You are currently viewing የመዋቅራዊ ጥቃትና ጦርነቱ ሰለባ ለሆኑ ተፈናቃይ ወገኖቻችንን ሕዝቡ በአፋጣኝ ይድረስላቸው! ባህርዳር:- መጋቢት 07/2014 ዓ.ም                 አሻራ ሚዲያ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ…

የመዋቅራዊ ጥቃትና ጦርነቱ ሰለባ ለሆኑ ተፈናቃይ ወገኖቻችንን ሕዝቡ በአፋጣኝ ይድረስላቸው! ባህርዳር:- መጋቢት 07/2014 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ…

የመዋቅራዊ ጥቃትና ጦርነቱ ሰለባ ለሆኑ ተፈናቃይ ወገኖቻችንን ሕዝቡ በአፋጣኝ ይድረስላቸው! ባህርዳር:- መጋቢት 07/2014 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ በሀገራችን ሞትን እየተለማመድን አኹን አኹን እንዲያውም የሞተው ሰው ቍጥርና የአሟሟቱ የዘግናኝነት መጠን ያነጋግር ካልኾነ እንጂ የጅምላ ፍጅትና እልቂት የሚያስገርም አልኾነም፡፡ በተፈናቃይ ቍጥር በአንድ ወቅት “፩ኛ” እስከመውጣትም ደርሰናል፡፡ እንዲህ ያሉ አደገኛ ልምምዶች ምን እንደሚያመጡ ሳንውል ሳናድር እያስተዋልነው ገፈቱንም እየቀመስን ለመኾኑ አስረጅ አይሻም፡፡ ዘቅዝቀን ስንሰቅል፣ ሰው ታርዶ በደሙ ሲታጠብ፣ ልጇን አርደው ደሟን ገድበው ለእናት ሲያጠጧት፣ ቤት ተዘግቶ ሕጻናትና የአእምሮ ሕሙማን እንደጧፍ ሲነዱ፣… ዝም/ቸል በመባሉ ዛሬ ሰው ከነሕይወቱ እያገላበጥን መጥበስ ላይ ተደርሷል፡፡ ይህም ዝም ስለሚባል ነገ ምን እንደሚደረግ መገመት አያዳግትም፡፡ በቅርቡ በመቶዎች የሚቆጠሩ መድረሻ ያጡ ምሥኪን ኢትዮጵያውያን አንገት ማስገቢያ ጎጆ አጥተው እንደ ኳስ ከቦታ ቦታ ሲላጉ እያየን “ሃይ” ባይ ስላጣን ዛሬ መቶ ሺዎች በመዋቅራዊ ጥቃት ሰበብ አማራ ክልል፣ ፍኖተ ሰላምና አካባቢውን አጥለቅልቀዋል፡፡ ማዕበሉ ሲታይ በቤት አይደለም ሸራ ወጥሮ እንኳን ማኖር ከባድ ያደርገዋል፤ “…በእንቁላሉ በቀጣሽኝ” ነዋ፡፡ ዛሬ የሞቀ ቤቱን፣ ሀብት ንብረቱን ትቶ “ተፈናቃይ” የተባለው ማኅበረሰብ ትናንት በሰሜኑ ጦርነት ሀገር ማጥ ውስጥ ስትገባ ቤት ያፈራውን ከሳንቲም እስከ ሚሊዮኖች፣ ከዶሮ እስከ ሰንጋ በሬ የለገሰ ነበር፣ ዛሬ ግን ትናንት “ለግስ” እያሉ ያግባቡት ከቀዬው ሲፈናቀል አልደረሱለትም፤ በጥቂቱ ሲሰላ ደግሞ አንገታቸው ዞሮ አላይ ስላለ ዘነጉት፡፡ ይሄው የመከራ ገፈት ቀማሽ እየኾነ የመጣ ክልልና ነዋሪው ትናንት ትሕነግ በለኮሰችው እሳት ሲለበለብ፣ አርባ ሲገረፍ ከርሞ አኹን ደግሞ ቢያንስ “ከጦርነቱ አረፍ አልኩ” ሲል በሰሜን ወሎ ሰቆጣና ቆቦ አካባቢ እንደገና በስደተኛ ማዕበል እየተጥለቀለቀ ነው፡፡ ትግራይ ክልል ውስጥ ያለው ኹኔታ “በጌታው” ትሕነግ እየተመራ ወደምድራዊ ሲዖልነት በመቀየሩ ማኅበረሰቡ እግሩ ወዳደረሰው በገፍ መሰደድ በመጀመሩ አንዱ መዳረሻ ወንድሙ ወደኾነው ቆቦና ሰቆጣ ማኅበረሰብ ኾኗል፡፡ ከመሞት መሰንበት ነውና እንደ ትናንቱ ያለውን ተቃምሶ ሞት እንኳን ቢመጣ አብሮ መሞትን ስለሚያውቅበት ማኅበረሰቡ ካለው ሳይሆን ከሌለው ላይ እየቆነጠረ እንደሚዘልቅ እምነታችን ነው፡፡ ነገር ግን ይህ እዳ በዚያ የመከራ ጥግ ሲጠበስ ለኖረ ማኅበረሰብ ብቻ የሚተው እዳ ሊሆን አይችልም፤ የኹሉም ኢትዮጵያዊና የመላው ዓለም እንጂ! ብዙም ሳንርቅ እግራችንን ከቆቦ ወደአፋር ክልል ራመድ እንዳደረግን እንዲሁ ብዙ መቶ ሺዎች ተንጠልጥሎ በቀረው ጦርነት እየተጠበሱ ከሞቀ ቤታቸው “ተፈናቃይ” ሆነዋል፡፡ ስለኾነም ለእኒህ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ በአማራና አፋር ክልል በተለያየ አካባቢና ኹኔታ ውስጥ ያሉትን ወገኖች መላው ኢትዮጵያዊና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲታደጋቸው ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ ብንታደልና የሚማር መንግስት ቢኖረን ትናንት በማንነታቸው ሚሊዮኖች ከሦማሌ ክልል፣ በመቶ ሺዎች በጌዲዮና አማሮ አካባቢ፣ ሺዎች በኮንሶና ወለጋ፣… ቤት ንብረታቸው ትተው ሲሰደዱ ምክንያቱን አጥንቶ ዘላቂ መፍትሔ ሽቶ ዳግም እንዲህ ያለው ድርጊት እንዳይፈጠር ኹሉንም አማራጮች ይጠቀም ነበር፡፡ ይህ ግን የእኛ ምኞት እንጂ ትኩረትና የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጠው አልቻለም፡፡ ይባስ ብሎ ሞትና ስደትን እየተለማመድን፣ ምንም እንዳልተፈጠረ የሚያስመስሉ የድግስ አበላና የዳንኪራ ጋጋታ ማየት ይዘናል፡፡ ምን አልባት እንጥፍጣፊ ሰውነት የቀራችሁ የተዋረድ አመራሮች ብትኖሩ ከእነዚህ በሀገራቸው ሀገር አልባ የሆኑ ዜጎቻችን ጉዳይ የሚቀድም የለምና ሰላምና ጸጥታውን አስጠብቆ ወደቀያቸው መመለስን ጨምሮ ባሉበት ሰውነት እንዲሰማቸው ማደረግ ትችሉ ዘንድ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ በሌላ በኩል በስደት ከትግራይ የሚመጡ ምሥኪን ወገኖቻችንን የክፋት አባት የኾነው ትሕነግና መሰሎቹ ለእኩይ ዓላማቸው ለመጠቀም እንዳይችሉ መከላከልን ጨምሮ በጥንቃቄ ሂደቱን መምራትና ሀገርና ወገን አለኝ ብለው ሲመጡ ፍቅር ሰጥቶ፣ ክብካቤ አድርጎና ስንቅ ቋጥሮ ሰላሙ ተመልሶ ለቤታቸው እንዲበቁ ማስቻሉን የኹላችንንም ርብርብ የሚሻ ዐቢይ ተግባር ነው፡፡ እኒህ ወገኖቻችንን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉትን እንደኹልጊዜው የመረዳዳት መንፈስ መላው ኢትዮጵያዊ የአቅሙን እንዲያደረግና እንዲታደጋቸው ፓርቲያችን ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ እናት ፓርቲ መጋቢት ፯ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች የአይበገሬዎቹ ልሳን:- ቴሌግራም :- https://t.me/asharamedia24 Facebook :- https://www.facebook.com/asharamedia24 youtube :- https://www.youtube.com/channel/UChir2nIy58hlLQRYyHIQeHA

Source: Link to the Post

Leave a Reply