‘ወደ ነገን ሂያጅ ነኝና’ የግጥም ስብስብ መፅሐፍ ተመረቀ

ዕረቡ ሰኔ 29 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በገጣሚ አስታውሰኝ ረጋሳ የተዘጋጀና ‘ወደ ነገን ሂያጅ ነኝና’ የተሰኘ የግጥም ስብስብ መፅሐፍ ዛሬ ሰኔ 27 ቀን 2014 በአገር ፍቅር ቴአትር ተመርቋል።

42 ግጥሞችን አካትቶ በ109 ገፆች የተዋቀረው መፅሐፉ፣ ተስፋን፣ ፍቅር እና አመስጋኝነትን ያነሳል።

በመፅሐፉ መግቢያ ላይ ሐሳባቸውን ያሰፈሩት ፍሬዘር ታሪኩ፤ <ገጣሚው በዚህ የግጥም ስብስቡ ውስጥ ዛሬ ምንም ሆነ ምን፤ ወደ ነገ ሂያጅ ነኝ ይለናል። ነገስ ምን አለ ብለን ብንጠይቀው ብርሃን፣ ተስፋ፣ ፍቅር እያለ ያወጋናል። እሱ ብቻ ነው ስንለው፤ አመስግን እያለ የተስፋ ዳናውን እየረገጠ ያዘግመዋል…> ብለዋል።

በምርቃት ሥነሥርዓቱ ላይም የፊልም ባለሞያ ቢንያም ወርቁ ከገጣሚው ጋር ያለውን ትውውቅና ወዳጅነት፤ እንዲሁም ስለገጣሚው አቅምና ችሎታ መስክሮ ሐሳቡን ለታዳሚው አጋርቷል። ተዋናይ ፍቃዱ ከበደ ወግ ሲያስደምጥ፤ ተዋናይ ሰለሞን ቦጋለ ከመፅሐፉ የተመረጠ ግጥም አቅርቧል።

በተጨማሪም ሰዓሊና ገጣሚ ቸርነት ወልደገብርኤል ኢትዮጵያ አሁን ስላለችበት ኹኔታ አውስቶ ስሜቱን ያጋራ ሲሆን፤ አገር የጋራ ቤት ነውና ኹሉም እያንዳንዱ ሰው፤ እየሆነ ያለውን የንፁሐን ዜጎች ሞትና መከራ በሚችለው አቅም በቃ ብሎ ሊያወግዝ እንደሚገባ አሳስቧል።

ቸርነትን ጨምሮም ገጣሚ ኤልያስ ሽታሁን፣ ተስፋሁን ከበደ (ፍራሽ አዳሽ) እንዲሁም አቢሲኒያ የተመረጡ የግጥም ሥራዎችን በመድረኩ አስደምጠዋል። ልዩ ዜማ ኳየር፣ ቃለአብ፣ ታምሩ ንጉሤ እና ሔለንም ጥዑም ዜማ አሰምተዋል።

እንዲሁም ፍሬዘር ታሪኩ የመፅሐፉ መዋቅር እና ይዘት ላይ ዕይታቸውን ሲያካፍሉ፤ ተዋናይ አማኑኤል የሺወንድ መድረኩን ግሩም አድርጎ አጋፍሯል።

ገጣሚ አስታውሰኝም በመድረኩ ላይ በሙዚቃ እንዲሁም በትወና የታጀበ የግጥም ሥራ አቅርቧል።

በመርሃ ግብሩ ማብቂያ ላይ ወላጅ እናቱን አስቀድሞ፤ በመቀጠልም በሥራው ለተሳተፉና በእለቱ በመድረኩ ለተገኙ ኹሉ ምስጋናውን አድርሷል።

‘ወደ ነገን ሂያጅ ነኝና’ የግጥም ስብስብ መፅሐፍ፤ ለገጣሚ አስታውሰኝ ረጋሳ ኹለተኛው የመፅሐፍ ሥራው ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ‘ተስፋ’ የተሰኘ የግጥም ስብስብ መፅሐፍ ለአንባብያን አድርሷል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply