የሕዝቦችን አንድነት ለመበተንና ሃገር ለመበጥበጥ የሚሰሩ ወንጀለኞችን መንግሥት አይታገስም – አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ

የሕዝቦችን አንድነት ለመበተንና ሃገር ለመበጥበጥ የሚሰሩ ወንጀለኞችን መንግሥት አይታገስም – አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሕዝቦችን አንድነት ለመበተንና ሃገር ለመበጥበጥ የሚሰሩ ወንጀለኞችን መንግሥት እንደማይታገስ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ገለጹ፡፡

አፈ ጉባኤውና የመከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙን ጨምሮ ከፍተኛ የፌደራልና የደቡብ ክልል አመራሮች በጉራፈርዳ ወረዳ ጥቃት ከደረሰባቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ወቅት በተደራጀና ስልጠና በወሰዱ ቡድኖች በተቀነባበረ ሁኔታ ጥቃቱ እንደተፈፀመና የአመራሮችም እጅ እንዳለበትም ተነስቷል።

በውይይቱ የተገኙ የኢፌዴሪ መከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል አደም መሐመድ ጥቃት ባደረሱ ወንጀለኞች ላይ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

በስፍራው ተጨማሪ ኃይል እንደሚሰማራ በመግለፅ ወንጀለኞች የትም ተደብቀው እንደማይቀሩም ነው የገለጹት።

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በበኩላቸው በተፈጠረው ችግር በክልሉ ስም ይቅርታ ጠይቀው፣ እጃቸው አለበት በተባሉ አመራሮች ላይ ማጣራት ተደርጎ እርምጃ እንደሚወሰድ አስረድተዋል።

በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በፀጥታ መዋቅሩ ላይ ማሻሻያ ይደረጋል ያሉት አቶ ርስቱ፣ በአካባቢው ያሉ ሚሊሻዎችን ትጥቅ ማስፈታትና እንደገና የማደራጀት ሥራ ይሰራልም ብለዋል።

እስካሁን እጃቸው አለበት ተብለው በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች 21 መድረሱን የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ነብዩ ኢሳያስ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

በጥቃቱ ከ2 ሺህ 635 ሰዎች በላይ መፈናቀላቸው የተገለጸ ሲሆን ጉዳዩን የሚያጣራ የምርመራ ቡድን ወደ ስፍራው ማቅናቱንም ነው ያስታወቁት፡፡

በተስፋዬ ምሬሳ

The post የሕዝቦችን አንድነት ለመበተንና ሃገር ለመበጥበጥ የሚሰሩ ወንጀለኞችን መንግሥት አይታገስም – አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply