የመንግስት ወታደሮች በጤናው ዘርፍ ያደረሱት ጉዳት በጦር ወንጀል ሊያስከስስ የሚችል ነው ተባለ 

ረቡዕ ሰኔ 26 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል ለአንድ ዓመት ገደማ በተካሂደውና አሁንም በቀጠለው ግጭት ምክንያት በክልሉ ባሉ የህክምና መስጫ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት እየደረሰ መሆኑን ሂዩማን ራይትስ ዋች ገለጸ።

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ባወጣው ሪፖርት በአማራ ክልል ካለው ግጭት ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ወታደሮች ለፋኖ ተዋጊዎች ህክምና ተሰጥቶበታል በሚል በሆስፒታል፣ በአምቡላንስ፣ በህክምና ባለሞያዎች እና በታካሚዎች ላይ እንግልት እና ግድያ ፈጽመዋል ተብሏል።

የህክምና ሰራተኞችን በየጊዜው ማዋከብ፣ ማስፈራራት እና ሆስፒታሉን እንዲሁም የሆስፒታሉን ሰራተኞች መኖሪያ ቤት ደጋግመው በመከታተል ስጋት መፍጠር እንደጀመሩም ሪፖርቱ ይገልጻል።

በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙት የአዊ ዞን፣ ሰሜን ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃም፣ ሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር እና ደቡብ ወሎ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 13 ከተማዎች በተደረገው ጥናት የመንግስት ኃይሎች ሰብዓዊ ድንጋጌዎችን እና የጦር ህጎችን ጥሰዋል ተብሏል።

ሪፖርቱ እንደሚለው በጤና ባለሙያዎቹ ላይ ከፋኖ ጋር ግንኙነት አላችሁ በማለት የስልክ ማስፈራሪያ እና ዛቻ ይደርስባቸዋል። በአማራ ክልል በርካታ ዶክተሮች፣ ነርሶች እና ሌሎች የጤና ባለሙያዎች ላለፉት ሶስት አመታት፣ የሰሜን ኢትዮጵያ የትጥቅ ግጭት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሁለቱም የኢትዮጵያ መንግስት ኃይሎች እና መንግስታዊ ያልሆኑ ታጣቂ ቡድኖች በጤናው ዘርፍ እና በህክምና ተቋማት ላይ ያሉ ሌሎች ሰዎችን በተደጋጋሚ ኢላማ ማድረጋቸው ተመላክቷል።

የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች፣ ፖሊስ እና ሚሊሻን ጨምሮ  የጸጥታ አካላቱ የጤና ሰራተኞችን እና ታማሚዎችን ገድለዋል፤ ዶክተሮች ላይ ዛቻ እና ጥቃት ፈጽመዋል፤ ህሙማንን አላግባብ አስረዋል፤ የህክምና ቁሳቁሶችን ዘርፈዋል እና አውድመዋል፤ የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን አላግባብ ተጠቅመዋል መባሉን አዲስ ማለዳ ከሪፖርቱ ተመልክታለች።

በተጨማሪም በተደጋጋሚ ወደህክምና ተቋማት ድንገት በመግባት በተለይም በጥይት ተኩስ፣ ፍንዳታ ወይም መሰል የጥቃት ቁስል ያለባቸው ታካሚዎችን በውጊያ ውስጥ በመሳተፍ ወይም ከፋኖ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ይደመድማሉ ተብሏል።

“በጦርነቱ ምክንያት ብዙ የተጎዱ ሰዎች አሉ፤ ነገር ግን በሆስፒታል አገልግሎት ማግኘት አልቻሉም። ምክንያቱም መንግስት አንድ ሰው በጥይት ወይም በመሳሪያ ተጎድቶ ካየ ፋኖ እንደሆነ አድርጎ ይቆጥረዋል” ሲል በደቡብ ጎንደር ዞን የሚገኝ የህክምና ባለሞያ ለሂዩማን ራይትስ ዋች ተናግሯል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ 58 ቃለ-መጠይቆችን እንዲሁም የሳተላይት ምስሎችን እና የተረጋገጡ ቪዲዮዎችን እና ፎቶግራፎችን መጠቀሙን አስታውቋል። በተጨማሪም በአምቡላንስ ላይ የተፈጸመ አንድ የድሮን ጥቃትን መመርመሩ ተገልጿል።

በምዕራብ ጎጃም፣ ምስራቅ ጎጃም፣ ደቡብ ጎንደር እና ሰሜን ሸዋ እና ደቡብ ወሎ ዞኖች የመንግስት ታጣቂዎች እና የፋኖ ታጣቂዎች በከተሞች በሚያደርጉት ተደጋጋሚ ግጭት መንገዶችን በመዘጋታቸው ምክንያት ማህበረሰቡ በቤቱ፣ በሆስፒታል ቅጥር ግቢ አልያም በህዝብ እና በህክምና መጓጓዣ ውስጥ ተገድለው እና ቆስለው ይገኛሉ ተብሏል።

በመሆኑም ውጊያው የህክምና አቅርቦቶችን፣ ሆስፒታሎችን እና የጤና አጠባበቅ ማዕከላትን ከማውደም ባለፈ አጣዳፊ እና ለረዥም ጊዜ አስፈላጊ የሆኑ መድሃኒቶች እና ሌሎች አስፈላጊ የጤና አጠባበቅ እቃዎች አቅርቦትን አቋርጧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የጎደሉ የሆስፒታል አቅርቦቶችን ለመሙላት የሚፈልጉ ባለሞያዎች በመንግስት ሃይሎች በጥርጣሬ የሚታዩ በመሆኑና አንዳንዴም ጥቃት በመድረሱ ለታካሚዎች ደህንነቱ በተጠበቀ አካባቢ እንክብካቤ የመስጠት አቅማቸው ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል ተብሏል።

በተጨማሪም በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት ምክንያት የአስተዳደር መዋቅሮች መፈራረስ፤ ገንዘብ ወደ ጤና አጠባበቅ አቅራቢዎች እንዳይደርሱ በማድረግ ለአስፈላጊ መድሃኒቶች እና የህክምና መሳሪያዎች እጥረት አስተዋጽኦ አድርጓል።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በአማራ ክልል ውስጥ እየተካሄደ ባለው ጦርነት የግጭት አባባሾችን እያበረታታ በደል የፈጸሙትን የፌዴራል እና የክልል ሃይሎችን ተጠያቂ ለማድረግ ምንም አይነት ትርጉም ያለው እርምጃ እንዳልወሰደ ተገልጿል።

በአማራ ክልል ሆስፒታሎች እና ሌሎች የጤና እንክብካቤ መስጫ ጣቢያዎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃትን እንዲቆም እና የህክምና ባለሙያዎች ለሲቪል እና ወታደራዊ ታማሚዎች ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ እንዲያገለግሉ እና የህክምና ቁሳቁስ እና ሰብአዊ እርዳታ ወደ ህክምና ተቋማት እንዲደርስ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

በተጨማሪም ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ አካላት በተለይም የአፍሪካ ህብረት እና የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎችም የሚመለከታቸው መንግስታት በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ እንደገና እንዲጣራ በአስቸኳይ ማሳሰብ አለባቸው ተብሏል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply