ዜጎች በሀገራቸው እና በቀያቸው በሰላም የመኖር ዋስትናቸው ስጋት ላይ ወድቋል ስትል የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ገለጸች፡፡ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ከየትኛውም…

ዜጎች በሀገራቸው እና በቀያቸው በሰላም የመኖር ዋስትናቸው ስጋት ላይ ወድቋል ስትል የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ገለጸች፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ከየትኛውም ሃይማኖት አስተምህሮ ፈጽሞ ተጻራሪ የሆኑ ክቡር የሆነውን የሰውን ልጅ ሕይወት ለሞት፣ ለመፈናቀል እና ለስደት የሚዳርጉ ተግባራት እየተደጋገሙ መጥተዋል ብላለች ቤተክርስቲያኗ፡፡

የሰውን ልጅ ክብር ለመግሰስ፣ ለሞት እና ለእንግልት ለመዳረግ የሚያበቃ ተቀባይነት ሊኖረው የሚችል ምንም ዓይነት ምክንያት እንደሌለ ቤተክርስቲያኗ ገልጻለች።

የሰው ልጅ በቅድስት ሥላሴ አምሳል የተፈጠረ፣ ሙሉ ክብር ያለው እና በምንም ምክንያት እና በማንም ሊገሰስ የማይችል በሕይወት የመኖር መብትን የተጎናጸፈ ነው።

በሕይወት መኖር ብቻ ሳይሆን ለመኖር ምቹ በሆነ አካባቢ፣ የአካል እና የአዕምሮ ደህንነቱ ተጠብቆ ሊኖር ይገባል ብላለች፡፡

ዜጎች በሀገራቸው፣ በቀያቸው በሰላም የመኖር ዋስትናቸው ስጋት ላይ እየወደቀ ያለበት ይህ ሁኔታ በእጅጉ አሳስቦኛል ብላለች።

እስካሁን በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች የበርካታ ንጹሀን ዜጎች ሕይወት ተቀጥፏል።

በርካቶች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በየመጠለያ ይገኛሉ።

የእነዚህ ሁኔታዎች ቀጥተኛ ተጎጂዎችም በብዛት አረጋውያን፣ ሴቶች እና ህፃናት ናቸው።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በየአካባቢው የሚፈጸሙ ዜጎችን ለሞት፣ ለመፈናቀል እና ለንብረት መውደም የሚዳርጉ ሁኔታዎችን አስመልክቶ በተለያዩ ጊዜያት ግልጽ ተቃውሞዋን በመግለጽ ስታወግዝ ቆይታለች።

አሁንም በጋምቤላና በምዕራብ ወለጋ የተፈጸሙትን በአብዛኛው ሴቶች እና ህፃናት ሰለባ የሆኑበትን የንጹሀን ወገኖች ግድያ በጽኑ ታወግዛለች።

እንዲሁም ሰው በማንነቱ እና በሃይማኖቱ መገደል የለበትም ትላለች ቤተክርስቲያኗ።

መንግሥት እና አካባቢያዊ አስተዳደሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ዜጎች በሙሉ ይህን መሰል እኩይ ተግባራት በአጭሩ እንዲቀጩ እና የቆየው እና በመላው ዓለም የምንታወቅበት የሕዝባችን ተከባብሮ እና ተደጋግፎ የመኖር ልማድ እንዲመለስ መስራት እንደሚገባ መልዕክቷን አስተላልፋለች፡፡

በሄኖክ ወ/ ገብርኤል

ሰኔ 18 ቀን 2014 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply