የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ ነገ ይጀመራል

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ ነገ ይጀመራል

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከግንቦት 21- 27 ቀን 2016 ዓ.ም ለሰባት ተከታታይ ቀናት የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ በአዲስ አበባ ያካሂዳል፡፡

 በነገው ዕለት ግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም የመክፈቻ ሥነስርዓቱ በአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም እንደሚከናወን ታውቋል፡፡

በዚህ የመክፈቻ ሥነስርዓት ላይ ከየወረዳው የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ ከ1700 በላይ የሚሆኑ ተሳታፊዎች ይገኙበታል ተብሏል፡፡

”ይህ መድረክ ህብረተሰቡ ከዚህ ቀደም ብዙም ባልተሄደበት ሁኔታ በሀገሩ ጉዳይ ላይ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እኩል የመምከር መብቱን ተግባራዊ ለማድረግ የተሄደበት እርቀት ማሳያ ነው፡፡ የሀገራዊ ምክክሩ ሁሉን አካታችና አሳታፊ መሆን አንድ ማሳያም ነው፡፡“ ብሏል- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፡፡

ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ ከተማ በሚያከናውነው በዚህ  የምክክር ምዕራፍ፣ ከ2500 በላይ ተወካዮችን ተሳታፊ  እንደሚያደርግ ተነግሯል፡፡

ለሰባት ቀናት በተከታታይ የሚካሄደው የምክክር ምዕራፍ፣ ሦስት ዋና ዋና ተግባራት እንደሚከናወኑበት ኮሚሽኑ አመልክቷል፡፡ ይኸውም፡- በዚህ እርከን ላይ የሚገኙ ተሳታፊዎች በውይይትና በምክክር የአጀንዳ ሃሳቦችን ያመጣሉ፤ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት አጀንዳዎቻቸውን የጋራ በማድረግ ያሰባስባሉ፣ ያደራጃሉ እንዲሁም የመፍትሄ ሃሳቦችን ያንሸራሽራሉ፤ በመጨረሻም የሂደቱ ባለድርሻ አካላት ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊ የሚሆኑ ተወካዮቻቸውን ይመርጣሉ – ተብሏል፡፡

መርሃ ግብሩ፤ ኮሚሽኑ በከተማ አስተዳደሩ ሥር ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ሀገራዊ መግባባት ሊደረግባቸው ያስፈልጋል የሚሏቸውን እጅግ መሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን የያዙ አጀንዳዎችን በህዝባዊ ውይይት የሚሰበስብበት ምዕራፍ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በቀጣይነት ኮሚሽኑ ተመሳሳይ መርሃግብሮችን በክልሎች ከተማ አስተዳደሮች እንደሚያከናውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለኢትዮጵያውያን ባስተላለፈው መልዕክት፤ ኢትዮጵያውያን የሚደረገውን የምክክር ሂደት ፋይዳ በመረዳት ዝግጅት እንዲያደርጉና በንቃት እንዲሳተፉ የጠየቀ ሲሆን፤ ለሂደቱ ስኬት ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርቧል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply