
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግሥት የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ አካል ጉዳተኞችን ያሳተፈና ልዩ ትኩረት የሰጠ መሆኑን የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ ገለጹ።
መንግሥት በተለያዩ ዘርፎች የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ አውጥቷል፣ በእቅዱ ዝግጅት ላይ የሚመለከታቸውን አካላት ሲያወያይም መቆቱን ገልጸው፤ በተዘጋጀው የ10 ዓመት መሪ እቅድ አካል ጉዳተኞችን ያሳተፈ በመሆኑ እኩል ተሳታፊነትን እንደሚያረጋግጥ አቶ አባይነህ ገልጸዋል።
የፕላንና ልማት ኮሚሽን የ10 ዓመት መሪ እቅድ ሲያዘጋጅም አካል ጉዳተኞች ማህበራት ጋር ሰፊ ውይይት ማድረጉን አስታውሰዋል።
በውይይቱም የትምህርት ተደራሽነት እንዲስፋፋ፣ አካል ጉዳተኞች ከሌላው ማህበረሰብ ጋር እኩል እድል አግኝተው እንዲማሩና የስራ እድል በሚያገኙበት ሁኔታ ላይ ምክክሮች መደረጉን ገልጸዋል።
“በቀጣይም የታቀዱና ውይይት የተደረገባቸው ጠቃሚ ጉዳዮች ወደ ተግባር እንዲለወጡ የሁሉንም ጥረት ይጠይቃል” ብለዋል።
የአካል ጉዳተኞች የስራ ስምሪት አዋጅም በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆን መንግስትና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ልዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
አሰሪዎች ለአካል ጉዳተኞች የስራና የስልጠና አካባቢን የማመቻቸትና ተስማሚ የሆኑ የስራ ወይም የስልጠና መሳሪያዎችን የማሟላት ሃላፊነት እንዳለባቸው በአዋጁ መካተቱንም ነው የጠቀሱት።
“የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል” ያሉት አቶ አባይነህ፤ መንግስት አሁን እየሰጠ ያለው ትኩረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ማመልከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
The post የመንግሥት የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ አካል ጉዳተኞችን ያሳተፈና ልዩ ትኩረት የሰጠ መሆኑ ተገለጸ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.
Source: Link to the Post