የመወለጃ ጊዜያቸው #ሳይደርስ የሚወለዱ ህጻናት

በፈረንጆቹ 2020 ላይ በተሰራ ጥናት በዓለማችን 13.4 ሚሊዮን ህጻናት ያለግዜያቸው መወለዳቸውን የተጠናው ጥናት ውጤት ያመለክታል፡፡

በኢትዮጵያ ከሚወለዱ ህፃናት ደግሞ 11 በመቶ የሚሆኑት ያለግዜያቸው የሚወለዱ መሆናቸውን መረጃወች ያሳያሉ፡፡
ይህም የጨቅላ ህፃናትን ሞት እንዲጨምር ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ እንደሆነ ይነገራል፡፡

ያለግዜ መወለድ በፅንሱ ፣በእናቲቱ ወይም በሁለቱም ችግሮች ምክንያት ሊከሰት እንደሚችሉ ባለሙያዎች ያነሳሉ፡፡
ከ5 አመት በታች ለሆኑ ህፃናት ቀዳሚ የሞት መንስኤ ያለግዜያቸው መወለድ መሆኑንም ጥናቶች ያመለክታሉ ፡፡
በዚህ ጉዳይም ሙያዊ ማብራሪያ እንዲሰጡን የህፃናት እና የጨቅላ ህፃናት ሀኪም ከሆኑት ዶ/ር ገስጥ መታፈሪያ ጋር ጣቢያችን ቆይታ አድረጓል፡፡

አንድ ህፃን ያለግዜው ነው የተወለደው ስንል ምን ማለት ነው ?

አንድ ልጅ ግዜውን ጠብቆ ተወለደ ብሎ ለመናገር ከተፀነሰበት ግዜ ጀምሮ 37 ሳምንት እና ከዛ በላይ ሆኖት የሚወለድ ከሆነ በግዜው ተውልዷል ማለት ይቻላል ፡፡
ያለግዜያቸው ተወለዱ የሚባሉት ደግሞ መወለድ ከነበረባቸው ከ37 ሳምንት በፊት የሚወለዱ ከሆነ ያለግዜያቸው ተወልደዋል ብለን መናገር እንችላለን ይላሉ ባለሙያው፡፡

መንስኤዎቹ ምንድን ናቸው ?

 • ፅንስ ውስጥ እያለ ለእድገቱ ምቹ ሁኔታዎች ከሌሉ ምጥን የማፋጠን ባህሪ ሊያጋጥም ይችላል፡፡
 • የአፈጣጠር ሁኔታ( አፈጣጠራቸው ላይ ችግር ካለ)
 • ከእናትየዋ ጤንነት ጋር ወይም ከማህፀኗ አፈጣጠር ጋር ተያይዞ የሚመጣ
 • የማህፀን ኢንፈክሸን
 • ደም ግፊት
 • ከእንግዴ ልጁ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የሚችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሚያስከትለው ጉዳት ምንድን ነው?

ከ 37 ሳምንት በፊት የሚወለዱ ልጆች ሁሉም አንድ አይነት የጤና እክል ይገጥማቸዋል ማለት እንዳልሆነ ዶ/ር ገስጥ ይናገራሉ።

 • ከ28 ሳምንት በፊት የሚወለዱ ህፃናት ከሌሎቹ በይበልጥ እንደሚቸገሩ እና አብዛኛው የሰውነት ክፍላቸው ሳንባቸው ፣ልባቸው ፣ የአግጀት ክፍላቸው ፣ ኩላሊታቸው፣ የአእምሮ ሁኔታቸው ሁሉም ያልተስተካከለ ስለሚሆን የውጪውን ነባራዊ ሁኔታ የመላመድ ችግር ይገጥማቸዋል ።
 • ከ28 ሳምንት እስከ 32 ሳምንት ያሉት ደግሞ ከ28 ሳምንት በፊት እንደተወለዱት የከፋ ችግር ላያጋጥማቸው እንደሚችል አንስተዋል።

ከ34 ሳምንት እስከ 37 ሳምንት የሚወለዱ ልጆች የጎላ ችግር አያጋጥማቸውም ምክንያቱም አብዛኛው የሰውነት ክፍላቸው ዳብሮ እና ጎልብቶ የሚወለዱ ስለሆኑ በቀላሉ የውጪውን ነባራዊ ሁኔታ መላመድ ይችላሉ።
ሁሉም ሰው መገንዘብ ያለበት ነገር አንድ ልጅ ፅንስ ውስጥ አንድ ቀን እድሜ ጨመረ ማለት ቢያንስ የሞት እድሉን ከ 2 እስከ 4 % ሊቀንስልን ይችላል።

መፍትሄዎቹ ምንድን ናቸው ?

 • በቂ የሆነ የፅንስ ክትትል
 • በወሊድ ግዜ የሚደረጉ እንክብካቤዎች
 • በቂ የሆነ ኦክስጅን መስጠት
 • ከተወለዱ በኋላ የሙቀተ ሁኔታቸውን ማስተካከል
 • ማንኛዋም እናት ከወለደች በኋላ ከህጻኑ ጋር ገላ ለገላ ንክኪን ማበረታታት
 • የእናት ጡት ወተት በበቂ ሁኔታ መስጠት
 • ከማዋለጃ ክፍል ወደ ማሞቂያ ክፍል በሚሄዱበት ግዜ መደረግ ያለባቸውን እንክብካቤ ባለማቋረተጥ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቀነስ መሞከር ያስፈልጋል፡፡

በመጨረሻም አንድ እናት ችግሩን ቀድሞ ለመከላከል ነፍሰ ጡር ከመሆኗ በፊት የማህጸን ሃኪሞችን ማማከር እንደሚያስፈልግ እና ፅንሱ ከተፈጠረ በኋላም በበቂ ሁኔታ ክትትል ማድረግ እንደሚገባት አስረድተዋል፡፡

እንዲሁም ያለግዜያቸው የተወለዱ ህፃናት ሁሉም አደጋ ላይ እንዳይወድቁ በተቻለ መጠን አስፈላጊውን ህክምና እና ክትትል እንደሚያስፈልጋቸው ዶ/ር ገስጥ ተናግረዋል፡፡

በሐመረ ፍሬው

ሚያዝያ 04 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply