(ሸክም የበዛበት ትውልድ፡ 2009 እና የምሥራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ)
ሀገር ተብላ የምትጠራ ማንኛውም የዜጎች መኖሪያ የኾነች አካባቢ በአለም የታወቀ የራሷ የኾነ ድንበር ያላት፣ ዕውቅና ያለው መንግሥት ያላት እንደኾነች ይታወቃል፡፡ ይህም ድንበር የራሱ የኾኑ አቅጣጫዎች ያሉት ነው፡፡ አንዱ አካባቢ ከሌላው ሊሰፋና ሰፋ ያለ ቁጥር ሊይዝ አልያም ያነሰና አነስ ያለ ቁጥር ሊይዝ ይችላል፡፡
ዞሮ ዞሮ ዋናው ነገር በውስጧ ይብዛም ይነስም ሰሜን፣ ደቡብ፣ ምሥራቅና ማዕከል ይኖራት ዘንድ ግድ ይላል፡፡ በመኾኑም ሀገር ማለት የነዚህ ውህድ ናት፡፡
ሀገር ያለዜጎች – ዜጎችስ ያለ ሀገር ሊታሰብና በተግባር ሊታይ ይችላልን? እንደምን ሁለት የተለያዩ ነገር ግን የማይነጣጠሉ ነገሮች ሊኾኑ ቻሉ? ይህ ከኾነ ዘንድ በጽንሰ ሀሳብና በተግባር ደረጃ ምን አይነት ዝምድና ይኖራል? ሊኖርስ ይገባል? ከምን አንጻር?
እንደሀገር “ኹሉም እንደየዕምነቱ የሚኮራበት ነገር በሌላኛው የሀገሩ ክፍል የሚገኝ ቢኾንም እንደሀገራዊነቱ፣ የአንድ ሀገር ዜጋ እንደመኾኑ ሰፋ አድርጎ ማየትና መተንተን ባለመቻላችን – ከዕምነቱና ከዕምነቱ ታሪክ ባሻገር በሀገራዊነቱ በቦታውና በቦታው አካባቢ ያሉ ቦታዎች ዕምነቱ የሚሰጡትን የኔነት፣ የኛነት፣ የባለቤትነት ስሜትና ኩራት፤ ታሪኩን የተሸከሙት ቦታዎች አይሰጡትም፡፡ አይሰማውም፡፡ እንዲሰጠውና እንዲሰማው ትርጉም ያለው ሥራ አልተሰራበትም፡፡ በዕምነቱ ባለቤት የኾነበትን፤ በዜጋነቱ ባለቤት መኾን አልቻለም፡፡ ዜጋነት ላይ ትርጉም ያለው ሥራ አልተሰራም፡፡”
“በአንድ የሀገራችን ክፍል የሚገኝን ባህል፣ uንu፣ ልማድ፣ ወግ፣ ታሪክ፣ ዕሴት፣ ዕድገት፣ ልማት፣ ብልጽግና፣ ገጠመኝ፣ ሐዘን፣ ደስታ፣ ችግር፣ ጉዳት፣ መከራና ሰቆቃ፣ – – – እንደሀገር ዜጋነታችን ባህላችን፣ uንuችን፣ ልማዳችን፣ ወጋችን፣ ታሪካችን፣ ዕሴታችን፣ ዕድገታችን፣ ልማታችን፣ ብልጽግናችን፣ ገጠመኛችን፣ ሐዘናችን፣ ደስታችን፣ ችግራችን፣ ጉዳታችን፣ መከራችንና ሰቆቃችን፣ – – – ማለት የሚያስችል እኛነት ወደ ያዘ ሀገራዊ ማዕቀፍ መሻገርና ማሻገር አልቻልንም፡፡” (ሸክም የበዛበት ትውልድ” ገጽ 151)
የአንዱ ህመም ለሌላው የማይሰማው ለምን ይኾን? የሀገር ህመም የሚባለውስ ማን ሲታመም ነው? ማን ሲሰጋ ነው – የሀገር ስጋት የሚባለው? የዜጎች ደህንነት በአስጊና በአስጨናቂ ኹኔታዎች ውስጥ አይደለምን ያለነው?
ከውጭ ለአንድ ቻይናዊ፣ እስራኤላዊ፣ የመናዊ፣ ኩባዊ፣ ታንዛንያዊ – – – ኢትዮጵያ ማለት በምሥራቅ አፍሪካ የምትገኝ ሀገር በውስጧ የሚኖሩ ሰዎችም በዜግነት ኢትዮጵያውያን እንደሚለን – እንደሚሉን አያጠያይቅም፡፡ በአንዱ የሀገራችን ክፍል የመኪና አደጋ አጋጥሞ ከ40 በላይ ሰዎች ቢሞቱ ለነሱ ኢትዮጵያውያን ሲኾን መላው የኢትዮጵያ ክፍል በሐዘን ላይ የሚወድቅ ይመስላቸዋል፡፡
በአንዱ የሀገራችን ክፍል ዜጎች በማንነታቸው ብቻ ሲፈናቀሉ፣ በአደባባይ ሲዘረፉና በድንጋይ ተቀጥቅጠው በአደባባይ ሲሰቀሉ – – – ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸሙት ድርጊት እንዴት ሊወስዱት እንደሚችሉ ግልጽ ነው፡፡
በጽንሰ ሀሳብ ዜጋ ማለት የሀገሩን ክፉ መስማት፣ ማየት፣ ማሽተት፣ ማንበብ፣ መጻፍ፣ መናገር – – – ወዘተ የማይሻ በአንጻሩ ለሀገሩ በጎ ምግባርን ለማሰማት፣ ለማሳየት፣ ለማሽተት፣ ለማስነበብ፣ ለማጻፍና ለመጻፍ፣ ለመናገርና ለማናገር በኹለንተናዊ መንገድ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴው ውስጥ ዕውን ይኾን ዘንድ የሚተጋ እንደኾነ ይታወቃል፡፡
እኛ በውስጣችን ግን ሐዘኑ፣ ቁጭቱና እልሁ በከባቢያዊነትና በመንደርተኝነት ላይ የተመሠረተ እንደኾነ እናውቃለን፡፡ ኢትዮጵያው ውስጥ ሕዝብ እንደሕዝብ ሲፈናቀል ከሰብዓዊነት፣ ከሕግ፣ ከሞራል ልዕልና ይልቅ ቀድሞ የሚነሣው ጥያቄ ማን? የሚል የማንነት ጥያቄ ነው፡፡ ከዛ የተለያዩ ጎራዎች ይፈጠራሉ፡፡
አንዳንዱ ትኩረት ባለመስጠት የድርጊቱ ተባባሪ ይሆናል፤ አንዳንዱ አይኑን በጨው አጥቦ ስለድርጊቱ ትክክለኛነት የዘቀጠና የወረደ አመክንዮን በማምጣት የሰብዓዊነትና በሕይወት የመኖር ታላቅ ጉዳይን የታሪክ አሰጣ ገባ፣ የሥልጣን ፖለቲካ የብሽሽቅ መጫወቻ ያደርገዋል፤ አንዳንዱ ድርጊቱን አውግዞ ድርጊቱን በራሱ የጥቂቶች ነው ብሎ የአብዝሃን በቁሙ መመልከትና በዝምታ መተባባር ቅቡል ለማድረግ ይጥራል፤ አንዳንዱ ድርጊቱን በሌላ ድርጊት ፍጻሜ ለመመለስ በመጣር ይንቀሳቀሳል፡፡ ዕውን ኢትዮጵያስ አለች – ኢትዮጵያውያን ግን አሉ?
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሚፈጸሙ ድርጊቶችን ስንመለከት ኢትዮጵያ ውስጥ ከመፈናቀል ይልቅ ዜጎች የሚፈናቀሉበት መንገድ፤ ከኢትዮጵያውያን ሞት ይልቅ አሟሟታቸው እጅግ በጣም አሳዛኝ ከመኾኑም በላይ ዕውን ይህን የሚፈጽሙት ኢትዮጵያውያን ናቸውን? ዕውንስ ከማህበረሰቡ ጋር የሚኖሩ ናቸውን? የሚል ጥያቄን እንድናነሣ ግድ ይለናል፡፡
ለአብነት፡- በቡራዮ የተፈጸመውን ድርጊት ስንመለከት ከ50 ያላነሱ ሰዎች መሞታቸውን ስንመለከት ከሞታቸው ባሻገር አሟሟታቸው በየትኛውም አመክንዮ ጤነኛ ሰዎች በኢትዮጵያ ሊፈጽሙት የሚችሉት ነው ተብሎ ባይታሰብም ተፈጽሟል፡፡ እዚሁ የዋና ከተማችን አፍንጫ ስር በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሲፈናቀሉ መመልከት በምንም ዓይነት ቃል ቢገለጽ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ሙሉ ስዕል ሊሰጥ አይችልም፡፡
ድርጊቱ ከተፈጸመ በኃላ መላው የሀገራችንን ዜጎች ያለ ምንም ልዩነት ሊያሰባስብና በጋራ በቁጭት፣ በእልህና በታላቅ እንባ ሊያወግዙት የሚገባ ተግባር ቢኾንም ጭራሽ የሥልጣን ፖለቲካ ሽኩቻ መወጫ መኾኑን መመልከት ልብ ያደማል፡፡
ሀገራችን በኹለንተናዊ መንገድ ስጋት ውስጥ መኾኗ ይታወቃል፡፡ ለዚህ ኹለንተናዊ ስጋት የዳረጉን በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም በዋናነት የምንላቸው እንጂ ኹሉን ጠቅልሎ የሚይዝ ነጥብ ማውጣት – አስቸጋሪ፣ ሰፊና ውስብስብ ከኾነው ባሕሪያዊና ጠባያዊ መገለጫው እንረዳለን፡፡
በጃንዋሪ 27, 1848 Alexis De Tocqueville በምክር ቤት ውስጥ ንግግር ሲያቀርብ ማጠቃለያውን ‘I believe we are sleeping on a volcano’ እንዳለው የሀገራችን ወቅታዊ ኹለንተናዊ ነባራዊ ኹኔታ እንደዛ በእሳተ ገሞራ ውስጥ እንዳንቀላፋን የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ እንደሀገር በእኔነት፣ በእኛነትና በእነሱት መሐከል ያለው መስተጋብር አለመጣጣም – እሳተ ጎመራነትን ከመፍጠር ባሻገር – እሱንም ያባብሳል፡፡ ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!
ቸር እንሰንብት!