ይህን ጽሑፍ የላክሁት ትናንት ነበር፡፡ በጣም ቸኩዬ ስለነበር “ኤዲት” ያላደረግኋቸው አንቀፆች ሁሉ እንደነበሩ ጽሑፉ በአንዳንድ ድረገፆች ከወጣ በኋላ ዘግይቼ ነው የተረዳሁት፡፡ ስሜታዊነት ይንጸባረቅበት እንደነበር ተገንዝቤያለሁ፡፡ ስንጽፍ በተቻለ መጠን ከስሜት ወጣ ብለን ይበልጡን በምክንያትና በመረጃ ተደግፈን ቢሆን መልካም እንደሆነ አምናለሁ፤ በሀገራችን የተንሠራፋው ብሶት ግን ለዚህ ስክነት አላደለንምና ብዙዎቻችን ለትዝብት ወደሚዳርገን ይህን መሰል ስህተት በተደጋጋሚ እንዘፈቃለን፡ ሰውና ብረት ከስህተትና ከዝገት ነፃ ባለመሆናቸው በየትኛውም ረገድ በታየብኝ ስህተት ከልቤ ይቅርታ እጠይቃለሁ – ዘመኑም የይቅርታና የምሕረት የመደመርም ጭምር ነው፡፡ የተስተካከለውን አሁን ልኬያለሁና የምትፈልጉ አስተናግዱት፤ ቀድማችሁ የለጠፋችሁትም ቢቻል በዚህኛው ብትለውጡልኝ ደስ ይለኛል፡፡ ማስቸገር እንደሆነ ለኔ ብርቅ አይደለም፡፡
ሀገራዊ መድረኮች ሲዘጋጁ አክራሪ ዘረኞች ዝግጅቱን ጥላሸት እንዲቀቡ ለምን እንደሚፈቀድ አልገባህ ብሎኛል፡፡ አካፋን አካፋ ማለት እየከበደን የማይረባውን ግብስብስ ከጠቃሚው መልካም ነገር ጋር እየለወስን በይሉኝታ መንገድ ከተጓዝን አንድም የሚጠቅም ነገር ሣንሠራ እንደስካሁኑ ሁሉ ጀምበር ትጠልቅብናለች፡፡ ይሉኝታ ድንበር ሊበጀለት ይገባል፡፡ “እገሌን/እነገሌን እንዳይከፋው/እንዳይከፋቸው፣ እገሌ እንዳይቀየም …” በሚል ከጋራ ምጣዱ ይልቅ ለወስላታዋ ዐይጥ ቅድሚያውን በመስጠታችን ለተደጋጋሚ ጥቃቶች ተዳርገናል፡፡ ለይሉኝታቢሶችና ለሀፍረት የለሾች አጋልጦ አሣራችንን እያበላን የሚገኘው ይህ የሚጠቅምን ከማይጠቅም መለየት ያለመቻላችን በሥነ ልቦና ቋንቋ የ“phlegmatic” ጠባያችን ነው፡፡ ሀገራዊና ምሥራቅ አፍሪቃዊ የዕርቅና የሰላም መድረክ ሊባል በሚችል ሁኔታ በተዘጋጀ የፍቅር መድረክ አንዱን ጎሣ ከሌላው ለማለያየትና በእግረ መንገድም ለማጋጨት ዜጎችን ለሁከት የሚያነሳሳ አንድምታ ያለው መልእክት ሲተላለፍበትና ጥቂት የማይባሉ የዋሃን ታዳሚዎች ሳይገባቸው ሲያጨበጭቡ መመልከት በእውነቱ ያናድዳል – የሚሌኒየሙ የበቀደሙ ዝግጅት ዋና ዓላማ የሁለት ሀገር ሕዝችን ማስታረቅና ማስማማት እንጂ በቡድኖች የተፈለሰፈም ይሁን ወያኔ በቤተ ሙከራው ከየቀለማቱ ቀጣጥሎ በማሰፋት ለየጎሣው ያደለው ባንዲራ እየተውለበለበ ሰዎችን ውዥንብር ውስጥ እንዲከት አይደለም፡፡ ከዚህ መሠረታዊ ነጥብ አንጻር የሚሌኒየሙ ዝግጅት ዓላማና የነአርቲስት አጫሉ ዓላማ መቶ በመቶ ይቃረናል፡፡ በሚቃረኑ ዓላማዎች ደግሞ ሰውን ማወናበድና በጨለማና በብርሃን በሚመሰሉ ተፃራሪ ዓላማዎች ጊዜን ማባከን ትክክል አይደለም፡፡ ለወደፊቱ ሊታሰበብበት ይገባል፡፡ መቻቻል ዓይነት አለው፡፡ መታገስ ልክ አለው፡፡ ልዩነትን በፍቅርና በመተሳሰብ ማስተናገድ ገደብ አለው፡፡ ዘመኑ የዴሞክራሲ መባቻ ነው ተብሎ የሀገርና የሕዝብ አንድነትን ተመርኩዞ በተዘጋጀ መድረክ ላይ ማንም እየተነሣ ድብቅ ዓላማውን ሊያራመድ አይገባም፡፡ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ ሲገነባው የሚውለውን በጎ ነገር አላዋቂዎችና የጎጠኝነት አስተሳሰብ ምርኮኞች ሲያፈርሱ እንዲያመሹ ከተፈቀደ ታጥቦ ጭቃ ነው፡፡ ስለሆነም ለሌላ የንፍር ቁስል ሊዳርገን የሚያዘጋጀንን ዘረኛ አካሄድ ልንጠየፈውና ካሁኑ ልንከላከለው ይገባናል፡፡ ዐርባና ሃምሣ ዓመታት ተሞክሮ እውን መሆን ያቃተው ሕዝብን በታኝ ወያኔያዊ አስተሳሰብ በዚህች በተፈጠረችልን መልካም አጋጣሚ ሠርጎ ገብቶ ለሌላ ዙር ሁከትና ብጥብጥ ሊዳርገን እንዳይችል ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይንና ለማን ተመስሎ የመጣልንን ይህን ወርቃማ ዕድል እንደዐይናችን ብሌን እንጠብቀው፡፡
ከፍ ሲል የጠቀስኩት አጫሉ የተባለ ወጣት አርቲስት ክፉ ነው፤ ውስጡን በስድስተኛው ስሜቴ ስፈትሸው የለዬለት ዘረኛና የጥላቻ ዋሻም ነው፡፡ ይህን ጎጠኛ ልጅ ቀልቤ እንዲወድልኝ ፈልጌ በምኞት ብቻ ቀርቻለሁ፡፡ ፊቴ የጠቆረባቸው በርካታ ስህተቶችን ፈጽሟል፡፡ ለምሣሌ በመድረክ ላይ ያውለበልበው የነበረው ባንዲራ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን የሚወክል አልነበረም – ጥሩ ነገር ማድረግ ሲችል አልፈለገም፤ ሙሉነትን ሣይሆን የግንጥል ጌጥ ጎደሎነትን መፈለጉን ይህ ድርጊቱ ብቻ ያሣያል፤ “እኛነት”ን በ“እኔነት” መተካቱን ያመለክታል – ወደታች ወደሽርንቁላ ወረደ፤ ከልጅነቱ ጀምሮ በወያኔና ግብረ አበሮቹ ሲጋት ያደገውን ቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ ውጤት በገሃድ አሳዬ – በነገራችን ላይ በሚሌኒየም አዳራሽ እጅግ ብዙ ንጹሕ የኢትዮጵያ የቀድሞ ባንዲራ ሲውለበለብ ነበር፤ ይህን ባንዲራም አዲሱ የለውጥ መንግሥት በሕዝብ ይሁንታ ወደቀድሞ ክብሩና ማዕረጉ በቅርቡ እንደሚመልሰውና ዜጎች የሚጠሉትን ያን ባለኮከብ ባንዲራ ወደታሪክ መዝገብ እንደሚያስገባው ሙሉ እምነት አለኝ፡፡ በሕዝብ ምርጫ የሕዝብን ፍላጎት እውን ማድረግ መለመድ አለበት፡፡ ሕዝብ የጠላውን ነገር በአፋጣኝ ማስወገድ ደግሞ ሀገራዊ ፍቅርን ይጨምራል እንጂ ክፋት የለውም፡፡
ጎጃም ባህር ዳር ላይ “አማሮች” የኢትዮጵያን ንጹሕ ባንዲራ በማውለብለባቸው ታላላቅ የፖለቲካ ጡረተኞች ሳይቀሩ “ህገ መንግሥት ተጣሰ” በሚል እሮሮኣቸውን አሰሙ፡፡ “የፌዴራል ሥርዓታችን ተንኳሰሰብን” ብለውም አገር ይያዝልን አሉ፡፡ አንዳንድ በፌዴራል ስም የተዋቀሩ አካባቢዎች በቅድሚያ “ፌዴራል” የሚባለው ትልቅ ጽንሰ ሃሳብና ትግበራው ይቅርና ራሳቸውን መግለጽ የሚያስችል በቂ ዕውቀትና ከዕለት እንጀራ ባለፈ ለጥቂት ጊዜ የሚሆን ጥሪት የሚያፈሩበት የሥራ ባህል በኖራቸው፡፡ ወያኔ ሲያላግጥባቸውና ሀብት ንብረታቸውን በዘዴ ሊቀማቸው ፈልጎ ወረቀት ላይ የቀመረውን የሌለ ፌዴራሊዝም እንዳይፈርስ አንዳንዶች ለመከላከል ሲሞክሩ ይገርማሉ (ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት”ይባላል፡፡ “ድንቄም ፌዴራሊዝም!” ለማለት ነው)፡፡ ለማንኛውም አርቲስት አጫሉ የፌዴራሉንም የቀደመውን የኢትዮጵያ ባንዲራንም ትቶ የተለዬ ሰንደቅ ዓላማ ሲያውለበልብ እነዚያ የ“ህገ መንግሥት ተጣሰ” አቀንቃኞች ምን ይሉ ይሆን? በደስታ የታጀበ ዝምታን እንደሚመርጡ አልጠራጠርም፡፡ ሌላ ልጨምር – አጫሉ “አመሰግናለሁ”ን በኦሮምኛ “ገለቶማ”፣ በማያውቀው በእንግሊዝኛ ደግሞ “thank you” እያለ ሲደጋግም በአማርኛ ግን ተስቶት አንዴም አላለም፡፡ ልሰልስ – በዚያን ሰሞን ይሄው አርቲስት በቤተ መንግሥት አንድ ግሩም ድራማ እንደሠራ ሰምቻለሁ – የሰማሁት እውነት እንደሚሆን ልጁን ከተጣባው የዘረኝነት ልክፍት በመነሣት ብዙም መጠራጠር አልፈልግም፡፡ አጫሉ እነ ሠራዊት ፍቅሬን የመሰሉ “በሕዝብ አገልጋይነት” የሚታወቁ አርቲስቶች ወደቤተ መንግሥት ሲጠሩ ጥሪውን ተቀብሎ ሄደ አሉ፡፡ አዳራሹ ውስጥ እንደገባ በርሱ ልኬትና ሚዛን መሠረት ዐይን የሚሞሉ የኦሮሞ አርቲስቶችን ያጣል አሉ፡፡ ያኔ “የኦሮሞ አርቲስቶች ባልተገኙበት ሁኔታ ይህ ስብስብ እኔን አይመጥንም” በማለት ወጥቶ ሄደ አሉ፡፡ አንድ የሕዝብ ልጅ እስከዚህን ወርዶ ሲታይ አሣፋሪ ይመስለኛል፡፡ ሌላው ከነሱ ምን ይማር? እነሱ ከኛ ተሽለው ካልተገኙ እኛማ ከነሱ እንዴት አንብስ?
በመሠረቱ አጫሉ አማርኛን ተናገረ አልተናገረ ለማንም ምንም ማለት አይደለም፤ ቋንቋ የመግባቢያ መሣሪያ እንጂ እስከዚህ የሚያስጨንቅ ነገር አይደለም፡፡ አንድን ቋንቋ የተናገረ ይጠቀምበታል – የማንም ይሁን የማን – የቋንቋው ባለቤት ከሚባሉት ጋር አንዳችም ግንኙነት የለውም፡፡ ከቋንቋው የመጀመሪያ ተናጋሪ ጋር አናያይዘው፤ አንድን ቋንቋ በአንድ ወይ በሌላ ምክንያት ያልተናገረ ልዩነቱን ያሰፋበታልና አይጠቀምበትም – ኤርትራውያን በአሁኑ ወቅት በዚህ በአማርኛ ምክንያት እንዴት እየተቆጩ እንደሆነ የፕሬዝደንቱ የአቶ ኢሣይያስ አማካሪ ሰሞኑን የጻፉትን አንድ ጽሑፍ በማንበብ መረዳት ይቻላል፡፡ በቋንቋ ላይ ማመፅ ትርጉም አልባ ነው፡፡ ቋንቋ ወንዝ ያሻግራል፤ ኩራት ብቻም ሣይሆን እራትም ጭምር ነው – ጦጣም ቋንቋ ካላት ተማረው ወንድሜ፤ አንድ ቀን ከጉድ ትወጣበታለህ፡፡ ሰይጣንም ቋንቋ ካለው እርሱንም ተማርና ልመደው – ስንቅህ ባለቀበት ወረትህ በሳሳበት አንድ ቀን ይጠቅምሃል – የሰው እንጂ የቋንቋ ክፉ የለውም፡፡ ኢሣይያስ አፈወርቂ ከስንት ዓመት በኋላ ሕዝብ ፊት ምናልባትም ዱሮ ይጠላው በነበረው ቋንቋ በአማርኛ ሲናገር የተገላቢጦሽ ሆነና እዚሁ እኛው ጋ ያለው ሁላችንን ሊያስተሳስር የሚገባው አርቲስት አጫሉ መልእክቱ ግልጽ በሆነ መልኩ ሊናገር አልፈቀደም፡፡ አማርኛ አለመናገሩ በምንም መንገድ ቆጭቶኝ እንዳልሆነ በድጋሚ ያንጀቴን መናገር እፈልጋለሁ፤ አጫሉ አልተናገረው ሪቻርድ ፓንክረስት ከነቤተሰቡ አቀላጥፎ ተናገረው ለኔ ለምሥኪኑ ዳግማዊ ምንም የሚፈይድልኝ ነገር የለም፤ ይህ ቋንቋ ከ80 በላይ ለሚሆኑ የኢትዮጵያ ነገዶችና ዘውጎች ድልድያቸው ነው፤ ይህን ቋንቋ መናቅም ሆነ ማክበር አማሮች ከሚባሉ ሰዎች ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ ነገሩ ያለው ከሀገር ኅልውናና ከሕዝብ አንድነት ጋር ነው፡፡ የአጫሉን መሰል የዘረኝነትና የጠባብነት ልኬት ማጣት ኅልው በሆነበት ሁኔታ የነዶ/ር ዐቢይ ጥረት የትም ሊደርስ እንደማይችል ይሰማኛል – ያ ደግሞ እንደአንድ ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ ክፉኛ ያሳስበኛል፡፡ የነዐቢይ ድካም ሕዝብን አንድ ማድረግ ነው፡፡ “የቀደመ የታሪክ ቁርሾ በማስታወስ ነገር ከማሞስካት ይልቅ የተበዳደልነውን ቢኖር ያን ያለፈ ታሪክ ይቅር በመባባል አዲስ ሕይወት እንመሥርት” ብሎ ሌት ከቀን ያለ ዕረፍትና ያለ ዕንቅልፍ ሲደክም ይህን መልካምነት የሚያጥረው አርቲስት የመሰሉ ሰዎች ደግሞ በዚህን ልጅ ልፋትና ድካም ቀዝቃዛ ውኃ ይቸልሳሉ፡፡ አስተዋይ ልቦና ይስጣቸው፡፡
ሕወሓትና ሕወሓታውያን በዐቢይና በቡድኑ የተጀመረውን ለውጥ እንደማይወዱት ማንም ይረዳል፡፡ እውነታቸውን ነው፡፡ በማንም አልፈርድም – ተንሻፎ የሚጓዝ የኅልውና ገመዳቸው ነውና፡፡ ለምሣሌ ጅብ አንዲት አህያ ዘርጥጦ ጥሎ እየቦተረፋትና እያወራረዳት ሳለ ሰው ደርሶ ከዚያ ሲሳይ ሊያባርረው ቢሞክር ሰውዬው ራሱ የጅቡ ሲሳይ ከመሆን አይተርፍም፡፡ ነብር ፍየልን ይዞ ደሟን እየመጠጠ ባለበት ሰዓት ሰው ደርሶ ሊያስጥል ቢል የፍየሏን ዕድል ይጋራል፡፡ አንበሣም ሚዳቋን ይዞ እየተምነሸነሸባት ሳለ ሰው ደርሶ ይህን ማዕድ ላጨናግፍ ቢል በሕይወቱ ቆርጧል ማለት ነው፡፡ የነገሮች ምስስል እንደዚህ ነው፡፡ ወያኔና በሚሊዮን የሚቆጠረው የትግራይ ተወላጅና ሌላው የፍርፋሪ ቀላዋጭ ሁሉ ዕድሉ የተሳሰረው ከወያኔ ጋር ስለሆነ እነሱን በዘዴ መያዝ እንጂ የሚያስከትሉት ጉዳት እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ሆድ መጥፎ ነውና፣ ሆዳም ሰው ፍቅር አያውቅምና፣ እነዚህ ሆዳሞች ሊያደርሱት የሚችሉት አጠቃላይ ውድመት በቅጡ መታሰብና ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ በረከት ስምዖን ገጠር ለገጠር እየኳተነ የሚገኘው ለጽድቅ አይደለም፡፡ የዐቢ ቡድን ግን የተኛ ይመስላል፡፡ “ሰነፍ እረኛ ከሩቅ ይመልሳል” እንዲሉ እንዳይሆን መጠንቀቅ አለባቸው፡፡ ጊዜ ደግሞ ባሰኘው አቅጣጫ እንደሚነፍስ ነፋስ እንጂ ቆሞ የሚጠብቅ ባቡር አይደለም፡፡
ሰሞኑን በአሥመራና በአዲስ አበባ በተካሄዱ የፍቅር ጅማሮና ዕድሳት መርሐ ግብሮች ላይ አንድ ነገር ይከሰታል ብዬ ፈርቼ ነበር፡፡ ግን እግዜር ይመስገን በአደባባይ የተገለጠ ምንም ነገር አልሆነም፡፡ ሁሉም በሰላም መጠናቀቁ ያስደስታል፤ ሀገርንም ያኮራል፡፡
ወያኔዎችን እከታተላለሁ፡፡ በሁሉም ረገድ ነው የምከታተላቸው፡፡ የክትትሌ መሠረትም ለዚህ ለውጥ ያላቸውን አመለካከት ለማወቅ ከመፈለግ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ትግራይ ቲቪን ሆን ብዬ አያለሁ፡፡ ደስተኞች አይመስሉም በለውጡ፡፡ ምክንያቱን ማወቅ አያስፈልገኝም፡፡ አውቀዋለሁ፡፡ ለምን ይህን እንዳልኩ ትንሽ ማለት ካለብኝ – የአማራውን ጨምሮ በሌሎች ቲቪዎች የፌዴራሉ አንዳንድ ሰበር ሁኔታዎች በቀጥታ ሲታዩ በነሱ ግን መደበኛ ፕሮግራም ነው የሚተላለፈው፡፡ ልጨምር – የቀድሞ ታጋዮችንና ከሕዝብ ጎን መቆም የሚጠበቅባቸውን የዩንቨርስቲ ምሁራንን በውይይት እያናጋሩ ለውጡን የሚቃወም ዝግጅት ይዘግባሉ፡፡ ልሰልስ – የቀድሞው የኢንሳ ሥራ አስኪያጅ ጄኔራል ተ/ብርሃን በአዲሱ የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ ያወጀውን ጦርነት ያስተላለፉት እነሱው ናቸው፡፡ እንዳላሰለች እንጂ መቀጠል በቻልኩ፡፡ ግን ይብቃኝ፡፡ ብቻውን ሀገርንና ሕዝብን ሲግጥ የነበረ ቡድን ከሥልጣን ሲገለል ደጋፊውና አጫፋሪው፣ የጥቅም ሸሪካውና አቀባይ ተቀባባይ ሁሉ ደስተኛ እንደማይሆን ግልጽ ነው፡፡
የሆድና የጥቅም ነገር ይገርማል፡፡ ኢትዮጵያን ብቻየን ለምን አልዘነጥላትም? ለምን ብቻየን እየዘረፍኩ ክልሌን አላለማም? የተቃወመኝን ሁሉ እያሰርኩና እየገረፍኩ፣ ጥፍር እያወለቅሁና በፈላ ዘይት እያንጨረጨርኩ፣ ውኃ የተሞላ ኮዳ እንትን ላይ እያንጠለጠልኩ፣ ፖሊስን፣ ደኅንነትን፣ መከላከያን፣ አየር ኃይልን፣ አየር መንገድን፣ ባንክን፣ ማዕድንን፣ ኋላ ቀር ክልሎችን፣ ፓርላማን(የውሸትም ቢሆን)፣ የተወካዮች ምክር ቤትን፣ የገንዘብና የመሣሪያ ግምጃ ቤትን፣ … ምን አለፋችሁ ሁሉንም የኢትዮጵያ የሆነ ነገር ሁሉ በአንድ ዘውግ ተቆጣጥሬ እንዳሻኝ ዕድሜ ልኬን ልዘባነን ብሎ አንድ ወገን ሲወስንና በሌላ በኩል “ተካፍለን እንብላ” የሚል አሳቢ ወገን ሲመጣ ይሄ ወያኔ የሚባል ዘረኛ ቡድንና አጫፋሪዎቹ ቡራከረዩ ሲሉ እጅግ ይገርማሉ፡፡ ባለ ላስቲክ ሆድ ምድረ ወያኔ ሁሉ በእውንም በህልምም ያልጠበቀው አዲስ ለውጥ ሲመጣ ጊዜ ምድር ቁና ሆነችበት፡፡ ወያኔ በተቃውሞ የሚጠረጥረውን ሁሉ በዝግ የሌሊት ስብሰባዎች እየወሰነነ ሲቻል በድብቅ ሳይቻል በግልጽ ድራሻቸውን ሲያጠፋ ለምዶ አሁን ላይ እንደዱሮው መጓዝ ባለመቻሉ ሰማይ ተደፋበት፡፡ ለሁሉም ችግሩ ግድያን እንደመፍትሔ ይወስድ የነበረው ህወሓት እነኦቦ ዓለማየሁ አቶምሣን የታሸገ ውኃ በመመረዝ አጠጥቶ አሰቃይቶ ገደለ፤ እነዚህ ከይሲዎች ከዚያ ደግ ሰው በተጨማሪ እጅግ ብዙዎችን አጥፍተዋል፡፡ አሁንም በዚያ የመግደያ ሥልት እነዐቢይንና ለማን ለመግደል እየዛቱና እየሞከሩም እንደሆነ ከሁነኛ ምንጭ ሰማሁ፡፡ የወያኔው የስለላ ቡድን ከአንጋፋዎቹ የዱሮ አለቆች ጋር በምሽት እየተገናኙ – አሁንም ድረስ – በዚያው ያረጀ ያፈጀ ሥልት የለውጡን ኃይል ገድሎ በመጨረስ በሀገራችን የፈነጠቀውን የነፃነት ጮራ ለማጥፋት ሤራውን እንደቀጠለ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን መልእክቴን ለሚመለከታቸው ወገኖች ሁሉ አድርሱልኝ፡፡ የምረቃ ዝግጅትንና የድግስ ወጪን በማይጠይቀው የማታ ትምህርት ቤት የማይገኝ ምሥጢር የለምና የምንሰማው ብዙ ነው፡፡ ከመነሻው ይህን ለውጥ ፈጣሪ የፈቀደው በመሆኑ ምንም ያህል ቢፍጨረጨሩ አይቀለብሱትም እንጂ ሙከራዎቻቸው ሁሉ ሲታዩ ተስፋን ያጨልማሉ – ወያኔዎች ክፉ የክፉ ክፉ ናቸው፡፡ ለማንኛውም በኋላ ከመቆጨት ቀድሞ መጠንቀቅ ይገባል፡፡
የኤርትራና የኢትዮጵያ መንግሥት በብዙ ነገሮች ላይ ተስማምተዋል፡፡ ኤምባሲዎች ተከፍተዋል፡፡ ቀጥታ ስልክ ተለቋል፡፡ የአየር ትራንስፖርትም ሊጀመር ነው፡፡ ሌላም ሌላም ሊቀጥል ነው፡፡ እጅግ መልካም ነገር ነው፡፡ ተለያይተው የነበሩ ወንዳማማችና እትማማች ሕዝቦች ወደቀደመ ሰላማቸው መመለሳቸው ከሰይጣኖቹ ወያኔዎች በስተቀር የማያስደስተው የለም፡፡ እነእንቶኔ ግን ጥቅማቸው ስለሚጓደል የነዚህን ሁለት ሕዝቦች ሰላምና ፍቅር አይወዱም ብቻ ሣይሆን በተቻላቸው ሁሉ ጥረት አድርገው የቀድሞው የፍጭትና የግጭት ጉርብትና እንዲመለስ መሞከራቸውን ይቀጥላሉ፡፡
እዚህ ላይ የምጠቁመው ነገር አለ፡፡ ይህን መልእክቴንም ለሚመለከታቸው ክፍሎች አድርሱልኝ፡፡ ኤርትራና ኢትዮጵያ እንደሌሎች ሀገራት አይደሉም፡፡ በተጣመመ ቀን ተለያይተው ሁለት ሆኑ እንጂ በቋንቋ፣ በደም፣ በሥነ ልቦና፣ በሃይማኖት፣ በኑሮ ዘይቤ፣ በኢኮኖሚና በመሳሰሉት እጅግ የሚመሳሰሉ በአንዳንዶቹም አንድ የሆኑ ሕዝቦች እንደሌሎች ሀገሮች የሚቆጠሩ ከሆነ ይሄ ሁሉ የአሥመራ-አዲስ አበባና ሀዋሳ ግርግር ከንቱ ድካም ነው፡፡ ለምሣሌ የስልክን ታሪፍ እንመልከት፡፡ ከአዲስ አበባ አሥመራ በደቂቃ ብር 10 ከ92 ሣንቲም ነው ተብሏል፡፡ ይሄ ምን ማለት ነው? “እንዳያማ ጥራው፣ እንዳይበላ ግፋው” አይሆንም ወይ? ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን ልክ እንደ ኢትዮጵያውያንና ካናዳውያን ከተቆጠሩ ዝምድናውና የቀድሞ አንድነቱ፣ ወደፊትም ሊደርሱበት የሚመኙት የጋራ ማኅበረሰብነቱ የት አለ? ተመኖች ሲወጡ የሁለቱንም ሀገራት ሕዝቦች ኢኮኖሚያዊ አቅም ግምት ውስጥ ካላስገቡ የተለዬ ዝምድና ያለን መሆናችን በምን ይታወቃል? አሥመራ ለመደወል እኮ ከአሁን በፊት በተዛዋሪ ብር 10 ብቻ ነበር የሚከፈለው፡፡ ታዲያ ዛሬ ስምምነት ሲፈጠር 92 ሣንቲም እንዴት ተጨማሪ ይከፈላል? ይህ ነገር በከፍተኛ ደረጃ ሊታሰብበትና ከሁለቱም ወገኖች የገንዘብ አቅም ጋር የሚገናዘብ ታሪፍ ሊወጣ ይገባል፡፡ የአሁኑ እጅግ ውድና የቀድሞውን የተዛዋሪ ስልክ አጠቃቀም የሚያስመርጥ ነው፡፡ ጥቅም እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ ሊሄድ አይገባም፡፡
በሌላም በኩል የአየር ትራንስፖርቱ ወደ ስምንት ሺህ የሚጠጋ ብር ነው፡፡ ይህም ታሪፍ ልክ እንደባዕዳን ሀገራት ታይቶ የተመደበ እንጂ የሁለቱን ሀገራት የዝምድና ትስስር ግምት ውስጥ አላስገባም፡፡ እናት ልጇን ለማየት፣ እህት ወንድሟ ለመጎብኘት፣ ባል ሚስትን ይዞ ለመሄድ/ለመምጣት፣ ወንድም ወንድሙንና እህት እህቷን ለመጎብኘት… እንዴት ይህን ያህል ገንዘብ ይጠየቃሉ? እንዲህ ያለ ታሪፍ የሚያወጣ ሰው በጣም ግዴለሽና ቅንጡ ነው ወይም የሁለቱ ሀገራት ዳግም ግንኙነት ያናደደው ግለሰብ መሆን አለበት፡፡ አቅማችንንና ግንኙነታችንን (ዝምድናችንን) ያገናዘበ ይሁን፡፡
በአውቶቡስ መሄድ ሲጀመርም እየተስተዋለ ቢሆን ጥሩ ነው፡፡ እያልኩ ያለሁት በአጭሩ ሲጠቃለል ኤርትራና ኢትዮጵያ እንደሌሎች ውጭ ሀገራት ሳይሆን እንደ አንድ ሀገር ክልሎች ቢታዩ የዜጎች እንቅስቃሴ በገንዘብ አቅም ምክንያት ሳይገደብ እንደልባቸው ሀገሮቻቸውን መጎብኘትም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን መጠየቅ ይችላሉ፡፡ በማንኛውም ረገድ አንደኛቸው ለሌላኛቸው እንደውጭ ሀገር ሰው እንዳይታዩና ገንዘብ ተርፎት ዓለምን እንደሚዞር ቅንጦተኛ ቱሪስትም እንዳይቆጠሩ መደረግ አለበት፡፡ ያኛው ለዚህኛው ቤቱ ነው፤ ይህኛውም ለዚያኛው ቤቱ ነው፡፡ የተጋነኑ ልዩነቶች የባዕድነት ስሜት እንዲሰማን ያደርጋሉና ጥንቃቄ ይደረግ፡፡ ሁላችንም የደላን አለመሆናችንም ግምት ውስጥ ይግባ፡፡
ለገምቢ አስተያየት – [email protected]