ዜጎችን በገዛ ሐገራቸው አማራጭ መፍትሔ ሳይፈለግላቸው ሜዳ ላይ መበተን ከፍተኛ የጭካኔ ተግባር ነው ሲል ጎጎት ፓርቲ ገለጸ፡፡

የጉራጌ ህዝብ እኩልነት እና ፍትህ ፓርቲ በምህጻሩ ጎጎት፣ በሸገር እና አዲስ አበባ ከተሞች እየደረሰ ስላለው ቤት የማፍረስ ዘመቻ እንዲሁም በጉራጌ የመብት ታጋዮች ላይ እየደረሰ ስላለው የመብት ጥሰት አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል፡፡

ፓርቲው በመግለጫው ዜጎችን የማቋቋም እና የመደገፍ ስራ መስራት የሚጠበቅበት መንግስት የዜጎች ከለላ ሳይሆን የስጋት ምንጭ መሆኑን አመላክቷል፡፡
በሸገር ከተማ እየተፈፀመ የሚገኘው ቤት የማፍረስ ዘመቻ በአድማሱ እና ዜጎች ላይ እያደረሰ ባለው ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት በርካታ ዜጎችን ለከፋ ችግር ተጋልጠው ይገኛሉ ሲል አስታውቋል፡፡

በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ቤታቸው እና የንግድ ቦታቸው ፈርሶ በከፍተኛ ችግር ላይ ሲገኙ እጅግ በርካታ ዜጎች ደግሞ በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ይገኛሉ ነው ያለው።
ቤታቸው ፈርሶ ለከፋ የጎዳና ህይወት የተጋለጡ በርካታ ዜጎች መኖራቸውም ለመረዳት ችለናል ብሏል ጎጎት።

በዚህ ሂደት እየደረሰ ያለው ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት ከጊዜ ወደ ጊዘ እየተባባሰ መጥቶ ዜጎች በከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንዲወድቁ አድርጓል ሲል በመግለጫው አጽዕኖት ሰጥቷል፡፡
ዜጎች ቤት እና ንብረታቸው ከመውደሙ በላይ ሰብአዊ ክብራቸው ተዋርዶ፣ የገዛ ቤታቸው ማፍረሻ ሂሳብ እየተጠየቁ፣ እቃቸውን ይዘው እንዳይወጡ እየተከለከሉ መሆኑ፣ ይዘው ከወጡም የኬላ ተብለው ከፍተኛ ገንዘብ እየተጠየቁ እንደሆነ አረጋግጫለሁ ብሏል ፓርቲው ባወጣው መግለጫ፡፡

ይህ ሁሉ ተግባር ግልፅነት እና ተጠያቂነት በጎደለው መንገድ እየተፈፀመ ይገኛል ሲል አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል የጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትህ ፓርቲ አባላት እና አመራሮች ጨምሮ በርካታ የጉራጌ ልጆች ከወልቂጤ፣ ከአዲስ አበባ፣ ከቡታጅራ እና ቡኢ ከተሞች ታፍሰው ቡታጅራ ከተማ በሚገኘው ቡታጅራ ከተማ ፖሊስ ጊዚያዊ ማረፊያ ቤት ታስረው እንደሚገኙ ገልጿል፡፡

የመብት ታጋዮች፣ ፖለቲከኞች፣ ነጋዴዎች፣ አመራሮች፣ ወጣቶች፣ ጋዜጠኞች በህገ ወጥ መንገድ ለወራት በእስር ታግተው ያለ ፍትህ እየተጉላሉ እንደሚገኙ ነው ፓርቲው ያስታወቀው፡፡

በመሆኑም የሸገር ከተማ አስተዳደር እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዜጎች ሰብአዊ መብት ላይ እየፈፀሙ ያሉት ጥቃት በአስቸኳይ እንዲያቆሙ፣ ግልፅ እና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራር እንዲከተሉ፣ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ተገቢው ካሳ እና መቋቋሚያ እንዲሰጣቸው ጎጎት አሳስቧል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply