የምሁራን መንጋዎች ዛሬም አምባገነኖችን በሙገሳ እየካቡብን ተቸግረናል!ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ ሰማይ አዘጋጅ)

በሕዝብ የመከራ ብሶት ምክንያት ለውጥ በመጣ ቁጥር ምሁራን በትረ-ሥልጣን ለተቆጣጠረ ሁሉ ነጠላቸውን አወንዝፈው አጋፋሪ ሆነው የሰፊውን ሕዝብ መከራ እንዲራዘም የማይነቀሉዕንቅፋቶች ሆነው ዛሬም የመቀጠላቸው ክስተት መፍትሄ አልተገኘለትም።

ከ1966 እስከ ዛሬ ድረስ ተራ በተራ ስልጣን ላይ እየወጡ ያሉ መሪዎች እና ቡድኖች ለሥልጣናቸው አስተማማኝ ምሽግ አድርገው የሚተማመኑበት ዋነኛው መሳሪያ የታጠቁት ጠመንጃ ሳይሆንየመንጋ ምሁራንና ጋዜጠኞች የፕሮፓጋንዳቸው አሰራጪዎች በማድረግ ነው

ምሁራኖቻችን  ጠንካራ ተሟጋቾች የሚመስሉ ግን ተሎ ሸብረክ የሚሉ የተሸናፊነት ባሕሪ የሚያጠላባቸው ደካሞች ስለሆኑ እስካሁን ድረስ ወደ ሥልጣን የመጡ አታላይ መሪዎች መጠቀሚያ እየሆኑ የሕዝባችን ሕይወት አደጋ ላይ እንዲወድቅ እያደረጉ ነው።ከዚህ አርጋጅ ባሕሪ የሚፈወሱበት መድሃኒት ካልተገኘ ኢትዮጵያ የአምባገነኖች እና የወንጀለኞች መፈንጫ መሆንዋ ትቀጥላለች። ወይንም ከነጭራሹ በዘር ጽዳት ትበተናለች።

ዛሬ ወደ ሥልጣን የመጣው “ቲም ለማ” እየተባለ የሚጠራው የፋሺስት ብሔረተኞች እና የወንጀለኞች ድርጅት ስብስብ -አብይ አሕመድ የተባለ እበባዊ ተክለሰውነት ያለው ዘዴኛ ወደ ሥልጣን በማውጣት በሕዝብ የተቀጣጠለው አብዮት “በሚማርኩ አጭበርባሪ ቃላቶች” ተጠቅሞ 98% የሚሆነው ምሁር በማጃጃል ለውጡ እንዲቀለበስ ተደርጛል። እንደሚታወቀው ሥልጣን ከትግሬዎች መንግሥት ወደ ኦሮሞዎች መንግሥት ቁጥጥር ሥር ወድቋል።

የጥገና ለውጥ አራማጅ በሎ ራሱን በአዲስ ስም ጋርዶ ወደ ሥልጣን የመጣ ይህ የወንጀለኞች ስብስብ፤ወደ ሥልጣን በወጣ በአንድ አመት ዕድሜው ውስጥ ለመስማት በሚዘገንን የሕዝባችን ጭፍጨፋ ተካሂዶ ከ 1 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ከሚኖሩባቸው ክልሎች “ውጡ” እየተባለ ተፈናቅለው የዘር ጽዳት ዘመቻ ተካሁዷል።”የጭካኔው እና የሥርኣተ አልባነት መጠን” ለመግለጽ ቃላት በሚየጥር ሁኔታ ተከናውኖኣል። ዛሬም ቀጥሏል።

በተደራጁ አሸባሪ ብሔረተኞች የተከናወነው የዘር ማጽዳት የባንኮች ዘረፋ፤የዜጎች መኖርያ ቤቶችን በቡልዶዘር ማፍረስ ሰላማዊያን አዲስ አበቤዎችን እስር ቤት እያጎሩ በወንድ ብልት ላይ ሃይላንድ እያንጠለጠሉ ሰቆቃ መፈጸም ቀጥሏል። ለዚህ ሁሉ ማስረጃዎች ታሪክ እንዲዘግበው ሞልቶ ተከምሯል። በሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍ “ባለሥልጣናት፤በታጣቂ ፖሊሶች፤ ሚሊሺያዎች እንዲሁም ልዩ ሃይል እና ፌደራል የተቀላቀለበት ሽብር “ለምን ተፈጸመ?” ተብለው በስልጣን ላይ ያሉት ፋሺሰቶች ሲጠየቁ በተለይም መሪያቸው አብይ አልሰማሁም፤ አለነበርኩም አላየሁም እያለ “አውቆ እንዳላወቀ” ከተጠያቂነት ለመሸሽ ሞክሯል።

የፋሺሰት መሪዎቹ ‘ችግሩ ከተነገራቸው በኋላም’ ቢሆን እንኳን በወቅቱ ደርሰው ለማስቆም ቀርቶ “ጭፍጨፋው” በብረት እየተደገፈ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ የመንግሥት ባለስልጠኖች እጃቸው በሴራው ውስጥ ማስገባታቸው ተጨባጭ ማስረጃ ሲነገራቸውም “አብይ” እራሱ በቃሉ እንደተናገረው ችግሩ ይቀጥላል፤ቀስ ብሎ ከጊዜ እራሱ ይከስማልእንዲህ ያለ ችግር የተከሰተበት ምክንያትም ሕዝቡ ነፃነት አላምጦ ስለማያውቅ ዛሬ ነፃነት ስላጣጣመ የዛው በነፃነት የመግለጽ ውጤት ነው! በማለት ወንጀልን የነፃነት ውጤት ነው በማለት ወንጀለኞች የልብ ልብ ሰጥቶ እንዲቀጥሉ አድርጎአቸዋል።

 

በሚገርም ሁኔታ ለወንጀለኞች ለባንክ ዘራፎዎች እና የዘር ማጽዳት ዘመቻ ለሚያካሂዱ “ኦሮሞ ኢንተርሃሙዌዎች” ምሰማር እና ሜንጫ ይዘው እያሉ እየፎከሩ ስብሰባ ለማካሄድ ሲፈቀድላቸው በአንጻሩ እንደ እነ እስክንድር ነጋ የመሳሰሉሃገራዊያን ዜጎችስብሰባ እንዳያካሂዱ የፋሺስቶቹ ስርዓትበተደጋጋሚአግዶአቸዋል። ግልጽ ጦርነት እናካሂድባችኋለን ብሎ አብይ የዛተባቸው ዛቸው “የመጀመሪያው እርምጃ” ነው። ቀጥሎም ሊረሽናቸውም ይችል ይሆናል። ታዋቂ ሰዎች ተገድለው እስካሁን ድረስ ምስጢሩ በይፋ አልታወቀም። የፋሺሰቱ ቡድን በታዋቂ ግለሰቦች ላይ ቅስፈትን” ማካሄድ ለ27 አመት የለመደበት ባሕሪው ነውና።

ይህ ሁሉ ወንጀል ተፈጽሞ እያለ ታዋቂ ምሁራኖች በሚያሳፍር ባሕሪ የፋሺስት ብሔረተኞቹ መሪ የአብይ አሕመድ እና የለማ መገርሳ “እምባ እቅራሪዎች ሆነው ማፈሪያ ሕሊናቸው ታሪክ እንዲስቅባቸው ያለ ምንም ማንገራገር እራሳቸው አስሰልፈዋል።

ሰሞኑን ፕሮፌሰር አል ማርያም አብይ አሕመድን ለመካብ በእንግሊዝኛ የጻፈውን አንብቤ ገርሞኝ ቅሬታየን በግል ኢመይሉ መልስ ጽፌለት ሳልጨርስ ትናንት ደግሞ አንድ በጣም የማከብረው መረጃዎችን ዘወትር የምንለዋወጥ የቅርብ ወዳጄ በቴሌፎኔ መልእክት የላከልኝ የአንድ ምሁር ጽሑፍ አንብቤ የምሁራን መንጋ እንዲህ መብዛቱ ብቻ ሳይሆን የአብይ አሕመድም ሆነ  የለማ መገርሳን ተክለሰውነት ለመካብ የተጠቀሙባቸው ቃላቶች ለመግለጽ ምን ያህል ርቀት እንደሚጓዙ አንብቤ የኢትዮጵያ ችግር አምባገነን መሪዎች ሳይሆኑ ፤ ለከት በአጣ ውዳሴ መሪዎችን ወደ ቅዱስነት እና ሙሴነት አልፎም ወደ እግዚአብሔርነት ለውጦ የመካብ ባሕሪ የተጠናወታቸው ምሁራን የችግራችን  ይነተኛ ችግሮች መሆናቸው የታዘብኩበት ጽሑፍ ነበር።

 

ምሁራኖቻችን እስስቶች በመሆናቸው ያወደሱትን እንደገና አፈር ጥለው አመድ የሚያደርጉት ሌላ ሲተካ እንደገና ተተኪውን ለማወደስ ደቂቃ የማይፈጅባቸው እንደገና እርሱንም ወደ ሰይጣንነት የመለወጥ ‘ተለዋዋጭ መስመራዊ መዋዠቅ’ የሚያጠቃቸው አደገኛ አወዳሾች ስለሆኑ ያልተማረው ሕዝብ ያለ ተከላካይ ለአምባገነኖች አጋልጠውታል።

በቅርቡ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ጻፉት ተብሎ ወዳጄ የላከልኝ ሳነብብ ፕሮፌሰሩ በየሳምንቱ እንደ እስስት የሚለዋወጡበት ፖለቲካዊ ባሕሪ የሌሎች መንጋ ምሁራን ተመሳሳይ የሆነ ገላጭ ማስረጃ ነው። ፕሮፌሰሩ ካሁን በፊት በአማራ አቀንቃኞች ጥርስ ገብተው ብዙ ወቀሳ እንደደረሰባቸው የሚታወቅ ነው። አማራ የሚባል የለም ሲሉ ይከራከሩ እና በመጽሐፋቸው ደግሞ “አማራ ሶማሌውን ሽርጣም እያለ ሲዘልፈው ነበር” እያሉ “አማራ የሚባል የለም” ሲሉ የነበሩትን አማራ “ከሰማይ በገመድ አውርደው” ‘ሶማሌውን አማራ እንዲህ እያለ ሲሰድብህ ነበር’ እያሉ የዘር እሳት ጭረው መጽሐፍ ጽፈው ለታሪክ ትተዋል።

መለስ ዜናዊ ወደ ስልጣን ሲመጣ ለንደን ድረስ ሄደው እንደነበር እና ወያኔዎችን የሚቃወሙትን “እስኪ ረጋ በሉ ልጆቻችን ናቸው እና እንያቸው..” ብለው ሕዝቡን አጃጅለውት ነበር እየተባለ ይወቀሱ እንደነበር አንቤአለሁ።

ዛሬ ደግሞ አብይ አሕመድ መጣ ሲባል ሲጽፉት እና ሲናገሩት የነበረው ‘አምልኮታቸው’ እንደገና 360 ዲግሪ ተገልብጠው ተቃራኒ ጽሑፍ ሲጽፉ ሰነበቱ እና ዛሬ ደግሞ ለማ መገርሳን እያሞገሱ እኛን አሉባልተኞች እያሉ ጥብቅና ገብተው እኛን ሲዘልፉን ታጥቀው ተነስተዋል።

ፕሮፌሰሩ የለማ መገርሳ ቁጣ በሚለው ጽሑፋቸው እንዲህ ይላሉ፡-

“የለማ መገርሳን ቁጣ አንዳንድ ሰዎች እንደፖሊቲከኛ ትርኢት አይተውታል፤ ያለቀሱም አጋጥመውኛል፤ እኔ እንባዬ ጠብ አላለም እንጂ በዓይኔ ላይ አቅርሮ ነበር፤ ይህ ሁኔታ እጅግም አያስደንቅም፤ ኢትዮጵያውያን ስሜታውያን ነን፤ የኔም እንባ ተንጠልጥሎ የቀረበት ምክንያት አእምሮዬ ጥያቄዎችን አጎረፈልኝ። “ በማለት ለማ መገርሳ በቁጣ ሲዋሽ ፕሮፌሰሩ በለማ መገርሳ ንግግር ዓይናቸው ዕምባ ማቅረሩን ነው የገለጹልን። ያውም በስተ እርጅና እውነት ሲነገር እንጂ ውሸት ሲስተጋባ ለምን ዕምባ እንዳቀረሩ ግራ የሚያጋባ ነው። ሆኖም ያን ለመሸፈን “ይህ ሁኔታ እጅግም አያስደንቅም፤ ኢትዮጵያውያን ስሜታውያን ነን” በማለት ለድክመታቸው ጥሩ ሽፋን ፍለጋ ገበተው እንዳንታዘባቸው መርገውታል (በብረት ሰሜንቶ ለስነውታል)።

 

 

የለማ መገርሳ “ጊልቲ” ስሜት በንዴት ለማምለጥ የሞከረበትን አራዳነት ንግግሩ እውነትም “አልቃሽ አላጣም”። ምክንያቱም “ኢትዮጵያውያን ስሜታውያን መሆናችንን  ስለገባው ዒላማው መትቷል። ፕሮፌሰሩ እንዲህ ሲሉ እርሱ ከሚወቀስ እኔ ልወቀስ ብለው በለመድነው እና ብዙውን የኢትዮጵያዊ ምሁራዊ የመንጋ ባሕሪ የሚወክል ለከት የሌለው ውደሳእንዲህ ሲሉ ክበውታል።

“አንድ ሰው በተለይ ዙሪያውን የተከበበበትን ጋሬጣ ሁሉ በጣጥሶ፣ የወያኔን ጭካኔ ተጋፍጦ፣ በአደባባይ በስብሰባ ላይ ለወያኔ ባለሥልጣኖች ልካቸውን የነገራቸውና የሀያ ሰባት ዓመቱን አፈና የደረመሰው ሰው እንደዚህ ምርር ብሎት ሲናገር ያሳዝናል፤ በጣም ያሳዝናል፤ የወያኔ ባለሥልጣኖችን ልብ አፍርሶ፣ ሐሞታቸውን አፍስሶ ፊታቸውን ጥቀርሻ ያለበሰው ሰው ሲያዝን ያሳዝናል፤ በስብሰባው ላይ ሲናገር ያስደሰተኝ በኢትዮጵያዊነቱ ነው እንጂ በኦሮሞነቱ አልነበረም፤ ሲያዝንም ያሳዘነኝ በኢትዮጵያዊነቱ ነው፤ በወያኔ ስብሰባ ላይ ሲናገርም ሆነ አሁን አዝኖ ሲናገር እሱንና እኔን ያያዘን ትልቁ የኢትዮጵያዊነት ገመድ ነው፤ ሁለቱንም ጊዜ የተሰማኝ ኢትዮጵያዊነቱ ነው፤ ከተሳሰርንበት ገመድ ወጥቼ ከምጠራጠረው ገመዱ ውስጥ ሆኜ አምኜው ብሳሳት ይሻለኛል።” ይላሉ::

እንግዲህ ምሁራን ችግራቸው እነሱ የሚክቡት መሪ የተጠራጠረ ዜጋ ሁሉ “ከኢትዮጵያዊነት ገመድ የወጣ ነው ብለው ወስነዋል።በቃ! ይኼ ነው የመንጋ ምሁር ክሽፈት።ሕዝቡን መሪዎችን እንዳይጠረጥር፤ በእርሱ ፈንታ እኔ ልሳሳት እያሉ ሕዝቡን ተጠራጣሪ እንዳይሆን በመሪዎች ጣፋጭ ንግግር እምባ እያቀረረ ዝንተ እለቱ ደንቆሮ ሆኖ እንዲኖር ምሁራን ፈርደውበታል።

እጅግ የማከብረው ኬኒያዊው ምሁር ፕሮፌሰር ፒ ኤል ኦ ኡጋንዳ ዩኒቨርሲ ተጋብዞ ሲናገር ያደመጥኩትን እንዲህ ይላል።

“… not myself a Marxist and have never been one. But the Marxist has beautiful slogans. One of which was this:-

“The safety of bourgeois demand, the proletariat be kept in the most profound ignorance.”

If I step it down into English, it is simply saying that “the safety of the leader demand that the people be kept in poverty”. “And that is what happens in Africa today!”ይላል ፕሮፌሰር ፒ ኤል ኦ።

 

ምሁራኖቻችን እያደረጉት ያሉት “ሕዝቡ በመሪዎቹ ላይ ጥርጥር እንዳያድረው “በተስፋ” እየተመኘ መከራው እንዲቀጥል ማድረግ ነው።ፋሺሰቶቹ የሚፈልጉት  የመንጋ ምሁራን እና መንጋ ጋዜጠኞችን ወደ ካምፓቸው በማስገባት (“ምህረት በመስጠት፤ በመደለል..) ሰፊውን ሕዝብ በተስፋ እየዋለለ በድንቁርና ታስሮ የተጠራቀመ የመሪዎቹ ወንጀሎች ቀስ እያሉ እንዲረሱና ፤ ቀጣይ ወንጀሎችም ነቅቶ ተጠራጥሮ ገዢዎች እና ወንጀለኞች እንዲሁም ዋሾ መሪዎችን በንቃት እንዳይመክት “ሕዝቡ” በደንቁርና አስገብቶ ተጠራጣሪ እንዳይሆን ማድረግ የገዢ መደቦች እና የመንጋ ምሁራን ዋነኛ ማደንዘዣ ግብ ነው።

ማደንቆር ብቻ ሳይሆን ማደህየትም በገዢዎች ስር እንዲወድቅ አዳኝ አድርጎ እንዲያያቸው ማድረግ ሁለተኛው ሜላ ነው።

በዘር ማጽዳት እየተፈናቀሉ ርሃብ ውስጥ ያሉ; በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ እና ማፈናቀሉን ሆን ተብሎ በጥናት የተፈጸመ  መንግሥታዊ ወንጀል ዋነኛ ምክንያት “ሕዝቡ ፋሺሰቶችን” “አዳኝ እና ተከላካይ” አድርጎ እንዲያያቸው ነው። አልገዛም እምቢ ካልክ ‘ማፈናቀሉ ቀጣይ ነው ፥ እነሱ የታጠቁ ናቸው ፥ እንኳን አንተን እኔም እንደልቤ አልዘዋወርም ፥ እኔንም ያሰጉኛል፥ አንተ አልታጠቅክም ባዶ እጅህ ነህ ፥ ስለዚህ እኔ ከሌለሁ የባሰውን ትፈናቀላለህ ፥ ትጨፈጨፋለህ፤ ስለዚህም ያለህ አማራጭ እኔን ሳትጠረጥረኝ ማምለክ ነው!” የሚል ነው በጥበብ እየተካሄደ ያለው የዜጎች መኖሪያ ቤቶች ማፍረስም ሆነ የማፈናቀሉ ዘዴ።

አብይ ከሌለ ፥ ለማ መገርሳ ሲቆጣ እኛ ዕምባ ካለቀረርን “ቄሮ” መጥቶ ፥ “አልሸባብ መጥቶ” ሊጨረሰን፥ ሊያርደን ፥ የበሰ ብጥብጥ ይመጣል እና አንድ እግርህ ብትበላም ሁለተኛዋ እንዳትደገም አርፈህየተሰጠህን አመስግን ይሉናል ምሁራኖቻችን እና ጋዜጠኞቻችን። የባሰ አታምጣ የሚል የተሸብራኪ “የመንጋ ምሁራን ቅስቀሳቸው” ፋሺስቶች እና ብሔረተኞች በሕዝባችን ላይ ይበልጥ እንዲያላግጡ ወንጀለኞችም እንዲበረታቱ በማበረታት መሪዎች “ወደ እግዚአብሐርነት እና ሙሴነት ለውጠዋቸዋል”።

መሪዎችም እግዚአብሐር መሆናቸው ያምኑ እና ወደ እግዚአብሔርነት ተለውጠው እግዚአብሔር የሚሰራውን ሙሉ ስልጣን ይዘው ቢገድሉንቢያስሩንቢያፈናቅሉንአንዴእግዚአብሔር ተብለዋል እናእግዚአብሔር በሚሰራው ሥራ መጠራጥር አይቻልምና የሚያደርጉንንየሚዋሹንን ሁሉ ዕምባ እያቀረርን ግፍን በጸጋ እንደንቀበል እየሰበኩን ነው። የምሁራን መንጋዎች ዛሬም አምባገነኖችን እየካቡብን ተቸግረናልና ሃገራውያን  ሆይ ለዚህ ችግር መላምት ፈልጉ!

ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ ሰማይ)

 

This Post Has One Comment

  1. TM

    Be calm
    Better to see the other side of the coin

Leave a Reply