የመንግሥት መዋቅሩን ጨምሮ የጅምላ ጭፍጨፋው ተሳታፊዎች በሙሉ ከተጠያቂነት አያመልጡም!…

የመንግሥት መዋቅሩን ጨምሮ የጅምላ ጭፍጨፋው ተሳታፊዎች በሙሉ ከተጠያቂነት አያመልጡም! ሕዳር 27 ቀን 2015 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ፣ ባህርዳር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት፣ መኢአድ እና ኢሕአፓ ፓርቲዎች የተሰጠ መግለጫ በታሪክ ድርሳናት ተመዘግቦ እንደምናገኘው በዓለም ላይ የተፈጸሙ የዘር ፍጅት… ክስተቶች አብዛኞቹ ወይም ኹሉም ሊባል በሚቻል መልኩ የመንግስት መዋቅር ቀጥተኛ ይኹንታ ወይም የእጅ አዙር ድጋፍ ወይም ባላዬ ማለፍ /by omission or commission/ የነበራቸው ናቸው፡፡ በቅርቡ የተከሰተው የሮሂንጋ ሙስሊሞች ጭፍጨፋ፣ የዳርፉሩ ጭፍጨፋ፣ የሩዋንዳው ዘር ፍጅት፣ የአይሁድ የጅምላ ጭፍጨፋ(Holocaust)፣ ኦቶማን ቱርኮች በአርመኖች ላይ የፈጸሙት ዘርፍጅት፣ ጀርመኖች በሄሬሮ/Hereros/ እና ናማ/Nama/ ጎሳዎች ላይ የፈጸሟቸው ጅምላ ጭፍጨፋዎች ጥቂት ማሳያዎች ናቸው፡፡ ገዳዮች ለፍጅቱ ሲያመቻቹ ሟቾችን ከሰውነት ጭምር በማሳነስ በረሮ/Cockroach/ እስከማለት ደርሰዋል፡፡ መንግስት ነው ላለማስባል ምርጡ ዘር (የአርያን ዘር) ነን እስከማለት ራሳቸውን በተለያየ ስያሜ ጠርተዋል፡፡ መደምደሚያው ግን የደም ምድር፣ የሬሳ ክምር ነው፡፡ እነዚሁ ድርሳናት በውል የሚነግሩን አንድ ታላቅ ቁምነገር ግን አለ፤ እሱም በ1948ቱ በተባበሩት መንግስታት ድንጋጌ/Convention/ እንዲህ ያለው አደገኛና የመጨረሻው ጭካኔያዊ ድርጊት ከሀገር ውስጥ አልፎ በዓለምአቀፍ ፍርድ ቤት የሚያስጠይቅ ወንጀል መሆኑን ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል በወለጋ ዞኖች በተደጋጋሚ ጊዜ ላለፉት አራት ዓመታት የአማራ ማንነት ባላቸው ዜጎቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ወንጀል፣ ማፈናቀል፣ የንብረት ዘረፋና ውድመት በመንግሥት መዋቅር ድጋፍ የተፈጸመ ለመሆኑ የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ጭፍጨፋው ለተወሰኑ ጊዜያት የዳቦ ስም በተሰጠው “ኦነግ ሸኔ” ተፈጸመ ቢባልም እያደር ምሥሉ እየጠራ፣ ጭምብሉ እየወለቀ ሲሄድ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ጭምር ግንባር ቀደም ተሳታፊነት ያለበት መሆኑ እየታዬ ነው፡፡ ከዚህ ዘለል ሲልም እስከአሁን ድረስ መንግሥት በኦሮሚያ ክልል ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጭፍጨፋዎችን ማስቆም ያለመፈለጉ፣ በቅጡ እንኳን በማውገዝ ለፍጅቱ እውቅና ያለመስጠቱ፣ ማድበስበሱና በጥቂቱም ቢሆን የሕግ ተጠያቂነት ያለመኖሩ የመንግሥት መዋቅር እጁ እንዳለበት ከበቂ በላይ ማሳያ ይሆናል ብለን እናምናለን። የአማራ ማንነት ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በጠላትነት ተፈርጆ ዘሩ ከምድረ ገፅ እንዲጠፋ ያልተፈነቀለ ድንጋይ፣ ያልተወረወረ የጥፋት ቀስት ባይኖርም ባለፉት አራት ዓመታት በማንአለብኝነት የሆነውን ያህል ግን ተፈጽሟል ብለን አናምንም። ምንም እንኳን የድርጊቱ ቀጥተኛ ሰለባ በጠላትነት የተፈረጀው የአማራ ማኅበረሰብ ቢሆንም ጭፍጨፋውን የሚቃወሙ፣ “ተው አይበጅም” እያሉ የጮኹ የኦሮሞ ማንነት ያላቸው ዜጎቻችንም ከእልቂቱ አልተረፉም፡፡ ይባስ ብሎ በጨለማ የ“ሸኔ” ቡድን ለመንግስት መረጃ ሰጥታችኋል በሚል፣ በቀን ደግሞ መንግስት “ሸኔን” ደግፋችኋል በሚል ሰበብ በኹለት ቢላዋ እየታረዱ ይገኛሉ፡፡ በቡሃ ላይ ቆረቆር እንዲሉ አንዱ ሌላውን እየደበቀና “ተው ከእርሱ በፊት እኔን አስቀድሙ” እየተባባለ ያለውን የጠነከረ የትሥሥር ገመድ ለመበጠስና ከለላ ለማሳጣት በማሰብ ኹኔታው ወደ እርስ በእርስ ጦርነት እንዲቀየርና ተጋብቶና ተዋልዶ፣ ደስታና ሀዘኑን ሲጋራ የኖረውን ማኅበረሰብ ለማጋጨት እጅግ አደገኛ ሴራ እየተሸረበ ይገኛል፡፡ ከሰሞኑ የደም ምድር እየሆነ የመጣው የምሥራቅ ወለጋ ዞን፣ በኪረሙ፣ ጊዳአያና እና ሀሮ አካባቢዎች እጅግ የሚሰቀጥጡ ፍጅቶች የተከናወኑ ሲሆን በመቶዎች ሞተዋል፣ በሺዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት ወድሟል፡፡ እንደ አካባቢው ነዋሪዎች ገለጻ በቅርቡ በጉትን ቀበሌ የክልል የጸጥታ ኃይል ደንብ ልብስ የለበሱ ናቸው የተባሉ ኃይሎች ተሠማርተው በንጹሓን ላይ የፈጸሙት ድርጊት እጅጉን አሳዝኖናል፡፡ ኹሉም እንደሚያውቀው ዜጎች መንግሥት የሚያቋቁሙት ለሦስት ዋና ዓላማዎች ነው፤ በግል መከላከል ስለማይችሉ መንግሥት ሰራዊት አቋቁሞ ዳር ድንበር እንዲጠብቅ፣ የፓሊስ ሰራዊት አቋቁሞ ጉልበተኛ ደካማውን እንዳያጠቃ ለመከላከል፣ ጉልበተኛ ደካማውን ካጠቃ ደግሞ ይዞ ፍርድ ቤት ለማቅረብና ለመቅጣት ነው፡፡ ሆኖም ከዚህ በተቃራኒው ከሠራ “ለስሙ አለን እንጂ መንግሥት አልባ ነን” ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ከላይ ስማችን የተጠቀሰው ፓርቲዎች እንዲህ ያለውን ጭካኔ የተሞላው ተግባር በጽኑ እያወገዝን የሚከተሉትን ምክረ ሀሳቦች ለማቅረብ እንወዳለን፡፡ -በክልሉ በማናለብኝነት የቀጠለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል እና ግብታዊ ግድያ ማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ኹሉ በስሙ ጠርቶ ሊያወግዘውና ከተጠቂው አማራ እና የግድያው ሰላባ ከሆኑ የኦሮሞ ማንነት ያላቸው ወገኖቻችን ጎን በመቆም ድምፅ እንዲሆናቸው ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። -በዚህ ዘግናኝ ጭፍጨፋ የተሳተፉ የትኛውም ኃይሎች በአስቸኳይ ለሕግ እንዲቀርቡ አበክረን እንጠይቃለን፡፡ -ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ በተዛባ የፖለቲካ ትርክት እርስ በእርሳችን ተከፋፍለንና “በእኛና እነርሱ” ጎራ ለይተን እንድንጫረስ የተፈጸመውን የፖለቲካ ቁማር በመገንዘብ የሕዝብ ለሕዝብ ትምምንና እርቅ በመፍጠር ጥፋተኛ ኃይሎችን በጋራ ለፍርድ አደባባይ እንድናቀርባቸው ጥሪ እናቀርባለን። -ክልሉን የሚያስተዳድረው የኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ብሎም ፌዴራል መንግስት እየሆነ ባለው ጉዳይ ዙሪያ ግብር ከፍሎ ደመወዝ ለሚቆርጥለት የክልሉ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሕዝብ በአስቸኳይ እየተደረገ ባለው ጭፍጨፋ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጥ በጽኑ እንጠይቃለን። -ዘላቂ ሰላም እስኪሰፍን ድረስ አካባቢው በኮማንድ ፖስት ሥር እንዲተዳደር፣ መከላከያም አካባቢውን እንዲቆጣጠር አበክረን እንጠይቃለን። -ፍጅቱ እንዲፋፋም፣ መልኩን እንዲቀይርና በቀጥታም ጭምር በመሳተፍ ለንጹሓን እልቂት ምክንያት እየሆናችሁ ያላችሁ ባለስልጣናትና ሌሎች አካላት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስጠይቅ ወንጀል እየሠራችሁ መሆኑን አውቃችሁ ከእኩይ ድርጊታችሁ እንድትታቀቡ እናሳስባለን፡፡ -የሚዲያ ተቋማት፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን፣ ሲቪክ ማኅበራት ኹሉ ላለፉት አራት ዓመታት ያለማቋረጥ በወለጋ እንዲሁም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ንጹሓን ወገኖቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን የተቀናጀ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንድታወግዙና ስለዘላቂ መፍትሔውም አበክራችሁ እንድትሠሩ በአጽንዖት እንጠይቃለን። በመጨረሻም በጭፍጨፋው ሕይወታቸውን ላጡ ኹሉ ወገኖቻችን የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን በድጋሚ እየገለጽን ለቤተሰቦቻቸው እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን እንመኛለን። ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ መኢአድ፣ እናት እና ኢሕአፓ ፓርቲዎች ሕዳር ፳፯ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች አሻራ ሚዲያ የአይበገሬዎቹ ልሳን:-Youtube:- https://www.youtube.com/…/UCPmgFzP2ZPmdGjHxXjigJ…/Facebook:- https://www.facebook.com/asharamedia24ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedia24

Source: Link to the Post

Leave a Reply