ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ድርጅት ከሳኡዲ በተመለሱ የትግራይ ተወላጆች ላይ እስራትና በደል እየደረሰ ነው አለ

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ድርጅት /ሂዩማን ራይትስ ዋች/ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በቅርቡ ከሳኡዲ አረብያ ወደ ኢትዮጵያ የተባረሩትን በሺህዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆችን ከህግ ውጭ በማሰርና በኃይል እንዲሰወሩ በማድረግ እንግልትና በደል ያደርሱባቸዋል ሲል ባወጣው ሪፖርት አስታወቀ፡፡ 

ድርጅቱ ሳኡዲ አረብያ የትግራይ ተወላጅ ስደተኞችን የምትይዝበት አሰቃቂ ሁኔታና በግዳጅ ወደ ኢትዮጵያ መመለሷን እንድታቆም ጠይቋል፡፡ 

ይልቁንም ስደተኞቹ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) ስር ሆነው ድጋፍ እንዲደርግላቸው አሳስቧል፡፡

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በተለያዩ ጊዜ ከሳኡዲ አረብያ የሚመጡትን የትግራይ ተወላጆች እየተቀበለ አዲስ አበባ ውስጥ ወደሚገኙ ማስተናገጃዎችና አንዳንዶቹም በህገ ወጥ መንገድ ወደሚታሰሩባቸው ስፍራዎች እንደሚወስዷቸው አመልክቷል፡፡ 

ወደ ትግራይ የሚጓዙትንም በየኬላ ጣቢያዎቹ በመያዝ የሚያስራቸው ሲሆን በአፋር ከሚገኘው የሰመራ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል የሚገቡትንም አፋር ውስጥ ወይም ደቡብ ኢትዮጵያ ወደ ሚገኙ እስርቤቶች እንደሚልካቸው አመልክቷል፡፡

ድርጅቱ ለተለያዩ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቋማት ስለሁኔታው ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም ምላሽ አለማግኘቱን አስታውቋል፡፡ 

የአሜሪካ ድምጽም እንዲሁ ዓለም አቀፍ ድርጅቱ ስላቀረበው ሪፖርት ከኢትዮጵያ ባለሥልጣና ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply