የላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናት የዕድሳት ሥራ እስካሁን አለመጀመሩ ተገለጸ

ከአራት ዓመት በፊት ታቅዶ የነበረው የላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናት የዕድሳት ሥራ እሳካሁን አለመጀመሩን የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ባህል እና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል፡፡

በጽህፈት ቤቱ የቅርስ ጥበቃ ቡድን መሪ ማንደፍሮ ታደሰ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፤ በ2011 መጨረሻ በፈረንሳይ መንግሥት ዕድሳት ሊደረግለት የተለያዩ ጥናቶች ተደርገው በቅርብ ቀናት ውስጥ የእድሳት ሥራው ይጀመራል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፤ እስካሁን ድረስ የዕድሳት ሥራው ሊጀመር አልቻለም።

2011 ላይ የከተማው ነዋሪ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናቱ የዕድሳት ሥራ ሊደረግላቸው ይገባል ብሎ በሰላማማዊ ሰልፍ ጭምር መጠየቁን ተከትሎ፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ እንዲሁም የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ወደ ሥፍራው አቅንተው የጉዳት መጠኑን መመልከታቸውን አስታውሰዋል፡፡

በወቅቱ 24 ባለሙያዎችን ያካተተ የጥናት ቡድን ከፈረንሳይ አገር መምጣታቸውን እና ሰባት የጥናት ዓይነቶችን በውቅር አቢያተ ክርስቲያናቱ ላይ መደረጉን ጠቅሰው፤ የጥናቱ ውጤትም ለኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን መላኩንም ተናግረዋል፡፡

ሆኖም በመሀል በተከሰተው የሰሜኑ ጦርነት እና በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የጥናት ቡድኑ ዳግም ወደ ሥፍራው ማቅናት ባለመቻሉ፤ ጥናቱ ተጠናቆ የዕድሳት ሥራው እንዳይጀመር ምክንያት ሆኗል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ የዕድሳት ሥራው እንዲጀመር ጥላው (ሼልተር) ቀድሞ መነሳት ስላለበት በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን በኩል በዚህ ላይ የሥራ ልምድ ያላቸው ዓለም አቀፍ ብቁ ባለሙያዎችን አወዳድሮ ለማሰራት ሂደት ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

ቡድን መሪው አክለውም፤ ካሉት 11 ውቅር አቢያተ ክርስቲያናት በተለይ ቤተ አማኑኤል የተሰኘው ውቅር ቤተክርስቲያን ላይ የደረሰው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ አስቸኳይ እድሳት ካልተደረገለት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የላሊበላ ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ ተስፋሀብቴ አበራ በበኩላቸው ለእድሳት ሥራው አንደኛ ዙር የበጀት ስምምነት መደረጉን ከጠቀሱ በኋላ፤ ከተማ አስተዳደሩ ከቤተክርስቲያኒቱ መዋቅር ጋር ሳይቀር ተደጋጋሚ ውይይቶች ማደረጉን ገልጸዋል።

ከንቲባዋ አክለውም፤ “ለኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን በተደጋጋሚ ለምን የጥገና ሥራው አይጀመርም?” ብለን ጠይቀን የተሰጠን መልስ “የጥናት ሥራው አላለቀም እንዲሁም በአካባቢው እንደልብ ተንቀሳቅሶ ለመስራት የጥናት ቡድኑ የጸጥታ ስጋት አለበት” የሚል መሆኑን ጠቅሰዋል።

እንዲሁም ከኮሮና ቫይረስና ከጦርነቱ በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ የቱሪስት መጥን በመኖሩ፤ ከቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ እና የከተማዋን ነዋሪ በእጅጉ ጎድቷል ነው የተባለው።

አዲስ ማለዳ ከኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ለተቋሙ ዳይሬክተር ደጋግማ ብትደውልም ስልክ ባለማንሳታቸው ሳይሳካ ቀርቷል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply