ወጋገን ባንክ የአዲስ አበባ ፖሊስ ያዝኩት ያለውን የጦር መሳሪያው በህጋዊ መንገድ ለባንክ ጥበቃ ስራ የገዛው መሆኑን አስታወቀ።ከዛሬ ረፋድ ጀምሮ የተለያዩ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን በወጋ…

ወጋገን ባንክ የአዲስ አበባ ፖሊስ ያዝኩት ያለውን የጦር መሳሪያው በህጋዊ መንገድ ለባንክ ጥበቃ ስራ የገዛው መሆኑን አስታወቀ።

ከዛሬ ረፋድ ጀምሮ የተለያዩ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን በወጋገን ባንክ ተከዝኖ ተገኘ ተብሎ የተሰራጨው መረጃ ስህተት መሆኑን ወጋገን ባንክ ለኢትዮ ኤፍ ኤም አስታውቋል።

በ2011 ዓ.ም በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ፍቃድ አግኝተን የገዛነውን የጦር መሳሪያ ነው እየተጠቀምንበት ያለነው ሲሉ የወጋገን ባንክ ተጠባባቂ ፕሬዝደንት አቶ ክንዴ አበበ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል።

ከጋፋት ኢንደስትሪያል የተመረቱ 113 የጦር መሳሪያዎችን በሶስት ዙር ገዝተን ተረክበናል ብለዋል።

አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ለቅርንጫፎች ባንኮች ልናከፋፍል ስላልቻልን የጦር መሳሪያዎቹን በዋናው መስሪያ ቤት አስቀምጠናቸው በፍተሻ ወቅት ሲገኙ በጸጥታ አካላት እንደተወሰደባቸው አቶ ክንዴ አበበ ነግረውናል።

ባንኩ ጦር መሳሪያዎቹን ከሚመለከተው የመንግስት ተቋም ጋር ተነጋግረን ህጉን ተከትለን የገዛናቸው ናቸው ብሏል።

የጦር መሳሪያዎቹ በቅርብ ለተከፈቱትና አዲስ ለሚከፈቱ ቅርንጫፎቻችን ያዘጋጀናቸው ናቸው ሲሉም አክለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው እንግዲህ ዛሬ ጠዋት በመገናኛ ብዙሀን 73 የጦር መሳሪዎች ህገ ወጥ ናቸው መባሉን የሰማነው ያሉት አቶ ክንዴ መረጃውን ላወጣው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በደብዳቤ ጥያቄ አቅርበናል ብለዋል ነገር ግን መልስ ሊሰጠን አልቻለም ሲሉ ነግረውናል።

በመቅደላዊት ደረጀ
ሕዳር 4 ቀን 2013 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply