የሙለር ሪል ስቴት ባለቤት ያለአግባብ ሀብት በማፍራት የሙስና ወንጀል ፍርድ ቤት ቀረቡ

የሙለር ሪል ስቴት ባለቤት ያለአግባብ ሀብት በማፍራት የሙስና ወንጀል ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሙለር ሪል ስቴት ባለቤት አቶ ሙሉጌታ ተክለኪሮስ ያለአግባብ ሀብት በማፍራት የሙስና ወንጀል ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡

አቶ ሙሉጌታን ፍርድ ቤት ያቀረበው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የሙስና ወንጀል ምርመራ ባለሙያ ሲሆን፥ ፖሊስ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የተጠረጠሩበትን ጉዳይ ይፋ አድርጓል፡፡

ተጠርጣሪው አቶ ሙሉጌታ ለሀገረ ሰላም ኩባንያ 150 ሚሊየን ብር፣ ለሁዳድ ድርጅት ደግሞ 250 ሚሊየን ብር በጥቅሉ 400 ሚሊየን ብር በአፋር ክልል ሰመራ የጨው ማቀነባበሪያ ጅምላና ችርቻሮ ስራ በሚል፥ 2 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ግምት ያለውን መክሊት ህንጻ አስይዘው ከአቢሲኒያ ባንክ ገንዘብ መበደራቸውን ጠቅሷል፡፡

ብድሩ በአግባቡ ስራ ላይ ያልዋለ እና በየደረጃው በብድር ህግ መሰረት የብድር ፕሮጀክት እየታየ የሚለቀቅ የነበረ ሲሆን፥ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም ሳይታይ ብድሩ መለቀቁን በማንሳት ይህ አግባብነት የለውምም ብሏል ፖሊስ፡፡

እንዲሁም በለገጣፎ ለሪል ስቴት ኪስ በሚል 500 ካሬ ሜትር መሬት ያለአግባብ ወስደዋል ያለው ፖሊስ ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል፡፡

ብድሩ ለምን አላማ እንደዋለ እና ብድሩን ያለ አግባብ የለቀቁ የባንኩ ብድር ክፍል ባለሙያዎችን ጉዳይ እየመረመርኩ ነው ብሏል፡፡

ለተጨማሪ ምርመራም 14 ቀን እንዲሰጠው ችሎቱን ጠይቋል፡፡

አቶ ሙሉጌታ በሦስት ጠበቃ ተወክለው የቀረቡ ሲሆን ብድሩ ላይም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ብድሩን የወሰዱት ሁዳድ እና ሀገረሰላም ድርጅት ሲሆኑ በድርጅቶች ማህበራት መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ ሰባት መሰረት በስራ አስኪያጆቻቸው በኩል ነው ብለዋል፡፡

አቶ ሙለጌታ የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ሳይሆኑ ባለአሲዮን እንደሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ የሁለቱም ድርጅቶች ባለቤት አቶ ሙሉጌታ ናቸው ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

የአቶ ሙሉጌታ ጠበቆች በበኩላቸው ከብድሩ መጠየቅ ጀምሮ እስከመፈረምና ብድሩን እስከመውሰድ ድረስ የደረሱት ስራ አስኪያጆቹ እንጅ አቶ ሙሉጌታ አይደሉም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

አቶ ሙሉጌታ በበኩላቸው መክሊት ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ህንጻ ነው፤ መክሊት ለመንገድ ትራንስፖርት ህንጻ እያከራየ 30 ሚሊየን ብር ገቢ የሚያገኝ ህንጻ ነው፤ እኔ እዚህ ህንጻ ላይ አክሲዮን ነው ያለኝ ወደ ሃገሬ ከመጣሁ 23 አመቴ ነው በርካታ ድርጅቶችን ያፈራሁና ከ1 ሺህ 500 በላይ ሰራተኞች የስራ እድል ፈጥሬ ለሃገራ ልማት እየሰራሁ እገኛለሁ ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ለገጣፎ ከሚገኘው ሮፓክ ሪል ስቴትም አክሲዮን ገዝቸ የነበረ ሲሆን ሸጨ ወጥቻለሁ የቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆኔም ዋስትና ይፈቀድልኝ ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

ጠበቆቻቸውም አቢሲንያ ባንክ መያዣው 292 ሚሊየን 231 ሺህ 800 ብር መሆኑን በመጥቀስ 2 ነጥብ 9 ሚሊየን አይደለም ብለዋል፤ በባንኩ ውል ላይም ብድሩ ለታለመለት አላማ ካልዋለ ሂሳቡ ይታገዳል፣ ብድር ይሰረዛል፣ ወለድ ይጨመራል እንዲሁም በመያዣ ያለው ንብረት ተሸጦ ገንዘቡ ገቢ ይደረጋል የሚል ስምምነት ተደርጎ ከስራ አስኪያጆቹ ጋር ብድር መፈቀዱን አስረድተዋል፡፡

ስለዚህ ባንኩ ባልጠየቀበት ሁኔታ ፖሊስ ወደ ወንጀል ማምጣቱ ትክክል አይደለም ሲሉ መቃወሚያ አቅርበዋል፡፡

ከዚህ በፊትም በመዝገብ ቁጥር 217771 በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ታህሳስ 16 ቀን 2013 ዓ.ም በ100 ሺህ ብር ዋስ እንዲወጡ ፍርድ ቤት አዞላቸው ዋስትናው ተከፍሎ ከእስር ሳይፈቱ ሌላ መዝገብ መከፈቱ አግባብ አይደለም ነው ያሉት፡፡

በ400 ሚሊየን ብር የገንዘብ ጉዳይ 54 ቀን ታስረው ምርመራ ሲከናወንባቸው ነበር፤ አሁንም በዚሁ ገንዘብ ነው የቀረቡት ሲሉ ያቀረቡት መቃወሚያ ላይ ምላሽ የሰጠው ፖሊስ ከዚህ በፊት የተጠረጠሩት በሽብር ወንጀል እና በገንዘብ በመደገፍ ወንጀል ነው፤ ይህ ደግሞ አዲስ ግኝት የሙስና ወንጀል ነው ሲልም ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ክርክሩን ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ በአብላጫ ድምጽ ከታህሳስ 16 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ታሳቢ የሚደረግ 14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ለፖሊስ ፈቅዷል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ለዛሬ ከሰአት በኋላ ቀጠሮ የያዘበት የአውራምባ ታይምስ ባለቤትና ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ላይ 12 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜን ለፖሊስ ፈቅዷል፡፡

በታሪክ አዱኛ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

The post የሙለር ሪል ስቴት ባለቤት ያለአግባብ ሀብት በማፍራት የሙስና ወንጀል ፍርድ ቤት ቀረቡ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply