የመንግስት ህግ የማስከበር ሀላፊነት ጥያቄ ውስጥ መግባቱ አሳስቦኛል -ኢዜማ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2014 የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ኢዜማ ፓርቲ መንግስት የህግ የበላይነትን የማስከበር ሃላፊነቱ ከዕለት ዕለት ጥያቄ ውስጥ እየገባ መምጣቱ በብርቱ አስግቶኛል አለ።
ፓርቲው ይህን ያለው በቄለም ወለጋ በንጹሀን ዜጎች ላይ የደረሰውን አሰቃቂ ግድያ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ነው፡፡

ኢዜማ “በድንገት መጥቶ ህዝብን ከሚያጠቃው እኩይ አካል እኩል ዜጋውን የመጠበቅ ግዴታ ኖሮበት የማይጠብቀው መንግስት ተጠያቂ ነው” በሚል ርእስ ባወጣው በዚህ መግለጫ በንጹሀን ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ መፈጸሙ እጅግ አሳዝኖናል ብሏል። ማንነትን መሰረት አድርገው የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለማስቆም መንግስት ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ በተደጋጋሚ ሲያሳስብ መቆየቱን ፓርቲው ገልጿል፡፡

ሆኖም መንግስት ማሳሰቢያዎችንም ሆነ ምክረ ሀሣቦቻችንን ለመቀበል ምንም አይነት ፍላጎት አላሳየም ሲልም በመግለጫ አመላክቷል። መንግስት፣ ታጣቂ ሀይሎች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ተከትሎ እየሸሹ የነበሩት ታጣቂዎች የፈጸሙት እንደሆነ ገልጿል። ይሁን እና እንዲህ አይነት እርምጃዎች ሲወሰዱ ታጣቂ ሀይሎች በሽሽት ላይ ምን አይነት ጉዳት ሊያደርሱ እንደሚችሉ ካለፉ ልምዶች በመማር የዜጎችን ነፍስ ለመታደግ የሚያስችሉ ተግባራትን በቁርጠኝነት ባለመተግበሩ ተጠያቂ ያደርገዋል ነው ያለው።

መንግስት በተለይም በወለጋ አካባቢ በዚህ ደረጃ ለምን የጸጥታ ችግሮችን መቆጣጠር እንደተሳነው ለሕዝብ በግልጽ የማሣወቅ ግዴታ ያለበት ከመሆኑም በተጨማሪ ዘላቂ መፍትሔዎችን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር መስራት እንዳለበት አጥብቀን ማስገንዘብ እንወዳለን ሲልም መግለጫው አትቷል። ይህ መፍትሄ የጊዜ ገደብ ወጥቶለት አካባቢውን ከመሠል ጥቃቶች በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ነፃ እንደሚያወጣ በይፋ በመግለጽ መንግስት ለዜጎች ደኅንነት መጠበቅ ምን ያህል ቁርጠኛ እንደሆነና መንግስታዊ የማስፈጸም አቅም እንዳለው ሊያሳይ ይገባልም ብሏል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply