የመከላከያ ሰራዊት “ከየትኛውም አቅጣጫ የሚሰነዘርበትን ጥቃት” ለመመከት “ዝግጁ” መሆኑን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት “ከየትኛውም አቅጣጫ የሚሰነዘርበትን ጥቃት” ለመመከት፤ ዝግጁ የሆነበት “ደረጃ” ላይ እንደሚገኝ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ። ኢትዮጵያ “በሰላማዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት ጥረት እያደረገች ያለችበት ነው” ባሉት በዚህ ወቅት፤ የሀገሪቱ “ታሪካዊ ጠላቶች” የውስጥ ችግሮችን ለማባባስ “የቋመጡበት እና የቆረጡበት” መሆኑንም አስታውቀዋል። 

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ይህን ያሉት፤ የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ በሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ለ24ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን መኮንኖች ትላንት ቅዳሜ ጥር 25፤ 2016 ባስመረቀበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ነው። “አንድነት” የሚል ስያሜ የተሰጠው የዘንድሮ ተመራቂዎች ስብስብ፤ “የካበተ የውጊያ ልምድ እና ተሞክሮ ያላቸውን” መኮንኖች የያዘ መሆኑ ከዚህ ቀደም ከነበሩት “ልዩ” የሚያደርገው መሆኑ በስነ ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

እነዚህ ተመራቂዎች ከተጨማሪ ስልጠና በኋላ ወደ መከላከያ ሰራዊቱ የሚመለሱበት የአሁኑ ወቅት፤ ኢትዮጵያ “ከቀይ ባህር ተገፍታ በመቆየቷ የደረሰባትን የኢኮኖሚና የጸጥታ ተግዳሮቶችን እና ስብራቶችን” ለመቅረፍ “እየሞከረች” ያለችበት መሆኑን ልብ ሊሉት እንደሚገባ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ አሳስበዋል። ይህ ሙከራ እንዳይሳካ፤ የኢትዮጵያ “ታሪካዊ ጠላቶች” የሀገሪቱን የውስጥ ችግር “ለማባባስ” “የቋመጡበት እና የቆረጡበት ጊዜ [ነው]” ሲሉም ተደምጠዋል። 

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ የኢትዮጵያን ዕድገት “በበጎ የማይመለከቱ” እና “ታሪካዊ ጠላቶቻችን” ሲሉ የጠሯቸውን ኃይሎች በስም ባይጠቅሱም፤ “አሁንም ኢትዮጵያን ለማዳከም የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ግልጽ [ሊሆንላቸው] ይገባል” ሲሉ አጽንኦት ሰጠዋል። እነዚህ ኃይሎች “ከማንኛውም የኢትዮጵያ ጠላት ጋር ከመሰለፍ ወደ ኋላ የማይሉ የውስጥ ባንዳዎችን በማጠናከር” ኢትዮጵያን “ለማተራመስ ሲንቀሳቀሱ” መቆየታቸውንም በንግግራቸው አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ “አንድ ሆና ቆማ ከውጪ የሚመጣ [ጥቃት] ካለ ለመመከት የሚያስችል ቁመና እንድትይዝ” በትላትናው ዕለት የተመረቁት መኮንኖች “ኃላፊነት” እንዳለባቸው ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ አስገንዝበዋል። በዚህ ረገድ መኮንኖቹ የሀገሪቱን “ጸጥታ የማስተካከል” ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸው አሳስበዋል። 

በመከላከያ ሰራዊት በኩል “ከየትኛውም አቅጣጫ የሚሰነዝርን ጥቃት” ለመመከት፤ “ዝግጁ የሆነበት” እና “እየሆነ ያለበት ደረጃ ላይ” እንደሚገኝ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በትላንቱ ንግግግራቸው አስታውቀዋል። ሰራዊቱ “ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ” ራሱን ማጠናከሩንም አክለዋል። የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሀገሪቱ ከዚህ ቀደም ያልነበራትን ራሺያ ሰራሽ “ሱ- 30” የተሰኘ ተዋጊ ጀት  እና  ከቱርክ የመጡ ስትራጄቴካዊ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) መረከቡን ከሶስት ሳምንት መረከቡን ማስታወቁ አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)    

Source: Link to the Post

Leave a Reply