የማንነት ፖለቲካ ዜጎች ተንቀሳቅሰው እንዳይሰሩ አድርጓቸዋል ሲል የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ ገለጸ፡፡

ጦርነት ባለበት ሀገር ልማት ሊኖር አይችልም ያለው ፓርቲው፣ ሁለቱ እርስ በርስ የሚጠፋፉ ናቸው ሲሉ የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራ ኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ ሀብታችንን ጦርነት ላይ እያዋልን፣ በተቃራኒው የወደመውን ደግሞ መልሶ ለማቋቋም የሚሰራ ስራ ውሃ ቅዳ ውሃ ምለስ ውጤት አልባ ስራ ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡

“እያንዳንዱ ጥይት በዶላር ነው የሚገዛው፣ በተመሳሳይ በርካታ የልማት ጥያቄዎች ይነሳሉ፣ ይህ እስከ መቼ ያስኬደናል?” ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡

በመሆኑም መንግስት ተነሳሽነቱን በመውሰድ ግጭቶችና ጦርነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ለንግግር ባለፈ ተግባራዊ የሆነ እርምጃ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ችግሮችን የምታስተናግድበት ትከሻዋ እየዛለ ነው የሚሉት ሊቀመንበሩ፣ በአሁኑ ወቅት በማንነት ፓለቲካ የተነሳ ዜጎች ተንቀሳቅሰው መስራት አልቻሉም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የስራ አጥነት መበራከት፣በርካታ ተፈናቃዮች በየክልሉ ባሉበት ሁኔታ ለጦርነት በጀት እያወጡ መቀጠል በምንም መመዘኛ ተገቢነት ያለው ተግባራ አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም መንግስት ሰላም የሚመጣበትን መንገድ መፈለግ ተቀዳሚው ስራው ሊሆን ይገባል ሲሉ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

በአቤል ደጀኔ

ጥር 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply