የሕጋዊነት ጥያቄ ባልተመለሰበት ሁኔታ የመንግስት የመኖሪያ ቤቶች ጨረታ በይፋ ተከፈተ


የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን ከሦስት ሺህ በላይ ቤቶችን ለሽያጭ ማቅረቡ ላይ የሕጋዊነት ጥያቄ ባነሳበት ሁኔታ የመኖሪያና የንግድ ቤቶቹ ጨረታ በዛሬው ዕለት መጋቢት 3 ቀን 2016 በይፋ ተከፍቷል።

የአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ እና የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ያስገነቧቸው የመኖሪያና የንግድ ቤቶች ጨረታ ታዛቢዎችና ተጫራቾች በተገኙበት መክፈታቸውን አዲስ ማለዳ ከቢሮው ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ኮርፖሬሽኑ ጥር 27 ቀን 2016  ጀምሮ ይፋ ባደረገው ማስታወቂያ፣ አጋጠመኝ ያለውን የፋይናንስ አቅም ችግር ለመፍታትና ተጨማሪ ወጪ ቆጣቢ ቤቶችን ለመገንባት በማለት የመኖሪያ ቤቶች እና የንግድ ሱቆችን በጨረታ ለመሸጥ የጨረታ ሰነዶችን ሽያጭ ከተጠቀሰው ቀን ጀምሮ ለተከታታይ 20 ቀናት ሲያካሄድ ቆይቷል። 

በዚህም በማይመለስ 1 ሺህ ብር ሲሸጠ የነበረው የቤቶች ጨረታ ሰነድ ማስገቢያ ጊዜ በትናንትናው ዕለት መጋቢት 2 ቀን 2016 ተጠናቋል።

ከዚህ ቀደም ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን ያቀረቡ የ1997 እና የ2005 ተመዝጋቢ የመኖሪያ ቤት ፈላጊዎች የጨረታ ማስታወቂያው ቤት ለማግኘት ለዓመታት ሲቆጥብ የነበረውን ህብረተሰብ ያላማከለ ነው መተቸታቸው አይዘነጋም።

በተጨማሪም በ1997 ተመዝግበው ከስቱዲዮ እስከ ባለሦስት መኝታ ቤት ድረስ ቤቶች ለማግኘት እየቆጠቡ ያሉ 959 ነዋሪዎች፣ ምን ያህል እንደቆጠቡ የሚገልጽ ሙሉ ስማቸው ከፊርማቸው ጋር ያረፈበትና በድምሩ 144 ሚሊየን 820 ሺህ 085 ብር መቆጠባቸውን ከሚያሳይ ሰነድ በማያያዝ፣ ኮርፖሬሽኑ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን ለመሸጥ የጀመረውን ሒደት እንዲያሳግድላቸው የሚጠይቅ ደብዳቤ ለዕንባ ጠባቂ ተቋም ጨረታው ይፋ በተደረገበት ዕለት ማስገባታቸውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ገልጿል።

አቤቱታቸውን የተቀበለው ዕንባ ጠባቂ ተቋም የካቲት 22 ቀን 2016፣ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በሰባት የሥራ ቀናት ውስጥ ምላሹን እንዲያሳውቀኝ በማለት በጻፈው ደብዳቤ፤ ኮርፖሬሽኑ የመኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ በሽያጭ የማስተላለፍ ሕጋዊ መሠረት ያለው ስለመሆኑ በማስረጃ ተደግፎ እንዲቀርብ ጠይቋል። ኮርፖሬሽኑ ስለጨረታው ማብራሪያ እንዲሰጥ ጥያቄ አቅርቧል።

እንዲሁም መኖሪያ ቤቶቹ በጨረታ ለሽያጭ ሲቀርቡ የ1997 እና የ2005 የጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝጋቢዎችን ቅድሚያ በመስጠት፣ በልዩ ሁኔታ ተሳታፊ ያልተደረገበት ምክንያት ግልጽ እንዲደረግ፣ ቤቶችን በጨረታ ለመሸጥ ሲወስን ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው የከተማው ነዋሪዎችን አቅም ባገናዘበ መንገድ የጨረታ መነሻ ዋጋና የአከፋፈል ሥርዓት ሊታይ አለመቻሉ ሌላው ጥያቄ መሆኑንም የዕንባ ጠባቂ ተቋሙ ጠቅሷል። 

ይኽ የጨረታ ማስታወቂያ ይፋ ከሆነ ጀምሮ በርካታ የጋራ መኖሪያ ቤት ለማግኘት የቆጠቡ እና እየቆጠቡ የሚገኙ ነዋሪዎችን አስቆጥቷል።

በተመሳሳይም ለኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ባቀረቡት አቤቱታም “የከተማ አስተዳደሩ እያደረሰብንና እያለፍንበት ያለውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሞራላዊ ምስቅልቅልና ተስፋ አስቆራጭ ቤት የማግኘት ችግር ተቋቁመን፣ እስካሁን ይሁንታ እየተጠባበቅን በመሆኑ፣ የከንቲባ ልዩ ጽሕፈት ቤት የመፍትሔ ምላሽ ይስጠን” ሲሉም መጠየቃቸው አይዘነጋም።

ይህ “እኛን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዳ ስለሆነ፣ በእናንተ በኩል ይህንን እንድታስቆሙልንና ቤቶቹ ለእኛ ለሕጋዊ ተመዝጋቢ ጠባቂዎች እንዲተላለፍ እንዲወሰንልን” ሲሉ ጥያቄያቸውን በጽሑፍ አቅርበው ነበር።

ይሁን እንጂ አቤቱታው በቅረበበት እንዲሁም ኮርፖሬሽኑ ቤቶችን ገንብቶ በሽያች ማስተላለፍ የሚችልበት ሕጋዊ መሰረት ጥያቄ ምላሽ ባላገኘበት ሁኔታ፤ የሰነድ ግዢው ተጠናቆ በይፋ መከፈቱን አዲስ ማለዳ ተረድታለች።

Source: Link to the Post

Leave a Reply