የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያዉያንን ከድንቁርና ነፃ የማዉጣት ኃላፊነት አለባቸው የሐረር ፍትህና ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ [ሐፍዴፓ] ኢትዮጵያ አገራችን ከ፲፱፻፹፫ ዓ.ም. ግንቦት ወር ጀምሮ በታ…

የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያዉያንን ከድንቁርና ነፃ የማዉጣት ኃላፊነት አለባቸው የሐረር ፍትህና ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ [ሐፍዴፓ] ኢትዮጵያ አገራችን ከ፲፱፻፹፫ ዓ.ም. ግንቦት ወር ጀምሮ በታ…

የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያዉያንን ከድንቁርና ነፃ የማዉጣት ኃላፊነት አለባቸው የሐረር ፍትህና ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ [ሐፍዴፓ] ኢትዮጵያ አገራችን ከ፲፱፻፹፫ ዓ.ም. ግንቦት ወር ጀምሮ በታሪኳ አይታ በማታዉቀው አይነት ከፋፋይ እና አገር አፍራሽ የፖለቲካ ኃይል ስር እንዳለች ይታወቃል። ይህ ከኢትዮጵያ ታሪክ እና ከህዝቧ ባህልና ወግ ዉጭ የሆነ ፍልስፍና የሚከተል የፖለቲካ ሃይል ቀደም ሲል በህወሃት/ኢህአዴግ አሁን ደግሞ በብልፅግና መሪነት የአገሪቱን የመንግስት ስልጣን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሮ ይገኛል። ከኢህአዴግ ወደ ብልፅግና በተደረገው ሽግግር ወቅት ለኢትዮጵያ ሕዝብ በዶ/ር አብይ አህመድ የተገባው ቃልና የተሰጠው ተስፋ እጅግ መልካም ከመሆኑ የተነሳ ብልፅግና ስሙን የቀየረ ኢህአዴግ መሆኑን ሳይቀር የኢትዮጵያ ሕዝብ ረስቶት ነበር። ሆኖም ያደቆነ ሰይጣን …እንደሚባለው በህወሓት ፀረ-ኢትዮጵያ ትርክት ተኮትኩተው ያደጉ የብልፅግና ባለስልጣናት የኢትዮጵያን ህዝብ ተስፋ ድጋሚ አጨልመዉታል። በሚናገሩት ቋንቋ እና በተወለዱበት ቦታ ምክንያት ያለምንም ችሎታ እና ብስለት በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሚቀመጡ ባለስልጣናት የህወሓት አገር አፍራሽ ትርክት እና ወዋቅር በምንም መልኩ እንዳይለወጥ ወይም እንዳይሻሻል ሳንጃ እና ጦር ወድረው እንደቆሙ እያየን ነው። ህወሓት በኦህዴድ እስከተተካበት ቀን ድረስ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚዘገንን ሁኔታ የተጨፈጨፉትን ወገኖቻችንን ትተን፣ ህወሓት ወደተቀበረበት ትግራይ ከሸሸ በኋላ ብቻ ያለዉን ብናይ፤ በጥላቻ መንፈስ የተለከፉ ወጣቶች እና የጎሳ ፖለቲካ ዉጤት የሆኑት ልዩ ኃይሎች እና ፖሊሶች በታሪካችን የተማረከ ጠላት ላይ እንኳን ያላሰየነውን አረመኔያዊ ጭካኔ በገዛ ወገናቸው ላይ እየፈፀሙ ይገኛሉ። ጎሳ እና ቋንቋን መሰረት ያደረገ ጥቃት የድንቁርና እና የበታችነት ስሜት ዉጤት እንደሆነ ለማንም ግልፅ ነው። በሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ላለዉ ግፍ ዋና መንስኤው ህወሓት/ኢህአዴግ በጀመረዉ እና ብልፅግና በወረሰው የተመረዘ ልብ ወለድ ታሪክ እና አገር ለማፍረስ ታስቦ በጥቂቶች ፍላጎት ብቻ አገራችን ላይ የተጫነው ህገ መንግስት ነው። በዚህ የተመረዘ የታሪክ አስተምህሮ እና ሰዉን በሰዉነቱ ሳይሆን በጎሳ ማንነቱ ብቻ እውቅና የሚሰጠው ህገ መንግስት የማይገባቸዉን ስልጣን እና ሀብት የሰጣቸው ኃይላት ከሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ የዉድድር ዉስጥ የሚያልፉበት ስርዓት እንዳይመጣ የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ አይጠፋንም። በጎሳ ተዋፅዖ እና ለአገር አፍራሹ ህገ መንግስት ባላቸው ተአማኒነት በተመረጡ ሰዎች ከሚመራው የፍትህ ስርዓትም ብዙ ተስፋ ማድረግ እንደማይቻል የተረዳነው ወንጀለኞች እንዳሻቸው እየሆኑ የነፃነት እና የፍትህ ድሞፆች እስር ቤት ሲወረወሩ ነው። አሁን የኢትዮጵያ ሕዝብ የቀረው አንድ አማራጭ ነው – የህዝብ መገናኛ ብዙኃን። በሕዝብ የተመረጠ እና ለሕዝብ ታማኝ የሆነ መንግስት ባለበት አገር የህዝብ መገናኛዎች የሕግ አዉጭዉን፣ ፈፃሚዉንና፣ አስከባሪዉን ያህል ከፍተኛ ስልጣን እንዳላቸው እና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት አራተኛው ምሰሶ እንደሚባሉ ይታወቃል። እንዳለመታደል ሆኖ በአገራችን ኢትዮጵያ የፖለቲካ ባለስልጣናቱን የሚያባብል እንጂ ለሕዝብ ድምፅ የሚሆን የህዝብ መገናኛ ስርአት አልተመሰረተም። ለፍትህ እና እኩልነት ድምፃቸውን ያሰሙ ጋዜጠኞች እና ፀሐፊዎችም ተልካሻ ምክንያት እየተፈለገ ብዙ ግፍን መከራ ደርሶባቸዋል። አሁንም ብዙ ግፍና መከራ እየተቀበሉ ያሉ በርካታ ጋዜጠኞች እንዳሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያዉቃል። ይሄ ለሕዝብ እና ለአገር የሚከፈል መስዋዕትነት በኢትዮጵያ ታሪክ በደማቅ ቀለም እንደሚፃፍ ጥርጥር የለንም። ሆኖም የህዝብ መገናኛ ብዙኃን አሁን ከባድ ኃላፊነት ትከሻቸው ላይ እንደወደቀ ይሰማናል። ከላይ እንዳስቀመጥነው ኢትዮጵያ ዉስጥ ለ ፴ አመታት በተነዛዉ የዉሸት ታሪክ እና ለሱ ሕጋዊ ቁመና በሰጠዉ ህገ መንግስት ምክንያት ኢትዮጵያዉያን በገዛ አገራቸው ታይቶ እና ተሰምቶ የማይታወቅ ግፍ እየተቀበሉ ነው። ይሄን ሆን ተብሎ የተፈጠረ ድንቁርና መዋጋት አሁን አገራችን ያጋጠማትን ችግር ለመፍታት ዋናው መንገድ ነው ብለን እናምናለን። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ፖለቲከኞች መስማት የሚፈልጉትን ሳይሆን እዉነት የሆነውን የኢትዮጵያ ታሪክ ሕዝብ እንዲያዉቅ የማድረግ ግዴት አለባቸው። በጎሳ ፖለቲካ ዉስጥ ተኮትኩተዉ ያደጉ አሮጌ እና ነባር ባለስላጣናት ሳይሆን የታሪክ ምሁራንን ረጅም ጊዜ በመስጠት ሕዝብ እንዲያስተምሩ ማድረግ ያስፈልጋል። በዉሸት እና ምንም ሳይንሳዊ መሰረት የሌለዉን ጎሳ እና ቋንቋ ተኮር ክፍፍል ከመሰረቱ ለፖለቲካ አጀንዳ እንጂ ለሕዝብ ጥቅም ተብሎ እንዳልመጣ ለሕዝብ የማስተማር ግዴታ አለባቸው። በጎሳቸው ምክያት አዋቂ ነን ብለዉ የሚያስቡትን ሳይሆን በሰሩት ሥራ አንቱ የተባሉ የማህበራዊ ሳይንስ እና የፍልስፍና ምሁራንን በቂ ጊዜ በመስጠት ይህን ድንቁርና መታገል ያስፈልጋል። ምንም እንኳን በሕዝብ ሀብት እና ንብረት የሚንቀሳቀሱ ቢሆንም በርካቶች የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት አሁን ድረስ የሚመሩት በህወሓት/ኢህአዴግ የዉሸት ትርክት የተማረኩ እና ቋንቋን ከደም እና አጥንት ጋር አንድ አድርገው በሚያስቡ ሰዎች ነው። ስለዚህ ትግሉ የሚጀምረዉ ከዉስጥ ነው። ይሄ ይገባናል። ቢሆንም አገር በሁላችንም መስዋዕትነት ነው እና የምትገነባዉ በመገናኛ ብዙኃን ዉስጥ የምትሰሩ ኢትዮጵያዉያን እዉነት ነፃ ታወጣለች እና እዉነቱ እንዲታዉቅ የምትችሉትን ሁሉ አድርጉ። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዉያን ህወሓት/ኢህአዴግ ወይም በአዲስ ስሙ ብልፅግና ከሰፋልን የትምህርት፣ የፖለቲካ፣ የፍትህ እና የአስተዳደር ስርዓት በላይ ነን። በየሙያዉ ለምድር የከበዱ ኢትዮጵያዉያን መድረክ እና ዋስትና አጥተው ዝም ብለዉ ተቀምጠዋል። ለጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች እድሉን የምትሰጡትን ያህል የጎሳን ፖለቲካ እና ኢትዮጵያ ላይ ያለዉን ብልሹ አስተዳደር እርቃኑን የሚያስቀሩ ምሁራንን ፈልጋችሁ እድሉን ስጧቸው። ይህን ማድረግ ከቻላችሁ ሕዝብ እዉነቱን ያውቃል። እዉነቱን ካወቀ ከስሜታዊነት ይድናል። ከስሜታዊነት ከዳነ ወገኑን መግደል ያቆማል። እዉነቱን ካወቀ ከስልጣናቸው ዉጭ ምንም አጀንዳ የሌላቸው ደካማ ፖለቲከኞችን ተንኮል ይረዳል። ተንኮላቸዉን ከተረዳ ይታገላቸዋል። ከታገላቸው ያሸፋቸዋል። አሸንፎም ነፃነቱን ይቀዳጃል። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነት በእናንት እጅ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ እሁን ካለበት የድንቁርና ባርነት ነፃ የሚወጣዉ የህዝብ መገናኛ ብዙኃን ከእውነት እና ከሳይንስ ጋር ሲቆሙ ብቻ ነው። የኛም ጥያቄ ይሄው ነው። ከእዉነት እና ከሳይንስ ጋር ቁሙ!! የሐረር ፍትህና ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ [ሐፍዴፓ] ታሕሣሥ ፲፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓም ሐረር ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኖራለች!!

Source: Link to the Post

Leave a Reply