የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በቅድመ ምርጫ ባደረገዉ ቅኝት የምርጫ ቦርድ መረጃዎች ለገጠሩ ማህበረሰብ እየደረሱ አለመሆኑን አረጋግጫለሁ አለ፡፡

የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በቅድመ ምርጫ ፤በምርጫ ወቅት እና በድህረ ምርጫ ያሉ የመረጃ እና ሌሎች ምርጫ ነክ ጉዳዮችን በሚመለከት ምልከታዎችን አደርጋለሁ ማለቱ ይታወሳል፡፡በቅድመ ምርጫ ወቅት ባደረገዉ ቅኝትም ለማህበረሰቡ በምርጫ ቦርድ አማካኝነት የሚሰጡት መረጃዎች በአንጻራዊነት እጅግ የተሻሉ እና የሚበረታቱ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ችለናል ያሉት የተቋሙ የመረጃ ነጻነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ማናዬ አለሙ ናቸው፡፡

ሆኖም ምርጫ ቦርድ በተለያዩ አማራጮች የሚያስተላልፋቸዉ መረጃዎች ለገጠሩ ማህበረሰብ በትክክል እየደረሰ እንዳልሆነ ተቋሙ ማረጋገጡን ለአሀዱ ተናግረ ዋል፡፡ምርጫ ቦርድ ካለፉት አምስት ምርጫዎች በተሻለ መረጃዎችን ለመራጩ ማህበረሰብ እያደረሰ ቢሆንም በተለይ በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚተላለፉ መረጃዎች በገጠር ላሉ ማህበረሰቦች እንዲደርሱ በምን መልኩ ታሳቢ ተደርጓል የሚለዉን ጥያቄ ያስነሳል ብለዋል፡፡

አደረግነው ባሉት ምልከታም በመረጃ ክፍተት የተነሳ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ምርጫዉ መቼ እንደሚደረግ እንኳን የማያዉቁ ሰዎች ማግኘታቸዉን ተናግረዋል፡፡አሀዱም የተነሳዉን ሀሳብ መነሻ በማድረግ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ በቀጣይ በዚህ ጉዳይ ላይ ቦርዱ ምላሽ የሚሰጥ ከሆነ ይዘን እንቀርባለን፡፡

ቀን 03/10/2013

አሐዱ ራድዮ 94.3

The post የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በቅድመ ምርጫ ባደረገዉ ቅኝት የምርጫ ቦርድ መረጃዎች ለገጠሩ ማህበረሰብ እየደረሱ አለመሆኑን አረጋግጫለሁ አለ፡፡ appeared first on አሐዱ ራድዮ 94.3 እና ቴሌቪዥን.

Source: Link to the Post

Leave a Reply