You are currently viewing ዐቃቤ ህግ በተመስገን ደሳለኝ ላይ ሶስት ክሶች አቀረበ

ዐቃቤ ህግ በተመስገን ደሳለኝ ላይ ሶስት ክሶች አቀረበ

በተስፋለም ወልደየስ

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ “ወታደራዊ ሚስጥሮችን ላልተፈቀደለት ሰው ወይም ለህዝብ በመግለጽ”፣ “የሀሰት ወይም የሚያደናግር መረጃ በማሰራጨት” እንዲሁም “መገፋፋት እና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር” በመፈጸም ወንጀሎች ተከሰሰ። የፌደራል ዐቃቤ ህግ በተመስገን ላይ ያቀረበው የክስ ዝርዝር ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 22፤ 2014  በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተነብቧል። 

ዐቃቤ ህግ በጋዜጠኛው ላይ ክስ የመሰረተው በትላንትናው ዕለት ቢሆንም፤ የክስ መዝገብ በተከፈተበት የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የህግ መንግስት እና የሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት “ዳኛ የለም” በመባሉ ጉዳዩ ለዛሬ ጠዋት ተቀጥሮ ነበር። ዛሬ ረፋዱን በተሰየመው ችሎት፤ በ“ፍትሕ” መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ላይ የቀረበው ክስ በንባብ የተሰማ ሲሆን፤ በጋዜጠኛው ጠበቃ በኩል የተነሳው የዋስትና ጥያቄም ተደምጦበታል።

በጋዜጠኛ ተመስገን ላይ የቀረበው የመጀመሪያው ክስ በኢፌዲሪ የወንጀል ህግ “ወታደራዊ ምስጢርን መግለጽ” በተመለከተ የተደነገገውን አንቀጽ ተላልፏል በሚል የቀረበ ነው። በተከሳሹ ላይ የተጠቀሰበት የወንጀል ህጉ አንቀጽ “ማንኛውም ሰው በጠቅላላው በሕዝብ ዘንድ ያልታወቁትንና በጠባያቸው ከፍተኛ ቁም ነገር በመያዛቸው ምክንያት ላልተፈቀደለት ሰው ወይም ለሕዝብ እንዳይገለጹ በምስጢር የሚጠበቁትን ወታደራዊ ምስጢርነት ያላቸውን ማናቸውንም ዓይነት ሰነዶች ወይም መረጃዎች ላልተፈቀደለት ሰው ወይም ለህዝብ መግለጽ ወይም ማስተላለፍ” ይከለክላል። 

ተመስገን ደሳለኝ ይህን የወንጀል ህግ አንቀጽ በመተላለፍ፤ “በሀገሪቱ ከፍተኛ የፖለቲካ እና የጦር አመራሮች መሀል የተደረገ ሚስጥራዊ ውይይት እና የሃገሪቱን የጦር ኃይል መሳሪያ አቅም ለህዝብ እና ላልተገቡ አካላት እንዲገለጽ በማድረግ” ወንጀል መከሰሱን ዐቃቤ ህግ በክስ ቻርጁ ላይ አስፍሯል። ከሳሽ ዐቃቤ ህግ ለዚህ ውንጀላው በማስረጃነት ያቀረበው፤ ተመስገን በስራ አስኪያጅነት ይመራዋል ባለው በልህቀት ኮሚኒኬሽን ብሮድካስት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስር በሚታተመው “ፍትሕ” መጽሔት ላይ የወጡ አራት ጽሁፎችን ነው። 

ከአራቱ ጽሁፎች መካከል በ“ፍትሕ” መጽሔት ባለፈው የካቲት 2014 ታትሞ የወጣው የብርጋዴየር ጄነራል ተፈራ ማሞ ቃለ ምልልስ ይገኝበታል። “የጄነራሉ ሚስጥሮች” በሚል ርዕስ ስር በመጽሔቱ በተስተናገደው በዚህ ቃል ምልልስ፤ ተመስገን “ጄነራሉ የነገሩትን ወታደራዊ ሚስጥሮች ለህዝብ ለማሳወቅ በማሰብ”፤ “በሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ህወሓት መካከል ስለነበረው ውጊያ፤ ወታደራዊ አመራሮች የተለዋወጡትን ሚስጥራዊ ንግግሮች እና ግምገማዎች በእትሙ ላይ እንዲገለጽ አድርጓል” በሚል ዐቃቤ ህግ ከስሷል።

በጋዜጠኛ ተመስገን የመጀመሪያ ክስ ላይ በማስረጃነት ከተጠቀሱ ጽሁፎች ውስጥ ሁለቱ፤ ከሶስት ዓመት በፊት በ2011 በ “ፍትሕ” መጽሔት ላይ ለንባብ የበቁ ናቸው። ተመስገን “ሪፎርም ወይስ ፈረቃ” በሚል ርዕስ ስር በመጋቢት 2011 በታተመ ጽሁፍ፤ “ለማንም ሊገለጽ የማይገባ ሀገራዊ ወታደራዊ ቁመና ከሌሎች ሀገራት ወታደራዊ አቋም ጋር በማነጻጸር ለህዝብ ገልጿል” በሚል ተወንጅሏል። 

ሌላው በ2011 የታተመ ጽሁፍ እና በተከሳሹ ላይ በማስረጃነት የቀረበው ጽሁፍ “ወታደራዊ አመፅ ያሰጋል” በሚል ርዕስ ስር የወጣ መሆኑ ተጠቅሷል። “ሰነዱ ከመከላከያ የተገኘው እንኳን ቢሆን ሃገራዊ ሚስጥር በመሆኑ ለማንም ሊገለጽ የማይገባ በመሆኑ በሚስጥር መያዝ ሲገባው ከመከላከያ የተገኘ ሰነድ በማለት ወታደራዊ ቁመና ግምገማ እና ሪፖርት የሚያሳይ ሰነድ 19 ገጽ በማለት ይዘቶቹን በመቀነጫጨብ አሳማኝ ሆኖ እንዲገኝ ለማድረግ የሃገር መከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹም ጽህፈት ቤት የሚል ማህተም ተመቶበታል ብሎ በመጻፍ በእትሙ ገልጿል” በሚል ዐቃቤ ህግ በክስ ቻርጁ ላይ አትቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

The post ዐቃቤ ህግ በተመስገን ደሳለኝ ላይ ሶስት ክሶች አቀረበ appeared first on Ethiopia Insider.

Source: Link to the Post

Leave a Reply