የሀይሌ ዝዋይ ሪዞርት ዛሬ ስራ ጀመረ።

በኦሮሚያ ክልል ባቱ ወይም ዝዋይ ከተማ ላይ የተገነባው የሀይሌ ዝዋይ ሪዞርት እደሳው ተጠናቆ ዛሬ ዳግም ስራ ጀምሯል፡፡

የአርቲስት አጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሰው ሁከት ዝዋይ ከተማ በሚገኘው የሀይሌ ዝዋይ ሪዞርት ላይ ጥቃት መሰንዘሩ ይታወቃል፡፡

በሀይሌ ሆቴሎችና ሪዞቶች የኦፕሬሽን ዘርፍ ዳሬክተር አቶ ጋዲሳ ግርማ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደገለፁት ሪዞርቱ 80 በመቶ ውድመት ስለደረሰበት ስራ አቁሞ ነበር።

አሁን ላይ ግን ሀይሌ ዝዋይ ሪዞርት የደረሰበት ውድመት እንደገና በማደስ ዛሬ ስራ ጀምሯል ብለዋል፡፡

ሪዞርቱ በተሰነዘረበት ጥቃት ሳቢያ ስራ ከማቆሙ በፊት 60 የሚደርሱ የመኝታ አልጋዎች የነበሩት ሲሆን በየቀኑ በአማካኝ 80 በመቶ የሚሆኑት አልጋዎች እንደሚያዙ አስታውሰዋል፡፡

ሪዞርቱ አሁን ላይ 52 የተለያዩ አይነት የመኝታ ክፍሎች ፤ ሁለት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ፤ 2 ሬስቶራንት ፤ መዋኛ ገንዳ እንዲሁም የጤና ክለብም ሙሉ እደሳ ተደርጎላቸው ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ቀደም ሲል የነበረንን ገበያ መመለስ በሚያስችል መልኩ እደሳው ተጠናቆ ዛሬ ስራ መጀመሩን ነግረውናል፡፡

አቶ ጋዲሳ ግርማ ሪዞርቱ በኮንስትራክሽን ዘርፍ እና የሆቴል ረገድ እድሳት የተደረገ ሲሆን በሁለቱ ዘርፍ ለእደሳ የወጣው ገንዘብ አሁን ላይ ሪፖርቱ አልደረሰም ብለዋል፡፡

ለእደሳው መንግስት በቃል ደረጃ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ከመስጠት ባለፈ ለእደሳው ምንም አይነት ካሳ እንዳልከፈለ ከሆቴሉ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በደረሰ አማረ
ሕዳር 22 ቀን 2013 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply