የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ምክትል ሥራ አስኪያጅ በታጣቂዎች መታገታቸው ተሰማ

እሁድ መስከረም 22 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የመንግሥት የልማት ድርጅት የሆነው የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ምክትል ሥራ አስኪያጅ በቀለ ጋረደው፣ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን ልዪ ሥሙ ጋቲራ በተባለ ቦታ ከእነ ሹፌራቸው በታጣቂዎች መታገታቸውን አዲስ ማለዳ ሰምታለች።

ምክትል ሥራ አስኪያጁ የታገቱት መስከረም 18/2015 ወደ ፋብሪካው እየተጓዙ ባሉበት ወቅት ነው ተብሏል።

መንግሥት እገታውን እንዲያውቅ ቢደረግም እስካሁን ታጋቾቹን ለማስለቀቅ ሙከራ አለማድረጉን አዲስ ማለዳ ጉዳዩን ከሚከታተሉ የፋብሪካው ሰራተኞች የሰማች ሲሆን፤ እገታውን የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ፣ ማዕድን ሚኒስቴርና ሌሎች የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች እንዲውቁት መደረጉ ተመላክቷል።

የታጋች ቤተሰቦች መንግሥት ለጉዳዩ አፋጣኝ ምላሽ ባለመስጠቱ ጭንቀት ውስጥ መግባታቸውን አዲስ ማለዳ ያነጋገርናቸው የፋብሪካው ሰራተኞች ተናግረዋል።

ምክትል ሥራ አስኪያጁን ከእነ ሹፌራቸው አግተዋል የተባሉ ስድስት የታጠቁ ኃይሎች ሲሆኑ፤ ታጋቾቹን ለመልቀቅ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መጠየቃቸውም ተሰምቷል።

ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በአድአ በርጋ ወረዳ ልዩ ሥሙ መኮዳ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ፣ ከአዲስ አበባ ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ 90 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡

The post የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ምክትል ሥራ አስኪያጅ በታጣቂዎች መታገታቸው ተሰማ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply