የህወሓት ቡድን ትንኮሳ ያደረገባቸውን ስትራቴጂክ ቦታዎች የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ማስለቀቁን አስታወቀ፡፡

የህወሓት ቡድን ቆቦ ከተማን በመቆጣጠር ወደ ሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች በቀላሉ ለማለፍ በተለምዶ የአርሴማ ተራሮች የተባሉ አራት ተራሮችን እስከ ሀምሌ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ተቆጣጥሮ ለቆቦ ከተማ ነዋሪዎች ከፍተኛ ስጋት ሆኖ መቆየቱን ኮምሽኑ አስታውሷል።

ሆኖም የፌዴራል ፖሊስ ሰሜን ዳይሬክቶሬት ዲቪዥን አራት ፈጥኖ ደራሽ አባላት ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በርካታ የህወኃት ሃይሎችን በመደምሰስ አራቱንም ተራሮች ማስለቀቁን የፌደራል ፖሊስ ኮምሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጄላን አብዲ ለአሀዱ ተናግረዋል፡፡

የጠላትን ግብዓተ መሬት ሳንፈጽም አንመለስም ያሉት የሰሜን ዳይሬክቶሬት ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ሻለቃ ምክትል አዛዥ ኢ/ር ሀሰን አብዱ የፌዴራል ፖሊስ አባላቱ ከሀገር መከላከያ ሰራዊትና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የህወሓት ቡድን ላይ እርምጃ በመውሰድ፤ የተማመነባቸውን ስትራቴጂክ ቦታዎች በማስለቀቅ ለአካባቢው ማህበረሰብ መረጋጋትን መፍጠር መቻሉን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

አባላቱ በአሁኑ ወቅት ወደ ሌላ ግዳጅ ለመሰማራት ዝግጅታቸውን አጠናቀው ትእዛዝ እየተጠባበቁ መሆናቸውንም የሰሜን ዳይሬክቶሬት ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ሻለቃ ምክትል አዛዥ ኢ/ር ሀሰን አብዱ መናገራቸውን ዳይሬክተሩ ለአሀዱ ተናግረዋል።

ለሀገር ሉዓላዊነት ሲባል ህዝባችንን ከጎናችን በማሰለፍና ቡድኑን እስከ መጨረሻው ለማጥፋት መስዋትነትም ጭምር ለመክፈል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዝግጁ መሆን ይጠበቅበታል ብለዋል።

ቀን 11/12/2013

አሐዱ ራድዮ 94.3

Source: Link to the Post

Leave a Reply