You are currently viewing #ዘር_ተኮር_ጭፍጨፋው_ወቅቱንም_መልኩንም_እየቀያየረ_ቀጥሏል_የመንግስትም_ቸልተኝነት_እንዲሁ!  በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ዘርና ሃይማኖት ለይቶ…

#ዘር_ተኮር_ጭፍጨፋው_ወቅቱንም_መልኩንም_እየቀያየረ_ቀጥሏል_የመንግስትም_ቸልተኝነት_እንዲሁ! በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ዘርና ሃይማኖት ለይቶ…

#ዘር_ተኮር_ጭፍጨፋው_ወቅቱንም_መልኩንም_እየቀያየረ_ቀጥሏል_የመንግስትም_ቸልተኝነት_እንዲሁ! በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ዘርና ሃይማኖት ለይቶ ዘርፍጅት እየተካሄደ ነው፤ ተገቢ ትኩርት ካልተሰጠው በስተቀር ነገ በእያንዳንዳችን ቤት የሚያንኳኳ ከባድ አደጋ አንዣቧል በሚል ዓለምአቀፍ ብያኔዎችን ጠቅሰን በመረጃና ማስረጃ አቅርበናል፡፡ ከሀገር ውስጥ ተቋማት እስከ ቆንስላዎችና UN የመሰሉ ዓለምአቀፍ ድርጅቶችና መገናኛ ብዙኃን በመግለጫም በአካልም በመገኘት ጉዳዩን አስረድተናል፤ በክብር ቀብር ላልተፈጸመላቸውና መንግስት ቸል ላላቸው የሕሊና ጸሎትና ጥቁር በመልበስ ሀዘናችንን እስከመግለጽ ደርሰናል፡፡ ሆኖም መንግስትም፣ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችም፣ ቆንስላዎችም፣ ሌሎቹም ጆሮ ዳባ ልበስ እንዳሉ ናቸው፡፡ ይባስ ብሎ በ…ተለይ መንግስት ተኮር መገናኛ ብዙኃንና የመንግስት መዋቅሩ በተናበበ አኳኋን በሚመስል መልኩ ጭፍጨፋው በቂ ትኩረት እንዳያገኝ ከፍተኛ የመሸፋፈን ሥራ ሲከውኑ አስተውለናል፡፡ እርግጥ ነው ዓለም ላይ ከደረሱ የዘር ፍጅት ክስተቶች በውል የምንረዳው ነገር ኹሉም በሚባል መልኩ መንግስታዊ ድጋፍ ያላቸው ነበሩ፡፡ በዚያው ልክ መንግስት ተኮር መገናኛ ብዙኃንም የድርጊቱ ዋና ተባባሪዎችና አራጋቢዎችም ነበሩ፡፡ ብዙዎቹ በቀጥታ ደግፈው ሠርተዋል፤ ጥቂቶች ደግሞ ባላየ በማለፍና በማለባበስ ተባብረዋል፡፡ ፓርቲያችን በዚህ ጊዜ አራጁም፣ ታራጁም፣ ቢላ አቀባዩም፣ የሞት አውድማውም በውል በሚታወቅበት ኹኔታ መንግስት የበለጠ መንቃትና መፍትሔ መፈለግ ሲገባው በጉዳዩ ላይ እያሳየ ያለው የበዛ ቸልተኝነት እጅጉን ያሳስበዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን በአሙሩ፣ ሆሮ ቡልቅ እና ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳዎች የኦነግ ሸኔ የሽብር ቡድን መስከረም 12 ቀን 2015 ዓ.ም በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ማንነት ያላቸውን ንጹሓን በአሰቃቂ ሁኔታ ቤት ለቤት በጠቋሚ ጭምር እየተዟዟረ ጨፍጭፏል። የሃይማኖት አባቶች በአሰቃቂ ኹኔታ ተገድለዋል፡፡ ክስተቱ ከነሐሴ 27 ቀን 2014 ዓ.ም የጀመረና ከእስከዛሬዎቹ ለየት ባለ መልኩ መበቃቀል ጭምር ያለበት እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ “የተለያዩ ቡድኖች” ባለቸው ኃይሎች በዚያው በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን የኦሮሞ ማንነት ያላቸው ዜጎቻችን ላይ የደረሰው ሞትም ሆነ በተከታታይ ጊዜያት ኦነግ ሸኔ በተባለው ቡድን የአማራ ማንነት ባላቸው ዜጎቻችን ላይ እየደረሱ ያሉ መጠነ ሰፊ እና ተከታታይ ግድያዎች መሠረታዊ ምክንያት የክልሉ እና የፌዴራል መንግሥት ዜጎችን ከጥቃት በመጠበቅ ረገድ መንግሥታዊ ሓላፊነታቸውን በአግባቡ አለመወጣት መሆኑን ፓርቲያችን በጽኑ ያምናል፡፡ በተዋረድ ያሉ የመንግሥት የጸጥታ አካላት ይህንን ሓላፊነታቸውን ባልተወጡ መጠን ዜጎች ፍትሕን የማስፈን ሥራን በእጃቸው በመውሰድ እና በበቀል እርምጃ በመሰማራት ችግሩ ተባብሶ አገር ወደ ከፋ ነገር ላለመግባቷ ምንም መተማመኛ የለም፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ባደረግነው ማጣራት ከተጠቀሰው ቀን ጀምሮ የጸጥታ ኃይሉ በሦስቱም ወረዳዎች የነበረና ፊት ለፊት ተኩስ እስከመክፈት የደረሰ እንደነበር መረዳት ችለናል፡፡ ከልብ ካዘኑ… እንዲሉ ነሐሴ 27 በነበረው ክስተት 4 የሚደርሱ የጸጥታ ኃይሎች የቻሉትን በማድረግ ሕዝቡን ከከፋ ጉዳት መታደግ ችለዋል፡፡ ፓርቲያችን እንዲህ ላሉ ለሕዝብና ሙያቸው የታመኑ ጀግኖች እውቅናና ክብር አለው፡፡ በአንጻሩ ከዚያ በኋላ ባሉ ኩነቶች የጸጥታ ኃይሎች ፊት ለፊት የመጣን አደጋ እያዩ በቂ ዝግጅት እንዲደረግ አልተደረገም፣ ያለውም ወደአጎራባች ወረዳዎች ትቶ ሸሽቷል፤ የሆነው ኹሉም ሆኗል፡፡ በዚህ መሐል ሕዝቡ የመጣውን አደጋ ያውቅ ነበርና የድረሱልን ጩኸቱ እስከ መሀል ሀገር ተሰምቶም ነበር፤ በበቂ ግን መልስ መስጠት አልተቻለም፡፡ ከሆሮ ጉድሩ አሳዛኝ ክስተት ጎን ለጎን የተቀናጀ በሚመስል መልኩ መስከረም 20 ቀን 2015 ዓ.ም መተሐራ ከተማ 12 የሚደርሱ የአማራ ማንነት ያላቸው ዜጎቻችንን ከመኪና በማስወረድ በአሰቃቂ ኹኔታ ገድለዋቸዋል፡፡ ፓርቲያችን በነዚህ ክስተቶች የተሰማውን ሀዘን እየገለጸና ይህን አሳፋሪ የዘር ፍጅት በጽኑ እያወገዘ ቀጣዮቹን ምክረ ሀሳቦች ለመጠቆም ይወዳል፡፡ መንግስት ኦነግ ሸኔ የተባለው የጥፋት ቡድን ከሕወሓት እኩል ጠላት እንደሆነ አውቆና ከበዛ ቸልተኝነቱ ነቅቶ ለሕዝቡ በቂ ትኩረትና መከላከል እንዲያደርግ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የሕዝብን ደህንነት መጠበቅ ተቀዳሚ ሚናውና ዜጎችን በእኩል መመልከት መንግስታዊ ተፈጥሮ መሆኑን ተገንዝቦ ከከፋፋይ ድርጊቱ እንዲቆጠብ፤ ውስጡን በአግባቡ በመፈተሽ በኹለት ቢላ የሚበሉ ካሉ ራሱን በማጽዳት ከሽብር ቡድኑ ቀጥታም ሆነ ተዘዋዋሪ ተባባሪነት ነፃ በማድረግ የዜጎችን ደህንነት እንዲያስጠብቅ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ በተለይ መንግስት ተኮር መገናኛ ብዙኃን ሓላፊዎችና ሠራተኞች ጉዳዩ በቂ ትኩረት እንዳይሰጠው ዘገባ በመንፈግ አለፍ ሲልም በመሸፋፈን ላደረገችሁት አስተዋጽዖ ከሕግና ታሪክ ተጠያቂነት እንደማታመልጡ ተገንዝባችሁ ሙያዊና ሞራላዊ ግዴታችሁን እንድትወጡ በጽኑ እናሳስባለን፡፡ መላው ኢትዮጵያውን በአካባቢው በከበባ ውስጥ ያሉ እና ተፈናቅለው ሻምቡ ከተማ ለሚገኙ በሺዎች ለሚቆጠሩ ወገኖች ድምጽ እንድትሆኗቸውና የዕለት ስንቅም በማቀበል እንድትረባረቡ እንጠይቃለን፡፡ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ወደየአካባቢዎቹ ጭምር በመዝለቅ ችግሮች ሰፍተው ወደእርስ በእርስ መተላለቅ እንዳይቀየሩ አባታዊ ሚናችሁን ትወጡ ዘንድ በትህትና እንጠይቃለን፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና ተቋማት ኢትዮጵያ ነገ ሌላ ሩዋንዳ ሳትሆን በጉዳዩ ላይ ገንቢ ሚናችሁን እንድትወጡ፣ እጃቸው ያለበት መንግስታዊ ሓላፊዎች፣ የጥፋት ቡድኖችና መገናኛ ብዙኃን በሕግ እንዲጠየቁ ቀና ትብበራችሁን ታደርጉ ዘንድ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ በመጨረሻም ፓርቲያችን ሀገር የጣለችባቸውን ግዴታ ሲወጡ ለሰው የጸጥታ ኃይሎችና የፍጅቱ ሰለባ ለሆኑ ወገኖቻችን እረፍተ ነፍስን፣ ለቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ደግሞ መጽናናትን ይመኛል። ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ እናት ፓርቲ መስከረም ፳፮ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

Source: Link to the Post

Leave a Reply