የመሰረተ ልማት አውታሮች ማርጀት እና የኃይል ስርቆት ከፍተኛ የኃይል ብክነት እያደረሰ እንደሆነ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የመሰረተ ልማቱ ማርጀት እና ከፍተኛ ኃይል መሸከም ብክነትን እንደሚፈጥር ለአሐዱ የገለጹት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ ኔትወርኩ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች እና ውድመቶች እንዲሁም ስርቆቶች ለብክነቱ ተጠቃሽ ምክንያቶች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

ኃይልን በአግባቡ መጠቀም አለመቻል አሁንም የሚስተዋል መሰረታዊ ችግር መሆኑን ያነሱት አቶ መላኩ ደረጃቸውን ያልጠበቁ እቃዎች ከፍተኛ ለሆነ የኃይል ብክነት ምክንያት እንደሆኑ አንስተዋል፡፡

በቤት ውስጥ የኃይል አጠቃቀም ሰዓትን አለመለየት ሌላው የኃይል ብክነትን እያመጣ ያለ ችግር ነው ያሉ ሲሆን ጉዳቱ በተቋሙ ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን ተጠቃሚውንም ለከፍተኛ ወጪ የሚዳርግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ ኔትወርክ የማሻሻል እና የመልሶ ግንባታ ስራ በስፋት እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰው በአዲስ አበባ እና ዙሪያው ባሉ አካባቢዎች ሶስተኛው ምዕራፍ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ማሻሻያው ሊደረግላቸው ከታቀደባቸው የክልል ከተሞች ከአዲግራት ውጪ በሁሉም አካባቢዎች በስፋት ግንባታው እየተከናወነ እንዳለ ገልፀው አዲስ የሚገነቡት መሰረተ ልማቶች የኃይል ብክነቱን ሊቀንሱት እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡

ቀን 05/12/2013

አሐዱ ራድዮ 94.3

Source: Link to the Post

Leave a Reply