ነፍሴ እየተጨነቀች ነው” አቶ ልደቱ አያሌው ለኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ከተናገሩት በጋዜጠኛ በላይ ማናዬ አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ… ጥቅምት 14 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ ዛሬ የአቶ ልደቱ አያሌውን የችሎት ውሎ በናዝሬት/አዳማ ኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤት ተገኝተን ለመከታተል ችለናል። አቶ ልደቱ ዛሬ አዲስ ክስ ተነብቦላቸዋል። ክሱም ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ ተንቀሳቅሰዋል የሚል ነው። ከሳሽ አቃቤ ሕግ በክሱ ላይ እንደጠቀሰው አቶ ልደቱን ለክስ ያበቋቸው ታኅሳስ 2012 እና ግንቦት 2012 ዓ/ም ለውጡ ከድጡ ወደ ማጡ የሚል እና የሽግግር መንግስት ምስረታ ሀሳብ ሰነድ፣ እንዲሁም ከመስከረም 30/2013 ጀምሮ የመንግስት ህጋዊነት ያበቃል በሚል በሚዲያዎች ያደረጓቸው ንግግሮች ናቸው። ከአራት ጠበቆቻቸው ጋር የቀረቡት ተከሳሹ፣ የችሎቱን ሂደት በአስተርጓሚ ተከታትለዋል። ክሱ በንባብ ከተሰማ በኋላ አቶ ልደቱ በጠበቆቻቸው በኩል የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያቸውን አቅርበዋል። በመቃወሚያቸውም ህገ መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው በተናገሩትና በፃፉት ጉዳይ ሊከሰሱ እንደማይገባ ተከራክረዋል። በተጨማሪም፣ አማራጭ ሀሳብ ማቅረብ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስራ ነው፣ ያደረግነውም ይኸንኑ ስለሆነ በወንጀል የሚያስጠይቀኝ አይደለም ብለዋል። አቃቤ ሕግ በበኩሉ፣ ክሱ ህገ መንግስቱን ለማፍረስ መንቀሳቀሳቸውን የሚያሳይ ስለሆነ ተገቢ ነው ሲል ምላሽ ሰጥቷል። አቶ ልደቱ ጉዳያቸውን በዋስ ወጥተው እንዲከታተሉ ጠይቀዋል። ለዚህም የተከሰሱበት ጉዳይ ዋስትና የማይከለክል ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ተከሳሹ ከፍተኛ የልብ ህመም ያለባቸው በመሆኑ ወጥተው ህክምና ማግኘት እንዲችሉ ዋስ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል። አቃቤ ህግ በበከሉ፣ አቶ ልደቱ በዋስ ቢወጡ ከሀገር ሊወጡና ቀጠሯቸውን አክብረው ላይቀርቡ ስለሚችሉ በሚል ጥያቄውን ተቃውሟል። ፍ/ቤቱ በመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ክርክሩ እና የዋስ መብት ጥያቄው ላይ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 20/2013 ቀጠሮ ሰጥቷል። አቶ ልደቱ ሀሳባቸውን ለችሎቱ ለመግለፅ ዕድል ሲሰጣቸው፣ “ወደዚህ ችሎት ስመጣ ነፍሴ እየተጨነቀች ነው። ከአያያዜ ጀምሮ ለህይወቴ አስጊ ሁኔታ ላይ ነው የቆየሁት። ህክምና ቀጠሮ እያለኝ ተከልክየ ነው ያለሁት። … ” አቶ ልደቱ ይህን መግለፅ ሲጀምሩ ችሎቱ አቋርጧቸዋል። ሀሳባቸው በዛሬ ክስ ላይ ብቻ እንዲሆንም ሲገልፅላቸው ተስተውሏል። አቶ ልደቱም፣ “በንግግሬ ችሎቱ የሚከፋ ከሆነ ልተወው እችላለሁ። ታስሬም ሀሳቤን ስገልፅ ችሎቱ ካላዳመጠኝ ሊቀር ይችላል” ማለታቸው ተከትሎ፣ ችሎቱ አጠር አድርገው ሀሳባቸው እንዲቀጥሉ ፈቅዷል። በዚህም ተከሳሹ፣ “የእኔ የጤና ሁኔታ የመኖርና ያለመኖር ደረጃ ላይ ነው። በሚቀጥለው ቀጠሮ እንኳ ስለመገኘቴ እርግጠኛ አልሆንም። የህጉ ዓላማ ማስተማር ከሆነ፣ ለመማርምኮ በህይወት መቆየት ይኖርብኛል” በማለት ያሉበትን ሁኔታ በመግለፅ በዋስ እንዲወጡ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል። አቃቤ ሕግ አቶ ልደቱ ወደ ወህኒ ቤት እንዲወርዱ እንዲታዘዝለት ጠይቋል። ተከሳሹ በበኩላቸው፣ ካለባቸው የጤና ችግር አንፃር ባሉበት ቦታ እንዲቆዩ ጠይቀዋል። ፍ/ቤቱም እስከሚቀጥለው ቀጠሮ ባሉበት የደብረ ዘይት/ቢሾፍቱ ፖሊስ መምሪያ እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply