
ዋቻሞ ዩኒቨርስቲ ከሰሞኑ በግቢው የተፈጠረውን ግጭት በአግባቡ ባለመፍታቱ በደህንነት ስጋት በርካታ ተማሪዎች ከግቢ እየለቀቁ በመውጣት ላይ መሆናቸውን ገለጹ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ በደቡብ ክልል ሀድያ ዞን ዋቻሞ ዩኒቨርስቲ ከየካቲት 22/2015 በተወሰኑ ተማሪዎች መካከል ተፈጥሯል የተባለውን አለመግባባት እና ግጭትን ተከትሎ በርካታ ተማሪዎች መደብደባቸው እና መቁሰላቸው ተገልጧል። ተማሪዎቹ እንደሚሉት ከአድዋ ድል በዓል አከባበር ጋር በተያያዘ ያለፈው ዓመት ተመሳሳይ የሆነ ችግር ገጥሟቸው ነበር። የመነሻ ምክንያቱ ከውሃ ተራ ጋር የተያያዘ ይሁንጅ አላማው ሌላ ነው የሚሉት ተማሪዎች የአማራ ተማሪዎች ተለይተው እየተጠቁ በመሆኑ በርካቶች ተረጋግተው አልተፈተኑም፤ የደህንነት ዋስትና በማጣታቸውም ሾልከው እየወጡ መሆናቸው ተናግረዋል። በግቢው የተፈጠረውን ግጭት በአግባቡ ባለመፍታቱ በደህንነት ስጋት በርካታ ተማሪዎች አሁንም ከዋቻሞ ግቢ እየለቀቁ በመውጣት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። አክለውም በግቢው ውስጥ ተደጋጋሚ ተኩስ ይሰማል፤ የሚደርስባቸውን ጥቃት ፈርተው ብዙዎች ግቢውን ለቀው ወደ ጫካ እየገቡ ነው፤ ተማሪዎቹ የፌደራል ፖሊስ ወደ ግቢው የገባ ቢሆንም በቂ ጥበቃ እያደረገ አይደለም ብለዋል። የዋቻሞ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሀብታሙ እና የግቢው ሰላምና ደህንነት አቶ ተሾመ በግቢው ውስጥ ከቀናት በፊት በተወሰኑ ተማሪዎች ግጭት ተፈጥሮ የቆሰሉ ተማሪዎች እንዳሉ እና የህክምና ክትትልም እየተደረገ ስለመሆኑ ተናግረዋል። ከግቢው ውጭ ሾልከው እየገቡ በተማሪዎች ላይ በቡድን ሆነው ጉዳት ያደረሱ አካላት የሉም፤ ግቢውም በጸጥታ አካላት እየተጠበቀ ነው፤ በስጋት የወጣ ተማሪ የለም ሲሉም አስተባብለዋል። ይሁን እንጅ ሊመረቁ ወራት የቀራቸው ተማሪዎች ጭምር በደህንነት ዋስትና ማጣት ምክንያት ከግቢ ለመውጣት መገደዳቸውን አስታውቀው አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ ነው የጠየቁት።
Source: Link to the Post