ዛሬ ታህሳስ ሶስት ነው ፡፡ እነሆ ታሪክ አሻራ ሚዲያ ታህሳስ 03/2013 ዓ.ም ባህር ዳር ‹‹ ሠላሣ ሦስት ዓመት የበላንበቱ የጠጣንበቱ… የታኅሣሥ…

ዛሬ ታህሳስ ሶስት ነው ፡፡ እነሆ ታሪክ አሻራ ሚዲያ ታህሳስ 03/2013 ዓ.ም ባህር ዳር ‹‹ ሠላሣ ሦስት ዓመት የበላንበቱ የጠጣንበቱ… የታኅሣሥ ባታ ለት ተፈታ ወይ ቤቱ›› ዓለም ለጥቁሮች ፊቷን ያዞረች ትመስል ነበር፡፡ ጥቁር ቆዳ ያለው የሰው ዘር በሙሉ እንደ ዕቃ እየተሸጠና እየተለወጠ ከርዕስቱና ከጉልቱ እየተፈናቀለ ይኖራል፡፡ ነጮች የጥቁሮች ፈጣሪ እስኪመስሉ ድረስ ዓለም የእኛ ብቻ ናት ብለዋል፡፡ የጥቁር መገኛዋ አፍሪካ እንደቅርጫ ስጋ ተከፋፍላ በቀኝ ግዢዎች ማቅ ውስጥ ገብታለች፡፡ በዚችው አህጉር በምሥራቅ ንፍቅ የምትገኝ አንዲት ሀገር ዳሯን እሳት አድርጋ ጠላቶቿን እየገረፈች ትመልስ ነበር፡፡ የጥቁር ዘር ሁሉ በምድር ላይ አንድ ተስፋ ብቻ ይጠባበቃል፡፡ ከወደ ምሥራቅ፤ ‹‹በምሥረቅ ፀሐይ ወጣ›› እንዳለ በምሥራቅ የምትወጣዋን ፀሐይ በጨለማ ውስጥ ሆነው ይጠብቋት ነበር፡፡ የጥቁሮቹ የጨለማ ዘመን እንዲያልቅ፣ ኃያልነታቸው በዓለም እንዲደምቅ፣ የነጭ አቢዮት እንዲወድቅ ያደረገ ተስፋ በተጣለባት ምድር አንድ ንጉሥ ነገሠ፡፡ ጥቁሮቹ ይመኩበታል፣ ነጩቹ ይፈሩታል፣ ጠላቶቹ ስሙን ሲሰሙ ይሸበራሉ፣ ኃያላኑ ከእግሩ ሥር ያጎነብሳሉ፣ ኢትዮጵያዊያን እንደ አባት ሳይሆን እንደ እናት አምዬ ይሉታል፡፡ በእናት ሀገራቸው እንደ እናት አኑሯቸዋልና፡፡ እብሪት የወጠረው የሮም ሰራዊት በአፍሪካ ምድር በብቸኝነት የቀረችውን ታላቋን ኢትዮጵያን ቀኝ ለመግዛት ከሮም ተነሳ፡፡ ‹‹ ኢትዮጵያ ቅርብ ሮም ሩቅ›› በማለት ጉዞ ጀመረ፡፡ ባሕርና የብሱን አቆራርጦ ጠላት የራደባትን፣ ጀግና የሚፈጠርባትን፣ ከቀደሙት የቀደመችውን የኢትዮጵያን ምድር ረገጠ፡፡ ብረኃን ዘ ኢትዮጵያ ንግሥትና እመቤት እቴጌ ጣይቱ እንደ አራስ ነበር ሆነች፡፡ አባ ዳኛው ምኒልክ ተቆጣ፡፡ ‹‹ ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት›› በማለት በማርያም ምሎ የሀገሩን ሕዝብ ጠራ፡፡ ‹‹ ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ነብር ዥንጉርጉርነቱን መቀዬር ይቻለዋልን?›› እንዳለ መጻሕፍ በኢትዮጵያዊነት ወደኃላ የለምና፣ የሀገሩ ሕዝብ የቻለ በጦርነት፣ ያልቻለ በፀሎት ለዘመቻ ተነሳ፡፡ ጉዞ ወደ አድዋ፡፡ ‹‹ እንኳን ለኢትዮጵያ ለእናት ሀገራችን፣ ለጎረቤት ስንል ይፈሳል ደማችን›› የሚለው ሩቅ አሳቢው የኢትዮጵያ አርበኛ የሮምን ሠራዊት አቧራ ሊያለብስ፣ ከድንበር ሊመልስ ገሰገሰ፡፡ ‹‹ምን ቢቃጠሩ ደረሰ ቀኑ›› ነውና የውጊያው ጊዜ ደረሰ፡፡ ጀግና በየጎራው ተሰለፈ፡፡ ወንድነት ተፈተነ፡፡ የኢትዮጵያዊያን አንድነት እንደ እሳት ይጋረፍ ጀመር፡፡ የራቀ በጠመንጃ የቀረበ በሳንጃ ተዋጋ፡፡ በሮም አደባባይ ለታላቅ ክብር ታጭቶ የተላከው የጣልያንን ወታደር የኢትዮጵያ አርበኞች እንዳልነበር አደረጉት፡፡ ‹‹ የአርበኛው ትንፋሽ መጣ ዘለቀ፣ በሰላ ብረት እየሰበቀ፣ ግንባር ግንባሩን እያወለቀ፣ ሲዞር ጀርባውን እያደቀቀ ተመልክት ብሎ የላከው ጥይት ቁም ነገር ሰሪ እንደደረሰ ሽንጡን ተርታሪ፤ ለዝና ብሎ ለመሞናደል ተመልከት ብሎ ግንባሩን መንደል›› የጥቁሮች የተስፋ ምድር ድል አደረገች፡፡ የጥቁሮቹ ጀንበር ፈነጠቀች፡፡ በአድዋ ተራራ ላይ ከፍ ብላ ወጣች፡፡ ጀንበር በሮም አደባባይ ያለ ሰዓት ጠለቀች፡፡ ዳግመኛም አልተመለሰች፡፡ ጥቁር እንደለበሰች ቀረች፡፡ ጣልያን አንገቷን ደፋች፤ ኢትዮጵያ አንገቷን አቀናች፤ የመጨረሻዋ የጥቁር ሕዝብ ተስፋ ከቃሏ ሳታጎድል ተስፋውን እውን አደረገችው፡፡ ከአድዋ ድል በኃላ ያለውን ሁነት አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ዳግማዊ አጤ ሚኒልክ በሚለው መጻሕፋቸው ‹‹ ከአድዋ ጦርነት ወዲህ የኢትዮጵያ ሥም ፀሐይ ባየው ሁሉ አገር ታወቀ፡፡ ከዚያ በፊት ኢትዮጵያ ምንም ከጥንት ከመሠረት ጀምራ ራሷን ችላ ብትኖር ከቶውንም በነፈርዖን ጊዜ ተባሕር ወዲያ እስከ ምስር ባንድ ወገንም አደን (ኤደን) ከአረብ አገር ተሻግራ ብትገዛ በአውሮፓ ስሟ የአሕዛብ አገራት ናት ትባል ነበር፡፡ በዳግማዊ ሚኒልክ እውነተኛው ስሟ ተገለጠ፡፡ ከእውነተኛ ማዕረጓ ገባች፡፡ የኢትዮጵያ ዓለም ከአድዋ ጦርነት ወዲህ ተጀመረ፡፡ እቴጌ ጣይቱ ‹ትንቢት ይቀድም ለነገር› ነውና የርጉፋን መከማቻ የነበረውን ገጠር አዲስ አበባ ብለው ስሙን ቀደሱት፡፡ እውነትም ከዚያ ወዲህ ኢትዮጵያ አበበች፡፡ የዚህን አበባ ፍሬውን የኢትዮጵያ ሰው በደስታ ለመብላት ያብቃው፡፡ ›› ዘመን ዘመንን እየተካ ሄዶ ኃያሉ ንጉሥ አያሌ ሥራዎችን ሠርቶ የፍጻሜው ዘመን ደረሰ፡፡ ወደ ማይቀረው ዓለም መሄድ አይቀርምና የአድዋው ጀግና ትንፋሽ ጠፋች፡፡ ሕዘቡ ተጨነቀ፡፡ እንጦጦ በሐዘን ተዋጠች፡፡ አዲስ አበባ ሳግ ተናነቃት፡፡ ጥቁሮች መመኪያቸውን ሊያጡ ነውና ወዮዎልን ወዮታ አለብን አሉ፡፡ እምዬ አባታችን እያሉ አለቀሱ፡፡ እምዬ በሚያልፈው ዘመን የማያልፍ ሥራ ሠርቶ የድካሟን ዓለም ተሰናበታት፡፡ የሞት መላዕክ ወሰደው፡፡ ተክለፃዲቅ መኩሪያ ዓፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት በሚለው መጻሕፋቸው ‹‹ ገናናው ንጉሠ ነገሥት በ1900 ዓ.ም የዠመራቸው በሽታ እየፀና ሄዶ በመጨረሻ ሰውነታቸው ዝሎ ፣ አንደበታቸው ተዘግቶ፣ እንደቆዬ በታኅሣሥ 3 ቀን በ1906 ዓ.ም ከዚሕ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ የሸዋ ንጉሥ በኋላም የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት በነበሩበት ዘመን ሁሉ ክፉውን በክፉ ሳይሆን ክፉውን በደግነት እየመለሱ፣ ጥፋትን ሁሉ በትግሥት እያሸነፉ፣አገር የሚሰፋበትን ልማት የሚዳብርበትን ዕረፍትና ሰላም የሚገኝበትን ከማሰብና ከመፈፀም አልተቆጠቡም፡፡ የአውሮፓን ኃያል መንግሥት በጦር ሜዳ በማሸነፍ ኢትዮጵያን በዓለም እንድትደነቅ አድርገዋል፡፡›› በእምዬ ሞት ጊዜ ብርኃን ዘ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ ‹‹ ነጋሪት ማሰማት እምቢልታ ማስነፋት ነበረ ሥራችን፣ ሰው መሆን አይቀርም ደረሰ ተራችን ›› በማለት ሙሾ አወረደች፡፡ የዛኔዋ ልዕልት የኋለኛዋ ንግሥት የንጉሡ ልጅ ዘውዲቱ ደግሞ ‹‹ እጅግ አዝኛለሁ አላቅሽኝ አገሬ፣ የሁሉ አባት ሞቶ ተጎዳችሁ ዛሬ፤ ድርቅ ሆናል አሉ ዘንድሮ አገራችሁ፣ ዝናሙ ሲጠፋ ምነው ዝም አላችሁ፤ ሠላሣ ሦስት ዓመት የበላንበቱ የጠጣንበቱ፣ የታኅሣሥ ባታ ለት ተፈታ ወይ ቤቱ›› በማለት ሙሾ አውርዳለች፡፡ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ገናናው ንጉሥ ዳግማዊ ምኒልክ በአንድ ወቅት ያስተላለፉትን መልዕክት እንዲህ ብለው አስቀርተውታል፡፡ ‹‹ ልጆቼ ወዳጆቼ አንዱ በአንዱ ምቀኝነት ይቅር ያንዱን አገር አንዱ እኔ እደርበዋለሁ እንዳትባባሉ፣ እኔ እስካሁን በፍቅር እንዳኖርኋችሁ እንናተም ተስማማታችሁ በፍቅር እንድትኖሩ እለምናችኋለሁ፡፡ እንናተ አንድ ልብ ከሆናችሁ፣ በምቀኝነት እርስ በእርሳችሁ ተዋግታችሁ ካላለቃችሁ በቀር አገራችን ኢትዮጵያን ለሌላ ለበዓድ አትሰጧትም፡፡ ክፉም ነገር አገራችን አያገኛትም፡፡ ነፋስ እንዳይገባባችሁ አገራችሁን በያላችሁበት በርትታችሁ ጠብቁ፤ ወንድሜ ወንድሜ እየተባባለችሁ ተደጋጋፉ፤ የኢትዮጵያን ጠላት ተጋግዛችኁ ተደንበር መልሱ፡፡ የኢትዮጵያ ጠላት በአንዱ ወገን ትቶ ባንድ ወገን ቢሄድና ደንበር ቢገፋ በእኔ ወገን ታልመጣ ምን ቸገረኝ ብላችሁ ዝም አትበሉ፡፡ ያ ጠላት በመጣበት በኩል ሁላችሁም ሄዳችሁ ጠላታችሁን መልሱ፡፡ እስከየ ቤታችሁ እስቲመጣ ዝም ብላችሁ አትቆዩ፡፡ ይህንን ምክር ለእናንተ መስጠቴ እኔማ በእግዚአብሔር ቸርነት ይህነን ያህል ዘመን ገዝቸ የለምን ግን ሰው ነኝና እንግዲህ እስንት ያህል ዘመን እቆያለሁ ስል ነው፡፡…… አገራችሁን ጠብቁ አደራ ብያችኃላሁ፡፡ አደራ የሚያኖሩበት ሰዉ የተማነ ስለሆነ ነው፡፡ … ተስማምታችኁ የኢትዮጵያድንበር እንዲሰፋ እንጂ አንድም ጋት መሬት እንዳይጠብ አድርጉ፡፡ ጠብቁ አልሙ፡፡ የደጊቱ አገራችን የኢትዮጵያ አምላክ ይግዛችሁ፣ ይጠብቃችሁ፡፡ ›› እነሆ ታላቁ ንጉሥ በዛሬዋ ቀን ነበር ያለፈው፡፡ እኛም ታላቁን ንጉሥ በእረፍቱ ቀን ልናስበው ወደድን፡፡ ኢትዮጵያ አንተን በመውለዷ ትደሰታለች፡፡ አፍሪካም በምድሯ አንተን ስላገኜች ትኮራለች፡፡ ሰው ስለሆንክ ብታልፍም የማያልፍም ሥራና ፍቅር ጥለህልን ስላለፍክ አንረሳህም፡፡ የጥቁርን ፀሐይ አውጥተኃልና እናመስግንኃለን፡፡ መልካም ዕረፍት፡፡ በማርሸት ጽሀው

Source: Link to the Post

Leave a Reply