“ውቅሮ ላይ እጅ ከሰጡ በኋላ ብሄር እየጠየቁ 3 አማራዎችን፣2 ኦሮሞዎችንና 1 ከደቡብ የኮንሶ ብሄረሰብ ተወላጅን ሲረሽኑ በአይኔ አይቻለሁ” የከሃዲው ሕወሓት ውቅሮ በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰ…

“ውቅሮ ላይ እጅ ከሰጡ በኋላ ብሄር እየጠየቁ 3 አማራዎችን፣2 ኦሮሞዎችንና 1 ከደቡብ የኮንሶ ብሄረሰብ ተወላጅን ሲረሽኑ በአይኔ አይቻለሁ” የከሃዲው ሕወሓት ውቅሮ በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ከፈፀመው ጥቃት የተረፈ አባል ምስክርነት! አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ… ህዳር 24 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ ከሃዲው ሕወሓት ውቅሮ በነበሩ በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ከፈፀመው ጥቃት የተረፈ አባል ምስክርነቱን ለአማራ ሚዲያ ማዕከል አጋርቷል። አባሉ በአሁኑ ሰዓት በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ እንደሚገኙ በመግለፅና ደማቅ አቀባበልና እንክብካቤ እያደረጉላቸው የሚገኙ የበየዳ፣ የደባርቅና የአካባቢውን ነዋሪዎችን አመስግኗል። “ያላሰብነው አጋጠመን!” ያለው ከሃዲው ሕወሓት ለግድያ ካሰማራው ገዳይ ቡድን ውቅሮ ላይ የተረፈው የመከላከያ ሰራዊቱ አባል መጀመሪያ ላይ ዋርድያውን በጥይት ገደሉና ምሽጉን ተቆጣጠሩ ይለናል። አባሉ ሲቀጥል ከጓዶቻችን ጋር እንዳንገናኝም ኔት ወርኩንና ራዳሩም ተዘጋ፤ ከመረጃ ውጭ አደረጉን። አገር ሰላም ብለን በተኛንበት ተኩስ ከፈቱብን፣እኛም ወዲያውኑ ልብሳችን በመልበስ ቦታ ቦታ ያዝን ራሳችን ለመከላከል ተኩስም ገጠምን። ከሌሊቱ 5:40 ጀምሮ እስከ ቀኑ 6 ሰዓት ድረስ ተኩሱ ቀጠለ፤የሚደርስ አካል አልነበረም፤ ሕወሓት ቦታዎችን ቀድሞ በሙሉ ተቆጣጥሮ ከበባ አድርጓል። እኛም ጥይት ስንጨርስ ያዙንና ለ15 ቀናት ያህል በውቅሮ ጨለማ ክፍል አንድ አንድ ዳቦና የተበላሸ ምግብ በመስጠት አሰሩን። ቁርስ ይሰጣሉ፤ ምሳ ይዘላሉ፤ እራት ይሰጣሉ (አንድ አንድ ዳቦ)! ለ15 ቀናት በውቅሮ አንድ ሆቴል ግራውንድ ውስጥ ነው ያሰሩን፤ 170 እንሆናለን። ከመካከላችን 11ዱ ሴቶች ናቸው። ከ15 ቀናት ቆይታ ኋላም ወደ ጫካ ወሰዱን። እስከ ህዳር 19 ቀን ድረስ እዛው አቆዩን። ትርፍ ቃል ተናገራችሁ ተብለው ተመርጠው የተረሸኑ አሉ፤ የቆሰሉትም አልታከሙም። በመቀጠል ሶስት ምርጫ ሰጡን። ልዩ ሀይል ሆናችሁ ከእኛ ጋር ታገሉ፣ ካልሆነም ከመከላከያ ወጥታችሁ በትግራይ በሰላም ነዋሪ መሆን፣ መሄድ አለብኝ የምትሉ ከሆነ ከመከላከያ ወጥታችሁ ወደ ቤተሰብ መሄድ የሚሉ አማራጮች አቀረቡልን። እኛ ለሀገር ነው እንጅ የወጣን ለአንድ ክልል አይደለም በማለታችን ሚሊተሪያችን አስወልቀው አቃጠሉብን። አንድ ለመከላከያ የወገነን ትግሬ ወዲያው ገደሉት፣አንድ ሌላ ትግራዊ የመከላከያ አባል ግን እነሱን ተቀላቅሎ እኛን ወጋ፤ ሁሉንም የመሳሪያ ዲፖ አሳያቸው። በመጀመሪያ የትግራይ ተወላጆችን እረፍት እያሉ በመውሰድ መሬት ይሰጧቸው ነበር። የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ከፍተኛ የመከላከያ አዛዦችም ዙረው ወግተውናል፤ አስወግተውናልም። ከዛም በሌሊት መጥተው ፌስታላችሁን አስቀምጡ፤ ልብስ አውልቁ አሉን፤ ቅያሬ ልብስ እንዳንይዝ አደረጉ። አብዛኞች በቁምጣና በፓንት ወጣን።ሜዳ ላይ አውጥተው በብርድ ሲያስመቱን አደሩ። ከሌሊቱ 4 ሰዓት እና 10 :30 ሰዓት ላይ በመኪና ጭነው ወደ ተከዜ የአማራና የትግራይ ድንበር ላይ አራገፉንና ተሻገሩ አሉን። ቁስለኛም ስላለ እና ውሀውም በመሙላቱ በከፍተኛ ችግር ተሻገርን፤ ከፊሎች ወደ ተከዜ ጀልባ ለማግኘት በሄዱበት ተኩስ ተከፈተባቸው፤ ይሙቱ አይሙቱ አናውቅም፤ ከእኛ ጋር ሲጓዙ ከነበሩት 8 ቁስለኞች መንገድ ላይ ሞተዋል። ሀሙስ ወጥተን ከ4 ቀናት ቆይታ በኋላ ሰሜን ጎንደር በየዳ ደረስን፤ከዛም ደባርቅ።አቀባበሉ ልዩ እና ፍፁም የማይረሳ ነበር ሲል አመስግኗል። ከፍተኛ አመራሮችን እና ሴቶችን በሙሉ ለይተው ወስደዋል፤ 850 ሴቶች አሉ በእዙ ውስጥ። ከእኛ ጋንታ ጡት ተቆርጠው የተገደሉ ሴቶች አሉ ተብሏል። ጥቃቱን የፈፀሙት የሕወሓት ሚሊሻ፣ ልዩ ሀይል፣ከማህበረሰቡም በርካታ ተባባሪ ነበር፣ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የመከላከያ አዛዦችም እንዲሁ ዋና ገዳይ አስገዳዮች እንደሆኑ ከሞት የተረፈው አባል ምስክርነቱን ሰጥቷል። ስለጉዳዩ ያነጋገርናቸው በሰሜን ጎንደር ዞን የአብን የአደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ የሆኑት አቶ ያለው ሙሉጌታ የተፈፀመው ጥቃት የሚያሳዝንና ልብ የሚነካ ሆኖ ነው ያገኘነው ብለዋል። ከጥቃቱ ከተረፉት የተወሰኑትን ማነጋገራቸውን የገለፁት አቶ ያለው የመታፈናቸው ዜና ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ ህዝባዊ ቁጣ መቀስቀሱን ተናግረዋል። ከሕወሓት የክህደት ጥቃት የተረፉት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደ በየዳ እየመጡ መሆኑን ከሰማንበት ጊዜ ጀምሮም የጃናሞራ ገጠር ቀበሌዎች በመውረድ እገዛ አድርገዋል። ከዛም በየዳ ድልይብዛ ደርሰው አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላም ወደ ደባርቅ አቅንተዋል፤ የደባርቅ ነዋሪዎች፣የተለያዩ አደረጃጀቶችም ሞቅ ያለ አቀባበል በማድረግ በደባርቅ ዩኒቨቨርስቲ ግቢ እንዲያርፉ አድርገዋል ያሉት አቶ ያለው የተረፉት አባላትም ደስተኛ ናቸው ብለዋል። በሰሜን ጎንደር የአብን ማስተባበሪያ ጽ/ቤትም ለጃናሞራ፣ለበየዳ፣ ለደባርቅና ለአካባቢው ህዝብ ለመከላከያ ሰራዊት አባላት ላደረገው የሞቀ አቀባበልና ክብር ላቅ ያለ ምስጋናችን ይድረስ ብለዋል። በቀጣይም ራስን ብሎም አካባቢን ነቅቶ መጠበቅ አስፈላጊ ነው ያሉት አቶ ያለው :አብን ያለምንም ልዩነት ከአማራ ወጣቶች ማህበር፣ከፋኖ፣ከፀጥታ መዋቅሩ፣ ከብልፅግና እና ሌሎች አደረጃጀቶች ጋር በመናበብ እየሰራ መቆየቱን፣እየሰራ መሆኑንና ለቀጣይም እንደሚቀጥልበት አስታውቀዋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply