የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ለ700 ሺህ አርሶ አደሮች የተሻሻሉ የስኳር ድንች ዝርያዎችን እያሰራጨ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በምስራቅና ምዕራብ ሀረርጌ ለ700 ሺህ አርሶ አደሮች የተሻሻሉ የስኳር ድንች ዝርያዎችን እያሰራጨ መሆኑን አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው የተመራማሪዎችና የአርሶ አደሮች የምርምር ቡድን አባላት በባቢሌ ወረዳ እየተካሄደ ያለውን የስኳር ድንች ልማት ትላንት በመስክ ጎብኝተዋል ።

በዩኒቨርሲቲው የምርምር የፕሮጀክቱ አስተባባሪና ተመራማሪ ዶክተር ደንደና ገልሜሳ÷ ዩኒቨርሲቲው ከታህሳስ 2011 ዓም ጀምሮ በአስራ አንድ የስኳር ድንች ዓይነቶች ላይ የምግብ ንጥረ ነገር ይዘት ልየታና የዝርያ ማሻሻል ምርምር እያካሄደ መሆኑን ገልጸዋል ።

በዚህም ምርምር እየተካሄደባቸው ካሉ የስኳር የድንች አይነቶች ውስጥ የሶስቱ ስራቸው ተጠናቆ ዝርያቸውን ለአርሶ አደሮች ማሰራጨት መጀመሩን ተናግረዋል ።

ለአርሶ አደሩ እየተሰራጩ ያሉት የስኳር ድንች ዝርያዎች ዲላ፣ አልሙራና ከቡዲ የተሰኘ ስያሜ የተሰጣቸውና በምግብ ንጥረ ነገር ይዘታቸው የበለጸጉ መሆናቸውን ጠቁመው ÷በምስራቅና በምዕራብ ሐረርጌ ለ700 ሺህ አርሶአደሮች ዝርያዎቹን ማሰራጨት መጀመሩን አመልክተዋል ።

የስኳር ድንች ዝርያዎቹ በሶስት ወር ጊዜ ለምርት የሚደርሱና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያግዙ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ከዚያም ባለፈ በቫይታሚን ኤ፣ አይረንና፣ ዚንክ ንጥረ ነገሮች የበለጸጉ በመሆናቸውም በእርግዘና ወቅት በእናቶች ሰውነት የደም እጥረት እንዳያጋጥም የሚረዱና የህጻናት የመቀንጨር ችግርን ለመከላከል የሚረዱም ናቸው ብለዋል።

የምርምር ፕሮጀክቱ በአንግሊዝ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ እንደሚካሄድና ለቀጣይ ለሶስት ዓመት የሚዘልቅ መሆኑን ማመላከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል ።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

The post የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ለ700 ሺህ አርሶ አደሮች የተሻሻሉ የስኳር ድንች ዝርያዎችን እያሰራጨ መሆኑ ተገለጸ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply