የሀመር አፈርን ከሌሎች የተፈጥሮ ግብዓቶች ጋር በማዋሀድ የፊት ውበት መጠበቂያ ማዘጋጀቱን ሄላዝ ቢውቲ አስታወቀ

የፊት ውበት መጠበቂያው ከመጪው መስከረም ወር ጀምሮ ለተጠቃሚዎች እንደሚቀርብ ተገልጿል

ዕረቡ ነሐሴ 25 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ሄላዝ ቢውቲ በአገራችን ደቡባዊ ክፍል ከሚገኘው የሀመር ምድር ላይ የሚገኘውን የሀመር አፈርን ከሌሎች የተፈጥሮ ግብዓቶች ጋር በማዋሀድ የፊት ውበት መጠበቂያ አዘጋጅቶ ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን በዛሬው ዕለት አስታውቋል፡፡

ምርቱ ላለፉት 3 ዓመታት መቀመጫቸውን አሜሪካ ባደረጉ የስነ-ውበት ባለሙያዎች ጥናት እና ምርምር ሲደረግበት ቆይቶ በተገኘው ውጤት፤ የፊት ውበትን ለመጠበቅ አቻ የሌለው መሆኑ በመረጋገጡ ምርቱን ወደ ገበያ ለማቅረብ ዝግጅት መጠናቀቁን የሄላዝ ቢውቲ መስራች እና ባለቤት ሄለን የማነህ ምርቱ ይፋ በተደረገበት መድረክ ላይ ተናግረዋል፡፡

ይህ በአገር ውስጥ የሚመረተው የፊት ውበት መጠበቂያ፤ ከመጪው መስከረም ወር 2015 ጀምሮ ለተጠቃሚዎች እንደሚቀርብ የገለጹት ሄለን፤ ምርቱን ከአገር ውስጥ በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በማምረት አገራችንን በዓለም ዓቀፍ ገበያ ተመራጭ የሆነች የውበት መጠበቂያ አምራች አገር ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

“በማኅበረሰባችን ዘንድ የምራዕባዊያን ብራንድ የተለጠፈባቸው ምርቶች ከፍተኛ ተቀባይነት አላቸው” ያሉት ሄለን፤ ሄላዝ ቢውቲ፤ ለምርቶቹ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎሉ ሥያሜዎችን በመስጠት፤ ወጣቱ ትውልድ በማንነቱ ሳያፍር እና ሳይሸማቀቅ በአገሩ ምርት እንዲኮራ ብሎም በዓለም አቀፍ መድረኮች ምርቶቹን እንዲያስተዋውቅ ለማበረታታት ድርጅቱ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።

ሄላዝ ቢውቲ ሥራዉን አገራዊ ሥያሜ ባላቸዉ የሊፕስቲክ ምርቶች ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት የጀመረ ሲሆን፤ ከእነሱም መካከል በርቺ ፣ ደፋር፣ ውቢት እና ጀግኒት የተሠኙት ይገኙበታል። ድርጅቱ በአሁኑ ሰዓት አንዲት ሴት ለመዋብ የሚያስፈልጋትን የውበት መጠበቂያ በዓይነትም ሆነ በጥራት የሚያሟሉ ከ 70 በላይ የተለያዩ የዉበት መጠበቂያ ምርቶችን ለደንበኞቹ እያቀረበ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በዛሬው ዕለት ይፋ የተደረገው “ሄላዝ ቢውቲ ሀመር ክሌይ ማስክ” የፊት ቆዳን ለማጥራት እና ለማለስለስ የሚያለግል ከመሆኑ በተጨማሪ፤ የፊት ቆዳን በጥንቃቄ በማጽዳት የሞቱ የቆዳ ሴሎችን፣ ጥቁር ነጥቦችን፣ ድርቀትን እና ከመጠን በላይ ዘይትን ማስወገድ ምርቱ ከሚሰጣቸው ጠቀሜታዎች መካከል ዋንኛዎቹ መሆናቸውም ተነግሯል፡፡

ሄላዝ ቢውቲ በሚያቀርባቸው የውበት መጠበቂያ ምርቶች፤ የተለያዩ ዓለም አቀፍ እውቅናዎችን ማግኘቱ በመድረኩ የተገለጸ ሲሆን፤ ከእነዚህም መሀከል በዓለም አቀፍ ደረጃ የውበት እና ፋሽንን የተመለከቱ መረጃዎች በማውጣት በሚታወቀው ግላሞር በተሰኘው ድረ-ገጽ በ2022 በዓለም ላይ ከሚገኙ ምርጥ 13 ሊፕስቲኮች መሀል ውቢት የተሰኘውን ሊፕስቲክ በ2ተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጦታል።

በተጨማሪም በአሜሪካ በ2021 በታተመው ምርጥ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች ታሪክ ዘጋቢ የሆነ ፅሁፍ ላይ፤ የሄላዝ ቢውቲ መስራች እና ባለቤት ሄለን የማነን ማስቀመጡም ተነግሯል፡፡

ሄላዝ ቢውቲ የውበት መጠበቂያ ምርቶችን ከማቅረብም በተጨማሪ፤ ማህበራዊ ሀላፊነትን ከመወጣት አንፃር የተለያዩ ሥራዎች በመስራት ላይ እንደሚገኝ ተነግሯል።

ከእነዚህም ሥራዎች መካከል፤ “ማንም ሴት በወር አባባ ምክንያት ከትምህርት ገበታዋ መሰናከል የለባትም” የሚል ሃሳብን ይዞ እየተንቀሳቀሰ ለሚገኘው ”አደይ ፓድስ“ እንዲሁም፤ ወጣት አካል ጉዳተኞችን በሙያ የማብቃት ሥራን በመስራት ላይ ለሚገኘው ተኪ የወረቀት ከረጢት መምረቻ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝም በመድረኩ ተገልጿል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply